ፍርደ ገምድሉ የኢትዮ-ፎረም ትንታኔ! ትግራይ፡ ለኢትዮጵያ የወንጌል ብርሃን እንደ ሰም ቀልጣ የእምነት ክርዋን ያስቀጠለች የኣቡነ ሰላማ ካሳቴ ብርሃን ቤት

በ ሳሙኤል ኪዳነ

ክፍል አንድ

ኢትዮ ፎረም የተባለ የዩቲብ ቻነል ሚዲያ “የትግራይ አባቶች ሕዝቡ ለሻቢያና የዐቢይ ጦር እንዳይገዛ አልገዘቱም” በሚል ርእስ ከኣድማጭ ተመልካች “ተላከልኝ” ያለውን ጦማር (ፅሑፍ) በንባብ ኣጋርታል። የዚኽ ጽሑፍ ዋና ኣላማ በጣብያው በኩል “በሕዝቦች መካከል ግጭት የማይፈጥር ገምቢ እና ለማሕበራዊ መቀራረብ ግብኣት የሚሆን የጣቢያችን ኤዲቶርያል ፖሊሲ የማይፃረር የትኛውንም ፅሑፍ ቢላክልን ለተከታታዮች በሚሆን መልኩ ኣጠናክረን እናቀርባለን” ባሉት መሠረት የተጻፈ ምላሽ ነው። መልካም ንባብ።

“ጦርነቱ የጀመረው ህወሓት ነው” ኣቡነ ጴጥሮስ

የፌደራል መንግስት ጥቅምት 24 2013 ዓ/ም ትግራይ ላይ ለሚያውጀው የተጠና የዘር ፍጅት ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን እንዲያስችለው፤ ኣንዲትም ነፍስ ከትግራይ ምድር ሾልካ ሳትወጣ ሁሉም ባለበት ጭጭ ይል ዘንድ የሱዳኑ ወታደራዊ ምክር ቤት መሪ የሆኑትን ጀነራል ኣል ቡርሃን አዲስ ኣበባ ድረስ በመጋበዝ ሱዳን በትግራይ በኩል ከኢትዮጵያ የሚያዋስንዋትን ድንበሮች እንድትዘጋ ተማጽነው እንደላክዋቸው በጀነራሉ በኩል በይፋ ተነግራል። ይኽ ነገር ከተነገረ ወዲኽ የኣደባባይ ሚስጥር ሆናል። ይኽንን ዕቅድ የቤተ መንግስቱ ባለሟል ከሆኑ የሰነባበቱ ኢትዮጵያዊው ራስ ፑቲን እንደፈለጉ የሚያሾሯትን የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ እና ሲኖዶሱ ኣያውቁትም ማለት ኣይቻልም። ቤተ ክህነትዋ በመዋቅራዊ ሰንሰልትዋ ኣልያም የክህነት ካባ ደርበው መንግስትን በማገልገል ላይ በሚገኙ ባለ ሁለት ምላስ “ጃንደረባዎችዋ” በኩል አገሪትዋን በሚመለከት የምታውቀው ጉዳይ እጅግ ጥቂት ነው። ከማታውቀው የምታውቀውን እንደሚበዛ ግልጽ ነው። እንግዲህ ይህንኑ የኣደባባይ ሚስጥር ከሆነ የቆየ ጉዳይን ነው ቤተ ክህነትዋ በጳጳሳቷ በኩል በአንድ እጃቸው መስቀል፣ ሌላኛው እጃቸው ደረታቸውን ላይ በማድረግ “ከመከላከያ ጎን ነኝ” ስትል ወደ መንግስታዊው የዘር ፍጅት ጦርነት በራሷ ፈቃድ ዘው ብላ የገባችው።

ቤተ ክህነትዋ ከመከላከያ ጎን ነኝ ከማለት ኣልፋ በትግራይ የሚገኙትን ኣብያተ እምነቶች በመድፍ፣ በኣውሮፕላን እና በድሮን ሲወድሙ፤ መነኮሳት ብራና እና ብእር በማገናኘት ለትውልድ እንዲሸጋገሩ የከተብዋቸው በመንፈሳዊም በቁሳዊም መመዘኛ ወደር የማይገኝላቸው ቅርሶች ሆን ተብለው የእሳት እራት ሲደረጉ ከቁብ ሳትቆጥር ኣሁንም ቤተ ክህነትዋ ከመከላከያ ጎን ነኝ ኣለች፤

