እንዴት ኣንታገል?

ፀሃፊ ፦ ተኸስተ ረዘነ | ተርጓሚ ፦ ወዲ ሓላል

ይህ ፅሑፍ የትግራይ የህልውና ትግል ልሳን ሆኖ ከሚያዝያ ወር 2013 ዓ.ም ጀምሮ መታተም ከጀመረው “ረመፅ” የተሰኘ የትግርኛ መፅሄት ተወስዶ የተተረጎመ ነው። የፀሃፊው ዋና ይዘትና መንፈስ ሳይቀየር ለመተርጎም የተሞከረ ሲሆን መዝጊያው ላይ ግን ለኣማርኛ ኣድማጮች ተጨማሪ ሃሳብ ለመስጠት ያክል በተርጓሚው የተወሰነ ሃሳብ ተጨምሮበታል። በዚህ ኣጋጣሚ ግን ፀሃፊውን ኣግኝተን ልናስፈቅደው ስላልቻልን ፀሃፊውን ባለህበት ይቅርታችን ይድረስህ ለማለት እንወዳለን።

እኛ ተጋሩ እንዴት ኣንታገል?

የትግራይ ህዝብ በረጅም የታሪክ ዘመኑ ኣያሌ ከባባድ ችግሮችን ኣልፏል። ለኣጭርና ለረጅም ጊዜ ያጋጠሙት ችግሮችም እንደየ ኣመጣጣቸው ፊት ለፊት ተጋፍጦ ታግልዋቸዋል። በየጊዜው ብዙ መሰዋእት ከፍሎም እነዛ ፈታኝ ጊዚያትን ኣልፎ ህልውናውን ኣረጋግጧል። እነዛ የማይታለፉ ይመስሉ የነበሩት ፈታኝ ጊዚያትን ኣልፎ፣ የማይሸነፉ ይመስሉ የነበሩት ጠላቶችንም ሰባብሮ በማሸንፍ ህልውናውን ኣስቀጥሏል። ዛሬም እንዳለመታደል ሆኖ ታሪካዊና ኣዳዲስ ጠላቶቹ ከያሉበት ተጠራርተው ስለወረሩት ህዝባችን በጠመንጃ ኣፈሙዝ እየተፋለመ ይገኛል።

ጥሩነቱ ግን የትግራይ ህዝብ ለመብቱና ለክብሩ ሲል እንዴት መታገልና ማሸንፍ እንዳለበት ጠንቅቆ የሚያውቅ ህዝብ ነው። የማታ ማታ ድሉ የኛና የኛ ብቻ መሆኑም ታሪካችን ህያው ምስክር ነው። እየታገልን ያለነው ጦርነት ስለምንወድ ኣይደለም፣ እየታገልን ያለነው ጦርነት ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳትና ምስቅልቅል ስለማናውቅም ከቶ ኣይደለም። ምናልባትም ከኛ በላይ የጦርነትን ኣስከፊነትና ጠባሳ የሚያውቅ የለም ብንል ማጋነን ኣይሆንም። ጦርነት ብደንብ ስለምናውቅም ነው ጠላቶቻችን ጦር ሰብቀው በስሜት ይዋጣልን እያሉ ነጋ ጠባ ሲተነኩሱን እንኳን ስለ ሰላም ስንል ከልክ ያለፈ ትእግስት ያሳየነው።

በስተመጨረሻ ግን በኣንድ በኩል ራስን በራስ የማስተዳደር መብታችንን ነፍጎ፣ በውድ የልጆቻችን ደምና መስዋእትነት ያረጋገጥነው ብሄራዊ ነፃነታችንን ደፍጥጦ፣ ታግለን ወደ ጣልነው ፋሺስት ደርጋዊ ስርኣት ሊመልሰን የሚመኝ የ4 ኪሎው ቡድን፤ በሌላ በኩል ደግሞ የዴሞክራሲና የልማት ሽታ የማያውቅ ኣምባገነን ኢሳይያስ ኣፈወርቂ ያቆመው ሽፍታ የኤርትራው ስርዓት፣ እንዲሁም የግዛት ማስፋፋት ቆሌ የተጠናወተው ትምክህተኛውና ተስፋፊው የኣማራ ሃይል በጋራ ተቀናጅተው ጦርነት ኣውጀውብናል። እነዚህ ሦስት ሃይሎች በትግራይ ህዝብ ላይ ካላቸው ጥላቻ ውጪ የሚያስማማቸው ፖለቲካዊ ዓላማና ኣንድነት የላቸውም።

ዋና ግባቸውም የትግራይ ህዝብን ማምበርከክና ከዓለም ካርታ ፍቆ ማጥፋት ነው። እንደዚህ ዓይነት የዘር ማጥፋት ጦርነት ከታወጀበት በኃላ ነው እንግዲህ የትግራይ ህዝብ ተገፍቶ የትጥቅ ትግል ለማካሄድ የተገደደው። ለምንድነው የምትታገሉት የሚል ጠያቂ ካለም የምንታገልበት ብዙ ሺ ምክንያቶች እንዳሉን ወዳጅም ጠላትም እንዲያውቅልን እንፈልጋለን። ከነዚህ ምክንያቶችም፦

ታዲያ ለህልውናችን ስንል እኛ ተጋሩ እንዴት ኣንታገል?

የጦርነቱ ዋና ዓላማና ጦርነቱን ያወጁብን ሃይሎች ፍላጎት የትግራይን ህዝብ እንደ ህዝብ ማጥፋት ነው። ወራሪዎቹ ሀሴት የሚያደርጉት መጀመሪያ ኣንገታችንን ደፍተን ስንሸማቀቅ ሲሆን የዘላለም ዕረፍት የሚያገኙት ግን በመቃብራችን ላይ ነው። ዕድሜና ፆታ ሳይለዩ በህዝባችን ላይ ማቆሚያ የሌለው ግፍና ግድያ እየፈፀሙ ያሉትም ለዚህ ነው። እነዚህ ወራሪዎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ግፍና የጅምላ ግድያ እየፈፀሙ ያሉት ሆን ብለው፣ ኣስበውና ኣቅደው ነው። ይህ የወራሪዎቻችን የጭካኔ ባህሪም እኛ ብቻ ሳንሆን መላው ዓለምም ኣውቆታል፤ የታወጀብን ጦርነት የዘር ማጥፋት ጦርነት መሆኑን ኣምኖም እያወገዘው ይገኛል። ለዚህም ነው እየታገልን ያለነው ለህልውናችን ስንል ነው የምንለው። ኣዎ! እንደ ህዝብ ላለመጥፋት፣ እንደ ህዝብ ላለመነቀል፣ ለህልውናችን ስንል የምናደርገው ገድል ነው።

ለነፃነታችንና ለራስ ኣስተዳደራችን ስንልስ እኛ ተጋሩ እንዴት ኣንታገል?

እኛ ተጋሩ ነፃነታችንና ራስን በራስ የማስተዳደር መብታችንን በትግላችን ያረጋገጥን ህዝብ ነን። ትናንት ብዙ ሺ የህዝብ ልጅ የሆኑ ተጋሩ ኣባትና እናቶቻችንን፣ ወንድምና እህቶቻችንን የሰዋነው፣ ለሁለት ኣስርት ዓመታት ያህል ጊዜ በየወንዙና በየገደሉ የተንከራተትነው፣ የተራብነውና የታረዝነው፣ በየተራራውና በየሜዳው የቆሰልነውና የሞትነው ለነፃነታችንና ለራስ ኣስተዳደር መብታችን ስንል ነው።

