የአማራን ሕዝብ ማን ይወክለው? ማንስ አይወክለው? እንዴት?

ዳምጠው ሸዋምየለህ – ከደብረብርሃን ከተማ

የአማራ ክልል መንግሥትና የፖለቲካ ሃይሎች የፌደራሉ መንግሥት በትግራይ ክልል ጦርነት ውስጥ እንደገባ ከሁሉም የፌደሬሽኑ አባላትና የአገሪቱ ፖለቲከኞች ሁሉ ቀድመው ከጠቅላይሚኒስትሩ ወገን ቆመው ወደ ጦርነት ገብተዋል፡፡

ጦርነቱን ቀድመው እንደተዘጋጁበት የራሳቸው ባለሥልጣናት (ለአብነት ሟቹ የፖሊስ አዛዥ) ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ አዝማቹ የፌደራሉ መንግሥትና ዋናውና ቀዳሚው ዘማች የአማራ ክልል ለጦርነቱ የሠጡት ትርጉምና ምክንያት ለየቅል ነበር፡፡ለጠቅላይሚኒስትሩ የጦርነቱ ዓላማ ሕግ ማስከበር ሲሆን ለአማራ ክልል ደግሞ ርስት ማስመለስ ነው፡፡

ጠቅላይሚኒስትሩ ሕግ አስከብራለሁ ሲሉ ሕገመንግሥታዊው የአገሪቱ ሠራዊት ስለተጠቃ ይህንን የፈፀሙትን ለሕግ አቀርባለሁ የሚል ምክንያት ነበራቸው (ምንም እንኳን እውነታው ሌላ ቢሆንም)፡፡የጠቅላይሚኒስትሩ ጁኑየር አጋር (Junior Partner) የአማራ ክልል መንግሥትና አጀንዳው የተመቻቸው የክልሉ ልሂቃን (በንግድ፣በሃይማኖት፣በፖለቲካና በመሰል ዘርፍ የተሰማሩ ጦርነቱን የደገፉት ልሂቃን) ግን ኢ-ሕገመንግሥታዊ በሆነ መንገድ በሃይል ግዛት እናመጣለን ብለው ተነሱ፡፡ይህ ከመነሻው ከዋናው አዝማች ጋር ትልቅ ልዩነት ነበረው፡፡ ልክ እንደ ኢፌደሪ መከላከያ ሠራዊት የአገሪቱ ክልሎችም ሕገመንግሥታዊና በሕግ የተቋቋሙ ናቸው፡፡ ሥለዚህ ገና ከጅምሩ የአማራ ክልል ልሂቃን ይህንን ጦርነት ዘው ብለው የገቡበት ሕግ ለማስከበር ሳይሆን ሕግ ጥሰው ግዛት ለማስመለስ ነበር ማለት ነው፡፡

ይህ ማለት ጠቅላይሚኒስትሩ በከፈቱት ጦርነትና የአገሪቱ ሃብት በሙሉ ለዚሁ ዘመቻ በዋለበት አጋጣሚ የኛን ፍላጎት ለማሳካት ትክክለኛ ጊዜው አሁን ነው ብለው የገቡበት ኢ-ሕገመንግሥታዊ ጦርነት ነው፡፡በሌላ ሕገ-መንግሥታዊ ክልል ውስጥ የሚገኝንና በሕጋዊ መንገድ የተካለለን ግዛት ኢ- ሕገመንግሥታዊ በሆነ መንገድ ለማምጣት በማለም ነው የአማራ ክልል ይህንን ጦርነት የገባበት፡፡

ስለዚህ የአማራ ክልል ሃይሎች የጠቅላይሚኒስትሩ አጋር ሆነው ወደ ዘመቻ የገቡት የጠቅላይሚኒስትሩን ሕግ የማስከበር ዘመቻ ከለላ አድርገው የራሳቸውን አጀንዳ ለማስፈፀም ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከጠቅላይሚኒስትሩ የሕግ ማስከበር ‹ሬቶሪክ› የተቃረነ ነው፡፡
በሰሜን ዕዝ ላይ ተፈጽሟል የተባለው ጥቃት የሁሉም ክልሎችና የፌዴራሉ መንግሥት ጉዳይ ነው፡፡ይሁን እንጂ ከሁሉም ክልሎች በፈጠነ ሁኔታ ቀድሞ ወደ ጦርነቱ የገባው የአማራ ክልል ነው፡፡ገና ጦርነቱ ጥቅምት 24-2013 ሌሊት እንደተጀመረ ትግራይን መውጋት እንደጀመረ የያኔው የክልሉ ርዕሰመስረዳድርና የወቅቱ የፖሊስ አዛዥ ተናግረዋል፡፡የያኔው የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተመስገን ጥሩነህ ‹‹ከዚህ በኋላ የሸረሪት ድር አንጠርግም፤ሸረሪቷን እናጠፋታለን እንጂ›› በማለት ነበር- ሕወሓትን ለማጥፋት የክልላቸውን ሐብትና ሠራዊት ሁሉ እንደሚያሰማሩ የገለጹት፡፡

ሕወሓት መጥፋት ካለበትም የማጥፋት መብት ያለው በቅድሚያ መብቱ የትግራይ ሕዝብ ነበር፡፡ሕወሓት የአገር ደህንነት ችግር ከሆነም ይህንን ሥራ መሥራት ያለበት የፌደራሉ መንግሥት እንጂ የአማራ ክልል አልነበረም፡፡ይሁን እንጂ ከአገሪቱ ዘጠኝ ክልሎች ሁሉ ቀድሞ ትግራይን እያስተዳደረ ያለውን ፓርቲ አጠፋለሁ ብሎ በመርህም በሕግም ያልተደገፈ ወረራ በትግራይ ክልል ፈፀመ፡፡

የአማራ ክልል አመራሮች ይህንን ወረራ ለመፈፀም አስቀድመው ተዘጋጅተው እንደነበር በኋላ ላይ ከማመናቸው በፊት በወቅቱ እንደምክንያት ለማቅረብ የሞከሩት በዳንሻ በኩል ተጠቃን የሚልን ሀሳብ ነበር፡፡በመሰረቱ መንግሥት ሕገመንግስታዊ ሥርዓቱን ለማስከበር ጦሬን ወደ ትግራይ አዝምቻለሁ እስካለበት ጥቅምት 24 ድረስ ዳንሻ በሕገመንግሥቱ መሠረት በትግራይ ክልል ውስጥ የሚገኝ ግዛት ነው፡፡በዚህ ግዛት ውስጥ የአማራ ክልል ሠራዊትም ሆነ ጦር ሰፈር አልነበረም፡፡ለዚህ ነው ሀሰተኛ ምክንያት ፈጥረው የክልሉን ሀብት አንቀሳቅሰው በትግራይ ክልል በተፈፀመው ወንጀል ላይ ተሳታፊ ሆነዋል የሚባለው፡፡

