በ ቅድሚያ ንሰብኣዊ መሰላት / Human Rights First
በመቐለ ዩንቨርስቲ ተማሪዎች ላይ የተፈፀመ ድብደባ እና እስራት በተመለከተ ከቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች የወጣ አጭር ሪፖርት
መግብያ
ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች ኢትዮጵያ በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ቁጥር 1113/2011 መሠረት በኢፌዴሪ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በቁጥር 4118 በሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ደርጅት የተመዘገበና እውቅና ያገኘ ሲሆን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የዜጎች ሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ እየሠራ ይገኛል። የዚህ አካል የሆነው የመቐለ ዩንቨርስቲ ተማሪዎች ላይ የተፈፀመ የመብት ጥሰት ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች በተገኘ መረጃ መሠረት እንደሚከተለው አጭር ሪፖርት በማጠናቀር አቅርቧል።
የተማሪዎች ተቃውሞ መነሻ
መቐለ ዩንቨርስቲ የተለያዩ ግቢዎች ያሉት ሲሆን ይህ ሪፖርት የሚያተኩረው በመቐለ ዩንቨርስቲ አሪድ ግቢ እና ዓዲ ሓቂ ግቢ ብቻ ነው፡፡ ይህ ሪፖርት ለማጠናከር ተማሪዎች እና አስተማሪዎች በመጠየቅ ጉዳዩን አጣርተናል፡፡ በአሪድ ግቢ ሆነ ዓዲ ሓቂ ግቢ ቀደም ብሎ የምግብ ጥራት ችግር ስለነበር ተደጋጋሚ ጥያቄ በተማሪዎች ቀርቦ ችግሩ ይፈታል የሚል መልስ ከዩንቨርስቲው አመራር ይሰጥ ነበር፡፡ በተለይ በዓዲ ሓቂ ግቢ 3 (ሶስት) ተማሪዎች በትርፍ አንጀት ሕመም ምክንያት ቀዶ ጥገና ያደረጉ ሲሆን ተማሪዎቹ በዩንቨርስቲው ከሚቀርበው እንጀራ ጥራት ጋር የተያያዘ ነው በሚል እምነት ቅሬታ እንደነበራቸው ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ትምህርት ሚኒስቴር የተማሪዎች የቀን የምግብ በጀት ከ22 (ሀያ ሁለት ብር) ወደ 100 (አንድ መቶ ብር) ከፍ እንዲል ካደረገ በኃላ አዲስ የምግብ ዝርዝር ይወጣል ተብሎ ለተማሪዎች የተነገረ ሲሆን በቀን 14/04/2017 ዓ/ም በአዲሱ የምግብ ዝርዝር መሰረት በፊት ሁለት ዳቦ የነበረ የጥዋት ቁርስ ወደ አንድ ዳቦ ተቀንሶ ቀርቦላቸዋል፡፡ የአሪድ ግቢ ተማሪዎች በዚህ ቅሬታ ጥዋት 14/04/2017 ዓ/ም ተቃውሞ የጀመሩ ሲሆን የዓዲ ሓቂ ግቢ ተማሪዎች ደግሞ ምሳ ሰአት የቀረበ እንጀራ በአሻዋ የተሞላ ስለነበር ተቃውሞ እንደጀመሩ ተረድተናል፡፡