እኛ ተጋሩ ያሻውን የሚያደርግ ፈላጭ ቆራጭ እንዲኖር የማንሻ፣ ከማንም በታች ሆነን መኖር ፍፁም የማንፈልግ ህዝብ ነን። ይሁን እንጂ ጠላቶቻችን ትናንት በትግላችን መንጭቀን የጣልነውና የሰባበርነውን የጭቆና ቀንበር መልሰው በጫንቃችን ላይ ሊጭኑ ሞክረዋል። የራስ ኣስተዳደር መብታችንን ነፍገው የትግራይን ታሪክና ስልጣኔ በማያውቁ ውዳቂ ምስለኔዎቻቸው ሊያስተዳድሩን፣ ህጋዊ መንግስታችንንም ሊያፈርሱብን ወስነዋል። መሰረታዊ የዴሞክራሲያዊ መብት መገለጫ ከሆኑት ተግባሮች ኣንዱ የሆነውን ምርጫ ማድረጋችን እንደ ሀጥያት ተቆጥሮብን ምርጫ የማያውቁ ወራሪዎቻችን እኛን ለመውረር እንደ ምክንያት ተጠቀሙበት። እኛም ለነፃነታችንና ለራስ ኣስተዳደር መብታችን ስንል እየታገልን፣ ውድ ዋጋም እየከፈልን እንገኛለን። ኣዎ ለነፃነታችንና ለራስ ኣስተዳደር መብታችን ስንል! ከፈጣሪያችንና ከራሳችን ሌላ በዚህ ምድር ማንም ጌታ እንዳያዘን ስንል!  

ለኣባቶቻችን የግዛት ክብር ስንል እኛ ተጋሩ እንዴት ኣንታገል?

ትግራዋይ መሬቱንና ‘የኣባቶቻችን ኣገር’ ብሎ የሚገልፃትን ትግራይ እንደ ኣይኑ ብሌን ነው የሚጠብቃት። ግዛቱንና መሬቱን ከጥንት ከጥዋቱ ጠንቅቆ የሚውቅ የትግራይ ህዝብ በኣሁኑ ጊዜ ግዛቱ በተስፋፊ ትምክህተኞች ተቆርሶ፣ ማሳውና ደኑ በወራሪዎች ተይዞና ተመንጥሮ፣ እህሉ ከቆፈውና ከኣውድማው በጠላቶች ተዘርፎ ቆሞ ማየት ኣይችልም። በምዕራብና ደቡብ ትግራይ ህዝባችን ከኣባቶቹ ግዛት ተነቀለ፣ ክብሩ ተገፈፈ፣ ከነሙሉ ሃብቱ ቤት ኣልባ ሆነ፣ ኣርሶ ሌላውን የሚመግብ ኣርሶ ኣደራችን ለራሱ ተራበ። ተባብረው የቀሙት ግዛቱና ክብሩን ለማስመለስ፣ እስከ ወዲያኛውም የግዛቱ ሉዓላዊነት ሊያረጋግጥ ነው እንግዲህ ህዝባችን እየታገለ ያለው።

ታዲያ ትግላችን ፍትሀዊ ሆኖ እያለ እኛ ተጋሩ እንዴት ኣንታገል?

የትግራይ ህዝብ እያካሄደው ያለው ትግል ፍትሀዊ ነው። ተወረርን እንጂ ኣልወረርንም፣ ተበደልን እንጂ ኣልበደልንም፣ ከኛ በታች ሁኑ ኣሉን እንጂ እኛ ከናንተ በላይ እንሁን ኣላልንም፤ ልንልም ኣንችልም። ወራሪ ሀይሎች ግን መሬታችንን ወረው ህዝባችንን ኣዋረዱት። እኛም ወራሪዎችና ግፈኞችን እየታገልን ያለነው በመሬታችንና በሉዓላዊ ግዛታችን ሆነን ነው።

ሊያጠቃንና ሊያጠፋን የመጣውን ሀይል ነው ያለ ምህረት እየደመሰስን ያለነው እንጂ ያጠቃነው ህዝብ የለም። የነጠቁን መብታችንን ለማስመለስ ነው ጠመንጃ ያነሳነው እንጂ የሌሎችን መብት ኣልተጋፋንም። እንዲያውም የሌሎችም ህዝቦች መብት እንዲጠበቅ ከቁጥራችን በላይ የሆነ እጅግ ውድ መስዋእትነት ከፍለናል። ጥያቄያችን ፍትሀዊ ነው የምንለው የራሳችን ዕድል በራሳችን እንወስን፣ ራሳችን በራሳችን እናስተዳድር፣ የህዝባችንና የግዛታችን ሉዓላዊነትም እናስጠብቅ የሚል ስለሆነ ነው። ለዚህ ፍትሀዊ ጥያቄም ነው እየታገልን ያለነው።

ታሪካዊ ሃላፊነት እያለብን እኛ ተጋሩ እንዴት ኣንታገል?