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳለው እነዚሁ የአማራ ሃይሎች በትግራይ ክልል ባደረጉት ወረራ ቢያንስ 1.2 ሚሊዮን ሕዝብ በማባረርና በመግደል የዘር ማጽዳት ፈጽመዋል፤አንድ የቤልጂየም ዩኒቨርሲቲ ደግሞ በትግራይ ክልል ከተፈፀመው አስገድዶ መድፈር ውስጥ ከ10 በመቶ በላይ የሚሆነውን የፈፀመው የአማራ ልዩ ሃይል ነው ብሏል፡፡ሮይተርስ በማይካድራ ባደረገው ምርመራ ደግሞ የአማራ ልዩ ሃይልና ሚሊሺያ ወደ ከተማዋ ከገባ በኋላ ዘግናኝ ጭፍጨፋ (ቀደም ሲል ለተፈፀመው ጥቃት አፀፋ) መፈፀሙን አጋልጧል፡፡
የአማራ ክልል መንግሥትና ፖለቲከኞች ይህንን ጦርነት ከሰማይ እንደወረደ መና ደግፈውት ተንቀሳቅሰዋል፡፡ጠቅላይሚኒስትሩ ለጦርነቱ የሚያስፈልጋቸውን ሁሉንም ነገሮች ከአማራ ክልል አግኝተዋል፡፡ጠቅላይሚኒስትር ዐቢይ በትግራዩ ጦርነት በአምስት ዘርፎች ድጋፍ ያስፈልጋቸው ነበር፡፡

እነዚህም ወታደራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ የሎጅስቲክስ፣ የዲፕሎማሲና የፕሮፓጋንዳ ድጋፎች ናቸው፡፡


እነዚህን አምስቱንም ድጋፎች ደግሞ ሙሉ በሙሉ ያገኙት ከአማራ ልሂቃንና መንግሥት ነው፡፡ይህ ማለት ግን በትግራይ ላይ የተካሄደውን ጦርነት ሁሉም የአማራ ልሂቃን እና ሕዝቡ ደግፎታል ማለት አይደለም፡፡በትግራይ ላይ የተከፈተው ጦርነት አገሪቱን እንደሚያጠፋ ተረድተው፣በትግራይ ሕዝብ ላይ የሚያደርሰውን እልቂትም ተገንዝበው፣ ለአማራ ሕዝብም መዘዝ ይዞበት እንደሚመጣ ገብቷቸው ይህንን ጦርነት የተቃወሙ ከአማራ ክልል የወጡ ፖለቲከኞች ነበሩ፡፡

ይሁን እንጂ ድምፃቸውም አናሳ፣ጩኸታቸው የቁራ ጩኸት ሆኖ ያለ አድማጭ ቀርቷል፡፡ በኋላም የፈሩትም ደርሶ፣የትግራይ ሕዝብ ፍዳውን አየ፤የአማራ ሕዝብም መዘዙ ደረሰበት፤ኢትዮጵያም አፋፍ ላይ ቆመች፡፡
የአማራ ሕዝብም ቢሆን ይህንን ጦርነት ደግፎ አልቆመም፡፡ የክልሉ ሕዝብ ይህንን ጦርነት ደግፎ ቢሆን ኖሮ ጦርነቱ ከትግራይ ክልል በዚህ ፍጥነት ሊወጣ አይችልም፤እንዲህ ያለ መልክም ሊኖረው አይችልም ነበር፡፡በቀጥታ አገላለጽ ጦርነቱ በአማራ ሕዝብ ተደግፎ ቢሆን ኖሮ በሁለቱ ሕዝቦች መካከል የሚኖረው እልቂትም ሆነ ጦርነቱ በትግራይ የሚኖረው ቆይታና የትግራይ አሸናፊነት ወይ ይዘገያል፤ወይም አይሳካም ነበር፡፡ይህ የሚሆነው ደግሞ የአማራ ሕዝብ ከትግራይ የተሻለ ጀግና ስለሆነ አለያም የትግራይ ሕዝብ የትግል ምክንያት ስለሌለው አይደለም፡፡ትግሉ የሚፈልገው የሰው ሃይልና ሀብት ከትግራይ የተሻለ አማራ ክልል በብዛት ያለ በመሆኑ ነው፡፡

ይሁን እንጂ የአማራ ሕዝብ ይህንን በትግራይ ላይ የተከፈተን ጦርነት ስለማይፈልገው የትግራይ ሠራዊት ትግሉን በወራሪዎቹ የአማራ ሃይሎችና በዋና አዝማቻቸው በጠቅላይሚኒስትሩ ላይ አነጣጥሮ ያካሄደውን ዘመቻ በስምንት ወራት ውስጥ መቀልበስ ችሏል፡፡ከትግራይ ክልል አስወጥቶም በአማራ ክልል ዞኖች ውስጥ አስፋፍቷል፡፡

መንግሥት በሕዝቦች መካከል ያለውን ጠላትነት ለማስፋት ‹‹ደጀኔ ወዳልኩት ቦታ ላይ ሠራዊቴን አስፍሬያለሁ›› ብሎ አማራ ክልል ቢገባም በለስ አልቀናውም፡፡

የአማራ ሕዝብ ይህንን ጦርነት እንደማይደግፈው የትግራይ ሠራዊት በወሎና ሰሜን ሸዋ በገባ ጊዜ የገጠመው መልካም አቀባበል (ቢያንስ ሕዝባዊ ተቃውሞ የሌለው መሆኑ) ማሳያ ነው፡፡የአማራ ክልል መንግሥትና የጠቅላይሚኒስትሩ ጋሻጃግሬ የክልሉ ልሂቃን ይህንን ጦርነት በተለያየ መንገድ በመቀስቀስ ለስድስተኛ ጊዜ የክተት አዋጅ ጠርተው በምኒልክም በማርያምም፣በሼህ ሁሴን ጅብሪልም…ቢማፀኑት ጆሮ ዳባ ልበስ ብሏቸዋል፡፡