የዓዲ ሓቂ ግቢ ተማሪዎች ከተማሪ ተወካዮች ጋር የሚያገናኝ እና ቅሬታቸው የሚገልፁበት የተማሪዎች የቴሌግራም ቻናል ያላቸው ሲሆን ከምግብ ጋር ያላቸውን ተቃውሞ በተደጋጋሚ ያነሱ ተማሪዎች በቻነሉ አስተዳዳሪዎቸ ከቻነሉ እንደተሰረዙ ገልፀውልናል፡፡ በዚህም የተማሪ ተወካዮች የምግብ ብልሽት ከሚፈጥሩ የዩንቨርስቲው አመራር እና የምግብ ግብአቶች አቅራቢ ኢንተርፕራይዝ ጋር ግንኙነት አላቸው የሚል ጥርጥሬ እንዳደረባቸው ቃለ መጠይቅ ካደረግንላቸው ተማሪዎች ተረድተናል፡፡ የተማሪዎች ተወካይ ምርጫ ከተደረገ ከ4 ዓመት በላይ እንደሆነ፣ አብዛኞቹ ተመርቀው የወጡ ሲሆን አሁን በተወካይነት እያገለገሉ ያሉ ጥቂት ብቻ ናቸው፡፡ በሕገ ደንባቸው መሰረት የተማሪ ተወካዮች በየ 2 (ሁለት) ዓመት መመረጥ ስላለባቸው አዲስ ተወካዮች ለመምረጥ በተደጋጋሚ የጠየቁ ቢሆንም የዩንቨርስቲው አመራር ምርጫ ለማመቻቸት ፈቃደኛ እንዳልሆነ ሁሉም የጠየቅናቸው ተማሪዎች ገልፀውልናል፡፡
ተማሪዎቹ ወደፊት የሚከፍሉት የወጪ መጋራት ክፍያ ከፍ ያለ ሲሆን ምግቡ ግን የባሰ ሆኖ መቅረቡ መብታቸው ለማስከበር ተቃውሞ እንደወጡ 11 (አስራ አንዱ) ያነጋገርናቸው ተማሪዎች አረጋግጠውልናል፡፡ ተማሪዎቹ ተቃውሞ በማሰማታቸው ድብደባ ከደረሰባቸው በኃላ ከተመራጭ ተማሪ ተወካዮች ቁጥጥር ውጪ የሆነ የራሳቸው አማራጭ ቴሌግራም ቻናል በመክፈት ችግሮቻቸው መወያየት ሲጀምሩ አማራጭ ቻነሉ ከፈቱ የተባሉ ሁለት ተማሪዎች በቀን 15/04/2017 ዓ/ም ከሰአት በኃላ በክልል ፀጥታ አካላት ታስረዋል፡፡ ሌላ አንድ ተማሪ ደግሞ ለማሰር እየፈለጉት እንደነበር ተረድናል፡፡
የተፈፀመው ድብደባ እና እስራት
በመቐለ ዩንቨርስቲ ዓዲ ሓቂ ግቢ
በዚህ ግቢ በቀን 14/04/2017 ዓ/ም ምሳ ሰአት አከባቢ ተቃውሞ የተነሳ ሲሆን ተማሪዎቹ ውጪ ወጥተው ለመቃወም ከግቢ ውጪ ሊወጡ ሲሉ በአከባቢው ያልነበሩ አዲስ የትግራይ የፀጥታ አካላት ተጠርተው ከግቢ ውጪ የዩንቨርሰቲው ዙርያ ከበው ነበር፡፡ ተማሪዎቹ ጥያቄያቸው የምግብ ጥራት ጥያቄ እንደሆነ፣ ለዩንቨርስቲው አመራር በተደጋጋሚ ጠይቀን መልስ ስላጣን ውጪ ወጥተው መቃወም እንደሚፈልጉ፣ ሚድያዎች መግባት እንዳለባቸው ሲጠይቁ ውጪ መውጣት ሆነ ሚድያዎች ማስገባት እንደማይፈቀድ ስለነገሩዋቸው ተመልሰው ግቢ ውስጥ ድምፃቸው ሲያሰሙ ውለዋል፡፡ የተቃውሞ ድምፁ በንብረት ሆነ በሰው ላይ ጉዳት እንዳይደርስ በኃላፊነት ስሜት የተደረገ እንደሆነና ምንም ዓይነት የንብረት ሆነ የሰው ጉዳት እንዳልደረሰ አጣርተናል፡፡ ሆኖም ግን ተማሪዎቹ ድምፃቸው እያሰሙ እያለ ከቀኑ 10፡30 አከባቢ ከግቢ ውጪ የነበሩ የትግራይ የፀጥታ አካላት (አድማ ብተና) ወደ ግቢው በመግባት ከፊታቸው ላገኙት ሰው ሁሉ በዘፈቀደ ከፍተኛ የሆነ ድብደባ ማድረስ ጀምረዋል፡፡ ወደ ተማሪዎች መኝታ ክፍል በመሄድ በር በመስበር ጭምር በመኝታ ክፍላቸው ለነበሩ ተማሪዎች እየደበደቡ ወደ አንድ መሰብሰቢያ ቦታ እንዲሰበሰቡ አድርገዋል፡፡ የሴት ተማሪዎች በወንድ ፖሊሶች ከመኝታ ክፍላቸው እየተደበደቡ ወደ መሰብሰቢያ ቦታው ተወስደዋል፡፡ በስብሰባ ቦታው የዩንቨርስቲው ምክትል ፕረዚዳንት ተኸስተ (ዶር) የተባሉ እንደተገኙና ጥያቄ እንዲያቀርቡ ሲፈቀድላቸው የፀጥታ አካላት ከምግብ ብልሽት ውጪ ሌላ ጥያቄ እንደማይቻል በመግለፅ ተማሪዎቹ ሲጠይቁ በመኃል እያቋረጡዋቸው ስለነበር በዚህ ሁኔታ መጠየቅ አንችልም በማለት ዝምታ እንደመረጡ ነግረውናል፡፡ በተለይ በተሰብሳቢ ተማሪዎች ፊት አንድ ሲቪል የለበሰ፣ የፊት ጭምብል (ማስክ) እና መነፅር ያደረገ ማንነቱ የማይታወቅ ሰው ተማሪዎች በነፃ ሐሳባቸው እንዳይገልፁ ይከለክል እና ያስፈራራ እንደነበር የዓይን እማኞች ገልፀውልናል፡፡
አንድ የዓይን ምስክር እንደገለፀልን ኣብርሃ (ሰም የተቀየረ) የተባለ የ5ኛ ዓመት የሕግ ተማሪ ሲሆን የሕግ ተማሪዎች ተወካይ ነው፡፡ በመንገድ ሲሄድ ከውጪ በብዛት የገቡ ፖሊሶች አግኝተውት ጥያቄአቸው የምግብ ጥያቄ እንደሆነ፣ ይህ ደግሞ የፍትሕ ጥያቄ እንደሆነ ፊት ለፊት ሲነግራቸው ጭካኔ በተሞላበት ደብድበው በደም እንደነከሩት፣ ወደ ቆሻሻ ውሃ ማስወገጃ ቱቦ በመጣል ሁኔታው እስኪረጋጋ እንዳቆዩት ፣ ሁኔታው ከተረጋጋ በኃላ አንስተው ወደ ክፍት ፓትሮል መኪና በመወርወር ይዘውት እንደሄዱ ነግረውናል፡፡
የ3ኛ ዓመት ተማሪ የሆነ ያሬድ (ስሙ የተቀየረ) በትግራይ ጦርነት ጊዜ ጉዳት ደርሶበት እግሩ ላይ ጉዳት እንዳለበት በመግለፅ ዶርም ውስጥ ተኝተን እያለ ድንገት ከውጪ የገቡ ፖሊሶች በሩን ከፍተው በመግባት ቀጥታ በመላ አካላታቸው ላይ በጭፍን ድብደባ እንደጀመሩ ፣ በመላ አካላቱ በተለይም ጉዳት በደረሰበት እግሩ ከፍተኛ የሆነ ድብደባ እንዳደረሱበት፣ ጉዳተኛ እንደሆነ ለመናገር እንኳ ዕድል እንዳልሰጡት በመጥቀስ በሁኔታው እጅግ እንደተጎዳ በሐዘን ስሜት ገልፆልናል፡፡ በአጠቃላይ ድበደባው በዘፈቀደ እና ከፍተኛ እንደነበር፣ ተማሪዎቹን የማሰቃየትና ርህራሄ የጎደለው የጥላቻ የሚመስል ድርጊት እንደነበር በመግለፅ ስሜቱን አጋርቶናል፡፡ ቁጥሩ በትክክል ባይገለፅም በመቶዎች የሚገመቱ ተማሪዎች እንደየ ክብደቱ እንደተደበደቡ ተረድተናል፡፡
በዚህ ሂደት 14 (አስራ አራት) ተማሪዎች መታሰራቸው ያጣራን ሲሆን የታሰሩበት ቦታም ዓዲ ሓቂ ክ/ከተማ ፖሊስ ጣብያ መሆኑን ተገንዝበናል፡፡ የታሰሩት ተማሪዎች ቤተሰብ ሆነ ሌላ ጠያቂ እንደማያገኛቸው፣ ከታሰሩት ውስጥ ከፍተኛ ድብደባ የደረሰባቸው ስላሉ ሕክምና ማግኘታቸውና አለማግኘታቸው እንደማይታወቅ ተረድተናል፡፡ ዛሬ ቀን 16/04/2017 ዓ/ም ከሰአት በኃላ የተለቀቁ ተማሪዎች ያሉ ሲሆን ገና ያልተለቀቁ ተማሪዎችም እንዳሉ፣ ፍ/ቤት መቅረባቸውና አለመቅረባቸው እንደማይታወቅ ተረድተናል፡፡
በመቐለ ዩንቨርስቲ አሪድ ግቢ