ኣሁን ያለቿ ትግራይ በብዙ ተከታታይ ትውልዶች ደምና ኣጥንት የተገነባች ነች። ብዙ ዋጋ ስለተከፈለባትም እጅግ ውድ ነች፤ ትግራይ። እያንዳንዱ የትግራይ ትውልድ ታሪካዊ ሀላፊነቱ እየተወጣ ነው ያለፈው። በኣንድ በኩል ከዛ ሁሉ የወላጆቹ መሰዋእት በኃላ ያሁኑ ትውልድ ተመችቶት ሊኖርና የወላጆችን የመሰዋእት ፍሬ ሊያጣጥም ሲገባው ተመልሶ ወደ ትጥቅ ትግል መግባቱ እንዳለመታደል የሚቆጠር ነው። ይሁን እንጂ ተኝተውልን የማያውቁ ጠላቶች ገፍተው ገፋፍተው ኣሁን ወደ ምንገኝበት ሁኔታ ኣስገብተውን ወሳኝ በሚባል ታሪካዊ ምዕራፍ ላይ ነው ያለነው።

ኣሁን ያለው ብቸኛ ኣማራጭም እንደ ኣባቶቻችንና ኣያቶቻችን ታሪካዊ ሀላፊነታችንን መወጣት ብቻ ነው። የኣሉላ ታሪክ፣ የሓየሎም መስተንክር፣ የብርሽዋ ትዝታ፣ የመለስ መንገድ፣ የገብረመስቀል ፅናት፣ የሚዘርና ሌሎች ሚልዮን ተጋሩ የገድል ታሪክ በሚደገምበት እጅግ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ነው ያለነው። ስለሆነም ታሪክ ላሸከመን ኣደራና ሀላፊነት ስንል እንታገላለን።

መጪው ጊዚያችንን ብሩህ ለማድረግ ስንል እኛ ተጋሩ እንዴት ኣንታገል?

ከሁሉም በላይ ደግሞ መጪው ጊዚያችን ብሩህና ኣስተማማኝ ለማድረግ ነው የምንታገለው። ታሪክ ራሱን እየደገመ፣ ዞሮ ከሚመጣብን የጦርነትና የበደል ኣዙሪት ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ቋጭተን የትግራይ ቀጣይ ትውልዶች በሰላምና ብምቾት የሚኖሩባት ትግራይ ለመፍጠር ነው የምንታገለው።

የኢ/ያ ህዝቦች ሆይ እናንተስ ለምንድነው የምትታገሉት? ኦሮሞ፣ ኣገው፣ ዓፋር፣ ሶማሌ፣ ሲዳማ፣ ወላይታ፣ ስልጤ፣ ጋምቤላ፣ ጉሙዝ፣ ሀረሪ፣ ከምባታ፣ ሺናሻ፣ ኣኝዋክ ወዘተ ወደ ትግራይ መጥታችሁ ከንቱ ሞት የምትሞቱትስ ለየትኛው ዓላማ ነው? ለማንስ ጥቅም ነው? እኛ ተጋሩ ብንሞት ተሰዉ እንጂ ሞቱ ኣንባልም፤ እናንተ ብትሞቱ ግን የሞት ሞት ሞቱ እንጂ ተሰዉ የሚላቹ የለም፤ ምክንያቱም በታሪክ ወራሪ ሟች እንጂ ሰማእት ሆኖ ኣያውቅምና። እኛ ግን የተከፈለውን ያህል ዋጋ ይከፈል፣ የወሰደውን ያህል ጊዜም ይውሰድ እስከ መጨረሻው ደቂቃ ድረስ በምንችለው ሁሉ እንታገላለን። ወራሪዎቻችን  ወረራን እስካላቆሙ ድረስም እኛ እንታገላለን። ኣዎ በፅናት እንታገላለን። እንዴትስ ኣንታገል!

ጨረስኩ፤ ቸር እንሰንብት!!!

ትግላችን ኣጭርና መራራ ነው!
ትግራይ ታሸንፋለች!