ይህ የሆነው የትግራይ ሠራዊት በአንፃራዊነት የተሻለ ዲሲፒሊኑ ስላለው ብቻ አይደለም፤የአማራ ሕዝብ የክልሉን መንግሥትና ልሂቃን ጦረኛ አጀንዳ መግዛት ስላልቻለና በትግራይ ወንድሞቹ ላይ የተከፈተው ጦርነት ፍትሐዊ አለመሆኑን በማመኑም እንጂ፡፡ሕዝብ በጋራ ጠላቶቹ ላይ ሲዘምትና ሕዝባዊ ትግል ሲያደርግ ቢያንስ በትግራይ አይተናል፡፡ይህንን በአማራ ሕዝብ በኩል ያላየነው የትግራይ ሠራዊት ፀረ ሕዝብ አጀንዳ ስላላነገበ ብቻ ሳይሆን የአማራ ሕዝብ ከሚመሩት ልሂቃንና ፖለቲከኞች ጋር የተፋታ ስለሆነ ነው፡፡ከዚህ በተጨማሪም የክልሉ ሕዝብ በትግራይ ላይ የተከፈተው ጦርነት ለሶስት ሺህ ዘመናት አብረው የኖሩ ወንድማማቾችን ደም ለማቃባት የተካሄደ አውዳሚ ውጊያ መሆኑን ስለተረዳ ነው፡፡

የአማራ ልሂቃን እንዴት ጦርነቱን ደገፉት?
የአማራ ክልል መንግሥትና በአማራነትም የተደራጁ ይሁኑ በሌሎች አደረጃጀቶች ውስጥ ያሉት የክልሉ ፖለቲከኞች (ለምሳሌ ኢዜማና ባልደራስ ውስጥ ያሉ አማሮች፣በቤተክርስቲያኖች ውስጥ ያሉ አንዳንድ የሃይማኖት መሪዎች) በግልም ይሁን በድርጅቶቻቸው በኩል ጠቅላይሚኒስትሩ ለሥልጣናቸው መጠናከር የከፈቱትን ይህንን ጦርነት በሚከተሉት አምስት ዘርፎች በመደገፍ አስተዋጽኦ አበርክተውላቸዋል፡፡ጠቅላይሚኒስትሩ አምስቱንም ድጋፎች በተለየ ሁኔታ ከአማራ ልሂቃን ብቻ ነው ያገኙት፡፡

1-ወታደራዊ

ጦርነቱ በቀዳሚነት የሰው ሃይል ድጋፍ ያስፈልገው ነበር፡፡የሰው ሃይሉ ደግሞ በወታደር የሚለካ ነው፡፡ጠቅላይሚኒስትሩ በትግራይ ላይ ጦርነት ለመክፈት ሲንቀሳቀሱና ሌሎቹን እዞቻቸውን ወደ ትግራይ ሲያንቀሳቅሱ የሰሜን ዕዝን አስቀድመው ለምርኮ አጋልጠውታል፡፡

እርሳቸው እንዳሉት የአገሪቱ ሠራዊት በትጥቅም፣በሰው ሃይልም ተደምሮ ሰሜን ዕዝን አያህልም ነበር፡፡ይህ ሠራዊታቸው ግን ከነሙሉ ትጥቁ ተማረከ፡፡ስለዚህ ይህንን የወታደር ጉድለታቸውን በፍጥነት የሚሞሉበት መንገድ ያስፈልጋቸው ነበር፡፡ለዚህ ደግሞ የአማራ ክልል ልሂቃንና መንግሥት ቀድመው አለሁ ብለው የክልሉን ሚሊሺያና ልዩ ሃይል ከነ ትጥቁ አስገብተውታል፡፡ስለዚህ ይህንን ወታደራዊ ድጋፍ በቀዳሚነት ከአማራ ክልል በማግኘት አሳክተዋል፡፡ሌሎቹ ክልሎች እጅግ ዘግይተው ነው-ወደ ጦርነቱ የገቡት፡፡ በተለይም ጦርነቱ ከትግራይ ወጥቶ ወደ ሌሎች የአማራና የአፋር ክልሎች ከገባ በኋላ!

2-ፖለቲካዊ

ጦርነቱ ከወታደራዊ ድጋፍ በተጨማሪ እጅጉን የሚያስፈልገው ፖለቲካዊ ድጋፍ ነበር፡፡ጦርነቱ ፖለቲካዊ ድጋፍ አገኘ ማለት ከገዥው ፓርቲ በተፃራሪ የቆምን ፓርቲዎች ነን የሚሉ ሃይሎች መንግሥት የሚያካሂደውን ጦርነት በድርጅት ደረጃና በደጋፊዎቻቸው ደረጃ ቅቡል እንዲሆን አደረጉ ማለት ነው፡፡ከዚህ አንፃር መንግሥት የተሟላ ድጋፍ አግኝቷል ከተባለ አማራ ነን ብለው ከተደራጂ የፖለቲካ ሃይሎችና የአማራ ከሚመስሉ ግን ደግሞ አገር አቀፍ ነን ከሚሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ብቻ ነው፡፡በቀጥተኛ አባባል ይህንን ጦርነት ፖለቲካዊ ድጋፍ ሰጥተው መግለጫ ያወጡትና በተግባርም የተንቀሳቀሱት የአማራ ድርጅት ነኝ የሚለው አብን፣የአማራ ተወላጅ ልሂቃን የሚበዙበት ኢዜማና ሙሉበሙሉ በሚባል ደረጃ የአማራ ተወላጅነት ያላቸው ሰዎች የተሰባሰቡበት ባልደራስ ብቻ ናቸው፡፡

ከአብን፣ከኢዜማና ከባልደራስ ውጭ አንድም የፖለቲካ ድርጅት በይፋ ይህንን ጦርነት የደገፈ የለም፡፡እነዚህ ድርጅቶች ደግሞ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አማራ ነን የሚሉ ሰዎች በተለያየ አልባስ የተሰባሰቡባቸው ናቸው፡፡

ይህ የጠቅላይሚኒስትሩ ጦርነት በሌሎች ክልል ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች እንዲህ ያለ ድጋፍ አላገኘም፡፡ ይልቁንም ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡በኦሮሚያ ውስጥ ለመንቀሳቀስ የተመዘገቡት እንደ ኦፌኮና ኦነግ ያሉት ፓርቲዎች በይፋ ጦርነቱን ተቃውመዋል፤የሱማሌ ክልሉ ኦብነግ በግልጽ ቋንቋ የትግራዩን ጦርነት አውግዟል፤ደቡብ ላይ ያሉ ፓርቲዎችም (የወላይታና የሲዳማ ድርጅቶች) ይህንን ጦርነት ኮንነዋል፡፡በአማራ ክልል ለመንቀሳቀስ የተመዘገቡ ሁሉም ፓርቲዎች ግን ይህንን ጦርነት ደግፈውታል፡፡