የእምነቱ እትብት የተቀበረባትን የአክሱም ጽዮን ማርያም በዘመነ ግራኝ አህመድ የታየውን የምእመኖችዋ ሞት በእጥፎች የሚበልጥ ቁጥር ያላቸውን ዜጎች በጠራራ ፀሐይ ሲታረዱ ከመከላከያ ጎን ነኝ ከማለት ኣልፋ፣ የለም አክሱም ውስጥ የተገደሉ የሉም፣ 700፣ 800፣ 1000 ተገድሏል ተብሎ የተዘገበው ሃሰት ነው። የማቾች ቁጥር ከ20 ኣይበልጥም በማለት በንጹሃን ሞት ተመጻደቀች፤

ማርያም ድንግላትን ጨምሮ በርከት ባሉ የእምነት ቦታዎች ውስጥ የታረዱ ሰማእታት ልክ ቤተ መቅድስ ውስጥ እንደተገኘች ውሻ ደማቸው ደመ ከልብ ሆኖ እንዲፈስ እንዳላየች እንዳልሰማች ኣሁንም ከመከላከያ ጎን ነኝ ኣለች። ይህች ናት እነ ኣቡነ ጴጥሮስ በሃሳብም በገቢርም የሚመሯት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን።

የዚህች ቤተ ክህነት፣ የክህነት ካባ የለበሱ በዘርኝነት መንፈስ ህሊናቸው የታወሩ ጳጳሳት ከፊት ረድፍ በማስቀመጥ የምእመኑ ሙዳይ ለተቶኳሽ ጳጳሳትዋ እና ኤጲስ ቆጳሳቶችዋ እንደ ኣስቶካሽ በመሆን የትግራይ ህዝብ ለማጥፋት በታወጀው ጦርነት ተጋሩ የእምነቱ ተክታዮች ከቁብ ሳትቆጥር ከመከላከያ ጎን ነኝ በማለት በዘር ፍጅቱ ቀጥታ ተሳታፊ ሆና እስክ መጨረሻ ዘልቃለች። ይህንን ትክክል ኣይደለም ያሉትንም ሊሉ ይችላሉ የተባሉትንም ጭምር ድምፃቸውን በማፈን ተጉዛለች።

ያም ሆኖ ሁሉንም መሰናክል ኣልፈው ቅዱስ ፓትሪያርኩ May 8, 2021 Denis Wadley በተባለ የውጭ ዜጋ በኩል በእጅ ስልክ በተቀረጸ መልእክታቸው ታፍኛለሁኝ የሚል የድረሱልኝ መልእክታቸውን ማስተላለፍ ችለዋል። ብጽኡነታቸው በወቅቱ ባሰራጩት መልእክት ትግራይ ላይ የተቀናጀ ኣረሜናዊ የዘር ፍጅት እየተካሄደ መሆኑን ፣ ሆኖም ግን እሳቸው እንደ አንድ መንፈሳዊ ኣባት የዘር ፍጅቱ እንዲቆም ዘንድ የሚጠብቀባቸውን ሃላፊነት እንዳይወጡ ከመንግስት እስከ የሲኖዶስ ጽሕፈት ቤቱ ድረስ በተዘረጋ የተናበበ ነውረኛ ኣፋኝ መረብ ከመገናኛ ብዙሃን ጋር እንዳይገናኙ መከልከላቸው፤ ከዚያም ኣልፎ በቤተ ክርስትያንዋ የመገናኛ ቴሌቪዥን ጭምር ሃሳባቸውን እንዳይገልጹ መታፈናቸው ቃል በቃል ተናግረዋል።

ይኽንን የእሳቸውን ንግግር በመስማት ከሲኖዶስ ጽሕፈት ቤት እስከ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ድረስ በ የእርከኑ የሚገኙ ሃላፊዎች ቅዱስነታቸው የተናገሩትን ሃሳብ ቤተ ክህነትዋን የማይወክል የኣፍ እላፊ ቃላት በማለት ቅዱስነታቸው የተናገሩትን ሃሳብ የእሳቸው የግላቸው ሃሳብ ብቻ መሆኑን በመገናኛ ብዙሃን ጭምር በመውጣት ገለጹ። ብጽኡነታቸውን የሚገባቸው ክብር በሃይል ገፍዋቸዋል፣ አንገታቸውን እንዲድፉ በመጽሐፉም በቃልም ክፉ የሚባሉ ቃላት በቅዱስነታቸው ላይ ኣዘነቡላቸው።