በዚህ ግቢ የተነሳ ተቃውሞ ተማሪዎቹ በዩንቨርስቲው አዲስ የተሰራ ካፊቴሪያ መጠነኛ ጉዳት ያደረሱ ሲሆን የሻይ ኩባያ ወደ ምግብ አቅራቢ ሰራተኞች የወረወሩ መሆኑን የጠየቅናቸው የዓይን ምስክሮች አስረድተውናል፡፡ ከኩባያ መወርወርና ስድብ በተጨማሪ በምግብ አቅራቢ ሰራተኞች ላይ የደረሰ የአካል ጥቃት ካለ ለማጣራት ጥረት አድርገን አካላዊ ጥቃት የደረሰበት አላገኘንም ፡፡
በተማሪዎች በኩል ወደ ግቢው የገቡ የትግራይ ፀጥታ አካላት ቁጥጥር እያደረጉ የነበረ ሲሆን በሁለት ተማሪዎች ላይ የድብደባ ጉዳት አድርሰዋል፡፡ ከዚህ ውጪ ያደረሱት ጥቃት እንደሌለ እና በአቀራረባቸውም የተማሪዎች ክብር የሚነካ ንግግሮች ወይም ዛቻና ማስፈራሪያ እንዳላዩ የጠየቅናቸው ምስክሮች አስረድተውናል፡፡
የተፈፀሙ የሕግ እና መብቶች ጥሰቶች
1. በኢፌዲሪ ሕገ መንግስት ዓንቀፅ 16 መሰረት የተደነገገውን ማንኛውም ሰው በአካሉ ላይ ጉዳት እንዳይደርስበት የመጠበቅ መብት አለው የሚል እና፣
2. በኢፌዴሪ ሕገ መንግስት አንቀፅ 18 (1) መሰረት ማንኛውም ሰው ጭካኔ ከተሞላበት ድብደባ፣ አያያዝ ወይም ቅጣት መጠበቅ አለበት የሚሉ ሕገ መንግስታዊ ጥበቃዎች ተጥሰዋል፡፡
3. የኢፌዴሪ ሕገ መንግስት አንቀፅ 30 የተደነገገውን የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነፃነትና አቤቱታ የማቅረብ ሕገ መንግስታዊ የመብት ጥበቃ ተጥሷል፡፡
በመንግስት ሊወሰዱ የሚገቡ የመፍትሄ እርምጃዎች
1. የትግራይ ክልል ፍትሕ ቢሮ ይህንን መሰረታዊ በሕገ መንግስት እና በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ስምምነቶች የተደነገጉ መብቶች በመጣስ ከፍተኛ ድብደባ እና ማሰቃየት ያደረሱ የፀጥታ አካላት ፣ ትእዛዝ የሰጡ እና ወደ ግቢው እንዲገቡ የፈቀዱ አካላት በሕግ እንዲጠየቁ ምርመራ እንዲያስጀምር እንማፀናለን
2. የትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር ይህንን ጥሰት የፈፀሙ አካላት በሕግ እንዲጠየቁ ድጋፍ እንዲሰጥና ፣ ማጣራት በማድረግ አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲወስድ እንጠይቃለን
3. የፈዴራል መንግስት በተለይ ደግሞ የኢፌዲሪ ትምህርት ሚኒስቴር የትግራይ የፀጥታ አካላት ለምን ወደ ዩንቨርስቲው ግቢ እንደገቡ፣ ማን እንዲገቡ እንደፈቀደላቸውና በተማሪዎቹ የደረሰው ጉዳት በማጣራት ይህንን ሕገ መንግስታዊ መብት ጥሰት በተማሪዎች ላይ እንዲፈፀም የፈቀዱ የዩንቨርስቲው አመራር በመለየት ተጠያቂ እንዲያደርግ እንማፀናለን፡፡
4. የዩንቨርስቲው አመራር ተማሪዎቹ ንፁህ ምግብ የማግኘት መብታቸው እንዲያስከብር፣ ተማሪዎቹ በሕገ ደንቡ መሰረት ተወካዮቻቸው እንዲመርጡ በማድረግ መብታቸው እንዲያስከብር እንጠይቃለን፡፡
ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች
Human Rights First
ታሕሳስ 17 ቀን 2017 ዓ.ም