የሁሉም ክልሎች መንግሥታት እንደ አማራ ክልል አቻቸው ጉልህ ተሳትፎ ባይኖራቸውም በተለያየ መልኩ ደግፈውታል፡፡መንግሥታቱ ጦርነቱን ለሥልጣናቸው ማጠናከሪያ እንደመሣሪያ ስለሚያዩት (ምክንያቱም የጠቅላይሚኒስትሩን የጦርነት እቅድ ተቃውመው አንድ ቀንም ማደር እንደማይችሉ ስለሚያውቁ) ጦርነቱን ቢደግፉት ላያስገርም ይችላል፡፡ መንግሥትን መቃወምና አማራጭ የሠላም፣የልማትና የዴሞክራሲ እቅዶችን በማቅረብ አገርን ማሻገር ግባችን ነው የሚሉ ተቃዋሚዎች ግን መንግሥት ለሥልጣኑ ማጠናከሪያ ይሆናል ብሎ ያሰበውን ጦርነት ግፋ በለው ማለታቸው አስደናቂ ነው፡፡ይህንን አስደናቂ ተግባር በብቸኝነት የፈፀሙት ደግሞ አማራ ነን ብለው የተደራጁና ኢትዮጵያዊ ነን በሚል የተሰባሰቡ በብዛት የአማራ ተወላጆች የሚገኙባቸው ድርጅቶች ናቸው፡፡ለጦርነቱ ፖለቲካዊ ድጋፍ በዚህ ልክ ሞቅ አድርጎ በመለገስ ጦርነቱ ላይ ተሳትፏል-የአማራ ፖለቲካዊ ሃይል!

ይህ ማለት ግን የአማራ ተወላጆች ያሉባቸው ወይም የሚመሯቸው ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች ጦርነቱን ደግፈውታል ማለት አይቻልም፡፡ለምሳሌ እንደ ሕብር ኢትዮጵያ ያሉ ፓርቲዎችና አመራሮቻቸው ጦርነቱን በግልጽ አውግዘዋል፡፡

3-የሎጀስቲክስ

ይህ የጠቅላይሚኒስትር ዐቢይ ጦርነት ከላይ ከተቀመጡት ድጋፎች በተጨማሪ ከአማራ ክልል መንግሥትም ጦርነቱን የሚደግፍ ሎጅስቲክስ በሚገባ አግኝቷል፡፡የክልሉ መንግሥት በምግብ አቅርቦት፣ በጤና ተቋማት ድጋፍ፣በትጥቅና መሰል መስኮች ጦርነቱን አግዟል፡፡

በግንቦት 2013 ዓ.ም የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ለፌደራል መንግሥቱ በፃፈው የካሳ መጠየቂያ ደብዳቤ ላይ እንዳስቀመጠው የቆሰሉ የሠራዊቱ አባላትን ለማከምና ለመመገብ ብቻ ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ፈሰስ ተደርጓል፡፡ይህ በጤናው ዘርፍ ብቻ ነው፡፡ በትጥቅና በሌሎች መስኮችም ከዚህ ያላነሰ እንደሚወጣ ይገመታል፡፡ምክንያቱም የክልሉ መንግሥት የክልሉን ልዩ ሃይልና ሚሊሺያ ወደ ትግራይ ያዘመተው በራሱ በጀት ያስታጠቀውንና የሚቀልበውን ሠራዊት ነው፡፡በዚህ ልክ በሎጀስቲክስ ዘርፍ የተሳተፈ አንድም ክልል የለም-ከአማራ ክልል ውጪ!

4-የዲፕሎማሲ

ጦርነቱ እጅጉን ከሚፈልጋቸው ነገሮች አንዱ ዲፕሎማሲ ነበር፡፡ይህንን ድጋፍ ለማግኘትም ጠቅላይሚኒስትሩ ብዙ ታትረዋል፡፡ይህንን ለማድረግም ከጎናቸው የቆሙት በዋናነት በውጪ የሚኖሩ የአማራ ተወላጅና የሻዕቢያ ደጋፊ ዳያስፖራዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ሃይሎች (በተለይም የአማራ ፖለቲከኛ ዳያስፖራዎች) ይህንን ጦርነት የሕግ ማስከበር ዘመቻ ነው ብለው ለማሳመን በብራስልስ፣ በኒዮርክና በዲሲ ጎዳናዎች ላይ በመሰለፍ ብዙ ጥረዋል፡፡ውጤታማ ያልሆነው ይህ እንቅስቃሴ በበላይነት የተመራው ደግሞ የአማራ ተወላጅ ነኝ በሚሉትና በጦርነቱ ጅማሮ ማግስት የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው በተሾሙት አቶ ደመቀ መኮንን ነው፡፡ይህ የአማራ ልሂቃን ተሳትፈውበት፣የአማራ ልሂቃንም መርተውት በሽንፈት የተጓዘ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ የጠቅላይሚኒስትሩን የጦርነት አጀንዳ ለመደገፍ ተብሎ በአማራ ሃይሎች የተደረገ ጥረት ነበር ማለት ይቻላል፡፡

5-የፕሮፓጋንዳ 

ይህ የጦርነት ዘመን በትልቁ የሚፈልገውን የፕሮፓጋንዳ ዕቅድ በዋናነት ያገኘው ከአማራ ልሂቃን ነው፡፡የአማራ ልሂቃን ለጠቅላይሚኒስትሩ የጦርነት ዕቅድ ያላቸው ልግስና ከላይ በተገለጹት ድጋፎች አላቆመም፡፡ልሂቃኑ የፖለቲካም ሆነ የወትድርና፣የሎጅስቲክስም ሆነ የዲፕሎማሲ ድጋፉን ይገልጹ የነበረውና ሕዝቡንም ለማሳመን ይሞክሩ የነበሩት በሚዲያ ፕሮፓጋንዳ ነው፡፡ጦርነቱን ደግፈው የቆሙ የሃይማኖት አባቶች፣እልቂቱን ያበረታቱ ፖለቲከኞችና ባለሃብቶች በብዛት የታዩት ከአማራ ክልል ነው፡፡

በአማርኛ በሚሰራጩ የመንግሥት የፕሮፓጋንዳ ሥራዎች ላይ በብዛት የሚሳተፉት የአማራ ልሂቃን  መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ በግል የሚንቀሳቀሱና በአማርኛ የሚሰሩ አክቲቪሥቶች፣የማሕበራዊ ሚዲያ (ለምሳሌ ዩቱዩብ) ተንቀሳቃሾች፣የአማራ ተወላጆች የሚበዙባቸው (ለምሳሌ ሪፖርተር ጋዜጣ፣አርትስ ቴሌቭዥን) ወይም የሚመሯቸው ሚዲያዎች (ለምሳሌ ኢሳት፣ኢትዮ 360፣ፍትሕ መጽሔት፣)  ወዘተ የትግራዩን ጦርነት ደግፈው መንግሥትም እንዴት ማካሄድ እንዳለበት (ለምሳሌ የኤርትራን ጦር ማስገባት እንደሚገባው፣በትግራይ በኩል 250ሺህ ሠራዊት ስላለ መንግሥት በዚያ ልክ መዘጋጀት እንዳለበት ወዘተ) ሲሰብኩ ከርመዋል፡፡ 

መንግሥት በትግራይ የከፈተውን ጦርነት በሰላም እንዲፈታ ወይም እንዲያቆም  የጠየቀ በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀስ ሚዲያ አልነበረም ማለት ይቻላል፡፡የጦርነቱን አውዳሚነትና አገር አፍራሽነት ለመዘገብ የሞከሩ ጋዜጠኞችና መገናኛ ብዙሃንም እንዲዘጉና እንዲታሰሩ ተደርጓል (ለምሳሌ ኢትዮ ፎረም፣አውሎ ሚዲያ፣አዲስ ስታንዳርድ ወዘተ)፡፡ 

መንግሥት የትግራዩን አውዳሚ ጦርነት ሲያካሂድ በግል የሚንቀሳቀሱትንም ሆነ በእርሱ ሥር ያሉትን (በዋናነት አማርኛ ተናጋሪ የፕሮፓጋንዳ ሃይሎቹን) ሚዲያዎች ለዚህ ጦርነት ሲያውል የአማራ ልሂቃን የአንበሳውን ድርሻ ወስደው ከአገር ውስጥ እስከ ውጪ ተሳትፈዋል፡፡ 

 የአማራ ክልል ልሂቃን ምን አተረፉ

የአማራ ክልል መንግሥትና ልሂቃኑ የጠቅላይሚኒስትሩን አጀንዳ ከለላ አደርገው የራሳቸውን ዕቅድ ለማሳካት የገባቡትን  ጦርነት፣አትራፊም አሸናፊም ሳይሆኑበት ቀርተዋል፡፡በጦርነቱ እናሳካዋለን ያሉትን የግዛት ማስመለስ (ወልቃይትና ራያ) አጀንዳ ሳያሳኩ ቀርተዋል፡፡ይህ ብቻ ሳይሆን ይህ ጽሁፍ እስከተፃፈበት ድረስ ከሁለቱ ጎጃሞች (ምሥራቅና ምዕራብ) በስተቀር ሁሉንም ዞኖቻቸውን ለትግራይ ሠራዊት አስረክበዋል፡፡የትግራይ ሠራዊት ግዛቶችን በጉልበት ወደ ትግራይ ክልል የማካለል ፍላጎትና አጀንዳ ቢኖረው ኖሮ ሰሜንና ደቡብ ወሎ፣ዋግኸምራና የኦሮሚያ ልዩ ዞን ሙሉ በሙሉ፣ሰሜን ሸዋና የጎንደር ዞኖች ደግሞ በከፊል የትግራይ ግዛት ይሆኑ ነበር፡፡ 

ስለዚህ የአማራ ልሂቅ እወክለዋለሁ የሚለውን ሕዝብ ለሰብዓዊ፣ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ ኪሳራ ከመዳረግ በዘለለ ከዚህ ጦርነት ያተረፈለት አንድም ነገር የለም፡፡ይልቁንም ለደረሰበት ሽንፈት ሕዝቡን ተጠያቂ ማድረግ ጀምሯል፡፡በተለይ የወሎንና የአዊን እንድሁም የከሚሴን ሕዝብ እየኮነነ (የቀድሞው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድሮች  አገኘሁ ተሻገርና ገዱ አንዳርጋቸው እንዲሁም የአብን አመራሮችና የተናገሯቸውን ንግግሮች መጥቀስ ይቻላል) እና ለሽንፈቱ እየወነጀለ ቀጥሏል፡፡ 

አስገራሚው ነገር ከላይ የተገለጹት የአማራ ፖለቲከኞች አምርረው የሚጠሉትን የትግራይን ሕዝብና ሕወሓትን እስከመጨረሻው ለማሸነፍ ሁኔታዎች ሁሉ ተመቻችተውላቸው መሸነፋቸው ነው፡፡ጦርነቱ የኢትዮጵያ ሙሉ አቅምና የአማራ ክልል መንግሥትና ከላይ የተጠቀሱት ልሂቃን የተቀናጁበት ብቻ ሳይሆን ፣የተባበሩት ኤምሬትስ፣የኢራንና የቱርክ ድሮን፣የኤርትራና የሶማሊያ ሠራዊት የዘመተበት ነው፡፡ 

በሌላ አገላለጽ የአማራ ሃይሎች ይህንን ጦርነት የተሸነፉት የራሳቸውን ክልል መንግሥታዊና ግላዊ አቅም ከአገሪቱ ጠቅላላ አቅም ጋር እንዲሁም ከምሥራቅ አፍሪቃ ሠራዊትና ከዘመኑ የጦር  ቴክኖሎጂ ጋር አዳምረው ከዘመቱ በኋላ ነው፡፡አጋጣሚው ፋኖ፣ሚሊሺያ፣ልዩ ሃይል ወዘተ በማለት ከራሳቸው አቅም በዘለለ የማዕከላዊ መንግሥቱን ሀብትና ማዕከላዊ መንግሥቱ የሚያሰባስበውን የውጪ ሃይል ለመጠቀም ያገዛቸው ቢሆንም ከመሸነፍ አልተረፉም፡፡የሽንፈታቸው ምክንያት ደግሞ በመጀመሪያ በአማራ ሕዝብ ስላልተደገፉ ሲሆን በሁለተኛ ደግሞ ኢ-ፍትሐዊ ጦርነት ውስጥ ስለገቡ ነው፡፡ ያልተደገፉት ደግሞ ኢ-ምክንያታዊ (causeless) ስለሆኑ  ነው።

አማራን ማን ይወክለው

አሁን ወደድንም ጠላንም አንድ ያገጠጠ እውነት የምንጋፈጥበት ወቅት ቀርቧል፡፡ትግራይ የተፈፀመባትን ጭፍጨፋ፣ረሃብ፣አስገድዶ መደፈርና መሰል ኢሰብዓዊ ጥቃት አሸንፋ በዓለምም ሆነ በኢትዮጵያውያን ፊት ልትከሰት የትግራይ ሠራዊትን ከፊት አስቀድማለች፡፡ 

ጥቅምት 24/2013 የተጀመረውን ጦርነት የአማራ ሃይሎችን ጁኒየር አጋር ያደረገው መንግሥት በ15 ቀናት አሸንፎ መቀሌን ተቆጣጥሮ ነበር፡፡የራሱን ታዛዥና ታማኝ አስተዳደርም አቋቁሞ ነበር፡፡ይሁን እንጂ መንግሥት ያሰማራው ሠራዊትና ወደ ትግራይ ያስገባው የአማራና የኤርትራ ጦር በንፁሃን ላይ የከፈተው ጥቃት ያንገሸገሻቸው የትግራይ ወጣቶችና ተበትኖ የነበረው ልዩ ሃይል እንደገና ተደራጅተው የመሠረቱት የትግራይ ሠራዊት በዱሮ የሕወሓት ታጋዮች እየተመራ አዲስ አበባ ሊገባ ጥቂት የጦር አውድማዎች ቀርተውታል፡፡በሌላ አገላለጽ ከጠቅላይሚኒስትሩም በላይ የአማራ ሃይሎችና ልሂቃን ከባድ ሽንፈት ተከናንበዋል ማለት ነው፡፡ይህ ማለት ግን ሕዝቡ ተሸንፏል ማለት አይደለም፡፡ሕዝቡ ወትሮም ስላልደገፋቸው ባልተሳፈበት ጨዋታ ተሸንፏል ማለት አይቻልም፡፡ 

የትግራይ ሠራዊት (አሁን ደግሞ የኦሮሞ ነፃነት ጦርም አለ ተብሏል) ለድል ከበቃ በኋላ የሚፈጠረው መንግሥታዊ ሁኔታ ተወደደም ተጠላም ብሔርተኛ ሃይሎች የሚሳተፉበትና ወሳኝ የሚሆኑበት ነው፡፡ይህ ደግሞ ገና ከአሁኑ የተጀመረ ይመስላል፡፡በአሜሪካ የተሰባሰቡትና ግንባር የፈጠሩት የፖለቲካ ሃይሎች ለዚህ ማሳያ ናቸው፡፡ይህ ግንባር እየሰፋ መሄዱ ደግሞ አይቀርም፡፡አሁን ያለው የአማራ ልሂቅና የፖለቲካ ሃይል ደግሞ የአማራን ፖለቲካ የግዛት አርበኛ፣የሰው ፈላጊ፣በጥባጭና ጨፍላቂ ተደርጎ እንዲሳል በማድረግ ለትብብርና ለድርድር የማይፈለግና የሚፈራ አድርጎታል፡፡ሁሉም የአገሪቱ ብሔርተኛ ሃይሎች የፖለቲካ እንቅስቃሴያቸውና አጀንዳቸው አሁን የአማራ ሃይሎች ከሚሄዱበት የፖለቲካ አካሄድ በተፃራሪ የሚሄድ ነው፡፡

በዚህ ሂደት ውስጥ ከ30 ሚሊዮን የሚልቀው የአማራ ሕዝብ በማን ይወከል የሚለው ጥያቄ መምጣት አለበት፡፡ይህንን ጥያቄ ስናስብ በቅድሚያ የክልሉ የፖለቲካ ተዋንያን እነማን ናቸው፣የክልሉን ፖለቲካስ ከፊት ሆነው የሚመሩት፣ከኋላ ሆነው የሚያሽከረክሩት እነማን ናቸው የሚለውን ጥያቄ መመለስ ያስፈልጋል፡፡ለዚህ ጥያቄ መልስ ስንፈልግ አሁን በይፋ የሚታወቁት የፖለቲካ ሃይሎች (አብን፣አማራ ብልጽግና ውስጥ ያሉ ወዘተ) ወደ አእምሯችን ሊመጡ ይችላሉ፡፡ግን የአማራን ፖለቲካ ጨዋታ የሚዘውሩት ተዋንያን ጥቂት ባለሃብቶች፣እነርሱ ያሰማሩት የማሕበራዊ ሚዲያ ሃይልና በስውር የተደራጀ ታጣቂና ያልታጠቀ ሃይል ነው፡፡እነዚህን በሁለት ዘርፍ ጠቅለል አድርገን መግለጽ እንችላለን፡፡ የመጀመሪያዎቹ፣መንግሥታዊ ነጠቃ የፈጸሙ (State Caputer) ባለሃብቶችና የጦርነቱን ሂደት የገቢ ምንጭ ያደረጉ (ለምሳሌ ጦር መሣሪያ በማቅረብ፣ብድር ለማግኘት ሲባል የመንግሥትን ቀልብ ለመሳብ ሲሉ በጦርነት ቅስቀሳ ላይ በመሳተፍ)፣ከጦርነቱም ውጤት ተጠቃሚ ለመሆን ያለሙ (በትግራይ ክልል ሥር ያሉ የሰሊጥ እርሻ መሬቶችን ለመጠቅለል) ናቸው፡፡እነዚህ ባለሃብቶች እና እነርሱ ያሰማሩት የማሕበራዊ ሚዲያ ሃይል የክልሉን መንግሥት የሚመራና ፖለቲካዊ አጀንዳን የሚቀርጽ ነው፡፡

በሁለተኛ ደረጃ የሚቀመጡት በስውር መንግሥትነት (Deep State) የተሰማሩት ናቸው፡፡እነዚህኞቹ በተለይም የቀድሞው የመከላከያ ሠራዊት ውስጥ የነበሩ ወታደሮች ያሰለጡኑትና እነርሱን የሚከተል የታጠቀና ያልታጠቀ ሃይል ነው፡፡ፋኖ በሚል ስም ይጠሩታል፡፡ፋኖ ወጥነት ባለው አደረጃጀት ውስጥ የገባ ሳይሆን በአውራጃዊነት ለተከፋፈለው የክልሉ ሃይል መጠባበቂያ ሆኖ የተዘጋጀ ነው፡፡የጎፋም ፋኖ፣የጎንደር ፋኖ ወዘተ እየተባለ የሚጠራ በአውራጃዊነት በሚናናቅና በሚወነጃጀል ሃይል የሚመራ ነው፡፡(ይህ ግን የክልሉን ብሔረሰብ ዞኖች አይመለከትም)!

እንግዲህ የአማራ ፖለቲካ በግልጽ ከሚታወቁት የፖለቲካ ድርጅቶች (የአማራ ብልጽግና አብን ወዘተ) በተጨማሪ እንዲህ ባሉ ኢመደበኛ ሃይሎችም የሚዘወር ነው፡፡እነዚህ ወንጀለኞችና በትግራዩ ፀረ ሰው ጭፍጨፋ ላይ የተሰማሩ በመሆናቸው ወደ ፍርድ ቤት እንጂ ወደ ሽግግር ምክር ቤት የመግባት እድላቸው ጠባብ ሊሆን ይችላል፡፡ምናልባት በአሸናፊው ሃይል ምሕረትና ይቅርታ ከተደገላቸውና ድርጅታዊ ሕልውናቸው ተጠብቆ በግለሰብ ደረጃ በጦርነቱ ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ ያደረጉ ሰዎች ብቻ ይሳተፉ ከተባለ በቀጣዩ የሽግግር ሂደት ውስጥ ለመሳተፍ ቢያንስ ሶስት ነገሮችን ማመን አለባቸው፡፡ 

አንደኛ እስካዛሬ የተጓዙበትን ጦረኛ መንገድ ሕዝቡ እንደማይደግፍላቸው (ምክንያታዊ ጦርነት ቢያደርጉና ቢደግፍላቸው ኖሮማ ጦርነቱን ያሸንፉ ነበር)፣ሁለተኛ የአገሪቱን ሃብትና የዘመኑን የጦር ቴክኖሎጂ እንዲሁም የምሥራቅ አፍሪቃን ጦር አስተባብረው ማሸነፍ ያልቻሉትን ጦርነት ከዚህ በኋላ ለማሸነፍ ይህንን የመሰለ እድልና አጋጣሚ እንደሌላቸው (በኮዝም በድጋፍም)፣በሶስተኛ ደረጃ በተዋለደውና በተዋደደው፣አብሮ በኖረው የትግራይና የአማራ ሕዝብ መሀል ለፈጠሩት ደም መቃባት ለነበራቸው አስተዋጽኦ በግልጽ ይቅርታ መጠየቅ፡፡ 

እነዚህን ሁነቶች አምኖ የሚቀበል ደፋር ከተገኘ የአማራ ሕዝብን መሠረታዊ ጥቅሞች ለማንሳትና ሕዝቡንም ወክሎ ለመደራደር ወኔ ይኖረዋል፡፡የአገር ፍቅር አለኝ ብሎ የሚምለው ይሔው የአማራ የፖለቲካ ሃይል ግራ ቀኝ ሳይል እነዚህን ነገሮች ከተቀበለና አውዳሚ በሆነ ጦርነት ውስጥ መሳተፉን ካመነ የአማራን ሕዝብ እንደ ኩርድ ከመበተን፣ኢትዮጵያንም በሰላምና በልማት እጦት ከመሰቃየት ያድናል፡፡ 

በዚህ ረገድ የአማራን ወካይ ሃይል ከሶስት ቦታዎች መፈለግ ይቻላል፡፡ 

1-በ1980ዎቹ ከኢሕዴንነት ወደ ብአዴንነት ለመቀየርም ሆነ በ2010 ከብአዴንነት ወደ አዴፓነት ከዚያም ወደ ብልጽግና ለመገልበጥ የማይቸገሩት የገዥው ፓርቲ ፖለቲከኞች በቀጣዩ የኢትዮጵያ ሁኔታ ውስጥ እራሳቸውን ሊከስቱ ይችላሉ፡፡እነዚህ ሃይሎች ግን መርህ የለሽና ጥቅመኛ በመሆናቸው በዘላቂነት የአማራን ሕዝብ አጀንዳ ወክለው ሊደራደሩ አይችሉም የሚል ክርክር ሊነሳ ይችላል፡፡እንዲያም ሆኖ ድርጅቱ ኢሕዴን ሆኖም ወደ ብአዴን ሲቀየርም ሆነ ወደ አዴፓና ብልጽግና ሲሆን ሳይጥማቸው በመቅረታቸው፣አለያም የሚያነሱት ሀሳብ ተቃውሞ እየገጠመው ወይንም ተባርረው የወጡና ተንጠባጥበው  የቀሩ ብዙ ሰዎች እንደሚኖሩ ይገመታል፡፡ከዚህ ውስጥ የሚሰባሰበው ሃይል መርህ ተከል እና ሕዝባዊ ሆኖ የሚመጣ ከሆነ ልምድ ያለውና ከሌሎች የአገሪቱ ሃይሎች አብሮ በመስራት ተሞክሮ ያለው በመሆኑ ጠቃሚ ይሆናል፡፡ 

2-ሁለተኛው እድል በዚህ ጦርነት ውስጥ ድርጅቶቻቸው የተሳተፉም ቢሆኑ ይህንን ስህተታቸውን ገምግመው፣ቀጥተኛ ሚና የነበራቸውን ደግሞ በአገሪቱ ለሚመሰረተው ሕጋዊ ተጠያቂነት አሳልፈው ሰጥተው፣በትግራይ ላይ በድርጅታቸው ስም ለተፈጸመው ስህትት ይቅርታ ጠይቀው፣ ከመካከላቸው ቀናኢ የአማራ ሕዝብ ወካይና ለአገር አሳቢ ሃይል ሊያወጡ ይችላሉ፡፡ይህንን ለማድረግ ግን ወኔው የሚኖራቸው ሰዎች ያስፈልጋሉ፡፡በዚህ ዘርፍ ውስጥ ያሉት ሃይሎች ካላቸው መታበይ አንፃር ይህንን ያደርጉታል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ይህንን ካደረጉት ትልቅ ተግባር ሊሆን ይችላል፡፡ 

3-የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የአገሪቱ የግዛት አንድነት የሚያሳስበው፣በሁሉም የአገሪቱ አካባቢ የሚኖረው አማራ እጣፈንታ የሚያሳስበው፣የኢትዮጵያ አንድ ሆኖና ተከባብሮ መኖር በቀዳሚነት የሚጠቅመው በሁሉም የአገሪቱ ማዕዘናት የሚኖውን የአማራ ሕዝብ እንደሆነ የሚረዳ የፖለቲካ ሃይል ሊፈጠር ይችላል፡፡ በተለይም ከአማራ ሲቪክ ማሕበራት (በውጭም ሆነ በውስጥ) የሚመጡ ሃይሎች ለዚህ ጥሩ ተመራጭ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

በዚህ ዘርፍ ሥር የሚሰፍሩት አማራን ወካይ ሃይሎች ግዴታ ፖለቲከኛና አማራ ክልል ብቻ መኖር ላይጠበቅባቸው ይችላል፡፡በሲቪል ማሕበር የተደራጁና በሌሎች ክልሎችም የሚኖሩም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

ይህ ሃይል ግን በዋናነት ችግር የሚገጥመው ከራሱ ከአማራ ክልል የፖለቲካ ማሕበረሰብ ነው፡፡የአማራ ፖለቲካ ሃይሎች ድርጅቶቻቸውንና ፖለቲከኞቻቸውን ሕልውናና ስም በማጥፋት የተጠመዱ መሆናቸው፣የውስጥ ችግሮቻቸውን በሙሉ ውጫዊ በማድረግና በሌሎች በማላከክ ላይ የሚታወቁ መሆናቸው  እንዲህ ያለውን ሕዝባዊ ሃይል እንዳይፈጠር ሊያደርጉት ይችላሉ፡፡በዚህም ሕዝቡን ያለ ወኪል በማስቀረት በ1983 አጥተነዋል ከሚሉት ውክልናም የባሰ ተወካይነት ሊያሳጡት ይችላሉ፡፡ስለዚህ ይህ ሕዝባዊና የአገር ፍቅር ያለው ሃይል ይህንን የሥም ማጥፋት- chracter assasination- (ምናልባትም የሕይወት ማጥፋትም ጭምር) ዘመቻ የሚቋቋም መሆን ይገባዋል፡፡ 

አማራ ካልተወከለስ?

ስለ አማራ ውክልና ስንነጋገር አንድ ትልቅ ጥንቃቄ ይሻል፡፡አማራን ለመወከል የሚነሳ ሃይል በክልሉ ጠቅላላ ዞኖችም ቅቡል መሆን ይጠበቅበታል፡፡በአማራ ክልል ውስጥ አሁን ያለው ፀረ ተጋሩና ፀረ ኦሮሞ (ለፖለቲካ ትክክለኛነት ስንል ፀረ ሕወሓትና ፀረ ኦነግ ልንለው እንችላለን) አመለካከት የሸፈነው የሚመስል አውራጃዊነት አለ፡፡የሸዋ ሥነልቦናና የፖለቲካ አቋም ከጎንደር ጋር የሚገጥም አይደለም፡፡የጎጃምና የጎንደር ልዩነት፣ወሎ እና ጎንደር ወዘተ ያላቸው ፖለቲካዊም ታሪካዊም ሥረ መሠረት አብሮ የሚሄድ አይመስልም፡፡በአጭሩ እነዚህን ሁሉ አንድ የሚያደርጋቸው አማርኛ መናገራቸው ብቻ ነው ብሎ የሚያምን በአደባባይ ያልወጣ አስተሳሰብ አለ፡፡በታሪክም፣በባሕልም፣በሥነልቦናም፣…አንድነት የሌላቸው እነዚህ የፖለቲካ ሃይሎች የጋራ ወኪሎችን ለመምረጥ ሊቸገሩ ይችላሉ፡፡ከዚህ በተጨማሪም ከባሕርዳር እጅግ የራቀ ጂኦግራፊያዊ ቦታ ላይ ያሉት ሰሜን ሸዋና ሁለቱ ወሎዎች እንዲሁም ከሚሴ ኦሮሚያ ከዚህ በኋላ የባሕርዳር ውል በቃን ቢሉ የማይጠበቅ አይደለም፡፡

የአማራ ሕዝብን የሚወክሉ ድርጅቶች ምክንያታዊ በሆነ መንገድና ፍጥነት ካልተደራጁ ክልሉ ወደ ውስብስብ ችግር ውስጥ ሊገባ ይችላል፡፡በአንድ በኩል የአማራ ክልል ወደ ሌሎች ትንንሽ ክልሎች ሊከፋፈል ይችላል፡፡ለዚህ ደግሞ በክልሉ የፖለቲካ ሃይሎች ውስጥ ቀደም ብሎ የነበረው አውራጃዊነት (በተለይ ከሰኔ 15/2011 ወዲህ የተባባሰው) እና በጦርነቱ ወቅት ፈሪና ጀግና ተብሎ በአመራሩ የተወነጀለበት መንገድ (በተለይም ሸዋና ወሎ) እራሳቸውን ችለው ወደ ክልልነት ለማደግ፣ሁለቱ ጎጃሞችም በአንድ ክልላዊ አስተዳደር ውስጥ ለመጠቃለል ወዘተ ሊፈልጉ ይችላሉ፡፡አዲሱ አስተዳደር እንዲህ ያለ አደረጃጀት ካመጣ ቀጣዩ የአማራ ፖለቲከኞች ትግል ወደ ‹‹ክልላችንን መልሱልን-Bring Back Our Region›› ሊጠብ ይችላል፡፡ይህ ማለት የክልሉ ትግል ዓላማ የሚሆነው ለአሁኑ ክልል ተጨማሪ ግዛቶችን ከማማተር ተሰብስቦ (ወልቃይት፣ራያ፣መተከል፣ደራ፣ወዘተ ከማለት ወጥቶ) የአሁኑን ክልል እንደገና ለመፍጠር  መትጋት ይሆናል፡፡ 

በሌላ በኩል ደግሞ የአማራን ሕዝብ ፍትሐዊ ጥያቄዎች አንግቦ ከጎረቤቶቹ ጋር በሰላም ለመኖር፣በአገሪቱ ፖለቲካ ላይም ተሳትፎ ለማድረግ የሚመጣ ሃይል ከሌለ ክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች በመሸጉ ሽፍቶች መታመሱ ሊቀጥል ይችላል፡፡በተለይ ታጣቂነት እንደ ጀግንነት የሚቆጥርና   በኢንዱስትሪ አልባነቱ የሚታወቀው ጎንደር ዋና የሽፍታ ማዕከል ሊሆን ይችላል፡፡አንዳንድ የጎጃም አካባቢዎችም ተመሳሳይ ችግር ውስጥ ሊወድቁ ይችላሉ፡፡ 

ለዚህ የሽፍታነት ተግባር ባለፉት ሶስት ዓመታት ትልቅ መሰረት የተጣለ መስሏል፡፡በአንድ በኩል ፋኖ፣ልዩ ሃይልና ሚሊሺያ በሚሉ መደበኛና ኢመደበኛ አደረጃጀቶች ተፈጥረዋል፡፡እነዚህ አደረጃጀቶች ወደተደራጀ ሽፍትነት ሊያድጉ ይችላሉ፡፡በሌላ በኩል ደግሞ በክልሉ ሲካሄድ በነበረው ውጊያ ምክንያት እየተሸነፈ ይሸሽ የነበረው የመከላከያ ሠራዊትና የፌደራሉ መንግሥት የፀጥታ ሃይል ትጥቁን ለሕዝቡ በርካሽ በመሸጥ የክልሉን ታጣቂ ሃይል አብዝቶታል፡፡ይህ ደግሞ ለሥርዓት አልበኝነት ትልቅ ግብአት መሆኑ አይቀርም፡፡ ከዚያ በፊት ግን ወደ ውስጥ መመልከት፣ጥፋትንና ሽንፈትን ማመን፣የይቅርታ ልብ ማደርጀት፣ሕዝባዊ መሆንና የሠላም ሃይል መሆን የአማራን ሕዝብም ሆነ የራሳቸውን የልሂቃኑን ዘላቂ ጥቅም ያስከብራል፡፡