ቅዱስነታቸውን የትግራይ ህዝብ ከፍ ሲል መንፈሳዊ ኣባትነታቸውን ዝቅ ሲል ሰብኣዊነታቸውን ኣይቶ ላቅ ባለ መንፈሳዊ ክብር በስስት ቢያይዋችውም በኣንጻሩ ከእሳቸው ኣጠገብ ያሉ ጳጳሳት ቅዱስነታቸው እውነታውን በመናገራቸው ብሄርተኛ፣ ሰለ ትግራይ ሲናግሩ ኣፈርንባቸው፣ ጁንታ፣ ወዘተ በሚሉ ከመንፈሳዊ ሂወት ረዥም እርምጃዎች ርቀው በሚኖሩ ሰዎቸ ኣንደበት የማይጠፉ መርዘኛ ተቀጥያዎች የስድብ እና የዛቻ ዶፍ በዶቦ ኣወረዱባቸው። ይኽ ድርጊት ግር የሚያሰኝ ኣይደለም፣ ምኽንያቱም ግልጽ ነው ቤተ ክህነትዋ እውነትን በኣፍ ጢምዋ ደፍተው ለጥፋት በተንሱ መሪዎች ስር ወድቃ ከሀገር መከላከያ ጎን ነኝ ማለትዋን ተያይዛው ኣለች!

በኣሁኑ ወቅት ቤተ ክህነትዋ በማን እጅ ስር እንዳለች ለማወቅ ብዙም ኣይከብድም። ሁሉም የዕለት ተዕለት ሰራዋ ገላጭ ነው። ይኽ እንዲህ ሆና እያለ ኢትዮ ፎረም ከኣድማጭ ተመልካች የመጣልኝን ብሎ ያስተላለፈው መልእከት በይዝትም በትርክትም የተዛባ ብቻ ሳይሆን የቤተ ክህነትዋ ከመከላከያ ጎን ነኝ የሚለውን ገዢ እሳቤ የሚያስቀጥል ጦማር ነው። ለዚህም ቅንነት የጎደለው መታረም ያለበት ሃሳብ ነው የሚል እምነት ኣለኝ።

ቤተ ክህነት እና ጦርነት

በኢትዮጵያ ረጅሙ የቤተ ክህነት እና የቤተ መንግስት የወዳጅነት ታሪክ ጥምረቱ ከወዳጅነት አልፎ እስክ ጣምራ አገዛዝ ድረስ የሄደበት አጋጣሚ በጣም ረጅምና ብዙ ነው። ቤተ መንግስትና ቤተ ክህነት በአንድ ሳምባ እየተነፈሱ መንግስታዊም መንፈሳዊም ጉዳዮች በጋራ እየመሩ ተጉዘዋል። ወዳጅነቱ ልቆ ነግስታት ለቤተ ክህነትዋ በዋሉት ውለታ ቤተ ክህነትዋ አንድ አንድ ነገስታት ጻድቅ ብላ እስከ መሰየም ደርሳለች። በሌላ መልኩ ቤተ ክህነትዋ መንፈሳዊም አስተዳደራዊም ስራቸው ያጋደሉ ነገስታት ታግላም ኣታግላም ገርስሳለች። በዚህ ታሪካዊ ፍጻሜ ላይ መከራከር ትርፉ ጉንጭ ማልፋት ነው የሚሆነው። ሆኖም ግን ኢትዮ ፎረም በኣድማጭ ተመልካች የተላከልኝ ጦማር ብሎ ለታዳሚዎቹ ባነበበው ጽሑፍ ቤተ ከህነት እና መንግስት የነበራቸውን ጥምረት የዘገበበት መንገድ መሰረታዊ የታሪክ መጣረሶች እና ጥሰቶች ያሉበት ጦማር ነው።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን በታሪክዋ እንኳን እያወቀች ተሳስታም በራስዋ ዜጎች ኣልያም ኣማንያን ላይ በውጭ ወራሪ ሃይል የተቃጣ ወረራ ደግፋ አታውቅም። አገሪትዋ ከቱርክ እስከ በኢጣልያ መንግስት ድረስ ያጋጠምዋትን የውጭ ወራሪ ሃይል ጦርነቶች ወራሪዎችን ለመመከት ባደረገቻቸው ጦርነቶች ይኽንን ክስተት ፈጽሞ ኣላጋጠማትም። የጦማሩ ጸሓፊ ሊናገሩት ያልፈቀዱት እውነታ ሌላ ነው።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን በተላያየ ወቅት ያጋጠማት በስነ-መለኮት ላይ ያተኮሩ ልዩነቶች ኣካባቢያዊ ብሎም የተውሰኑትን ደግሞ ሓሳቡ የፈለቀበት አልያም የሚንሸራሸርበት ኣድባራት ድጋፍ ይቸራቸው ነበር። ከዚህ ባለፈም በ የኣከባቢው የነበሩ ባላባቶቸ (መሪዎች) ወታደርዊ ድጋፍ ያደርጉላቸው ነበር። ክርክሩ ተለጥጦ ወደ የሃይል ግጭት ሲሸጋገርም የአከባቢው መሪዎችና ህዝቦች በመተባበር ለሚያምኑበት የስነ-መለኮት ትምህርት ይዋጉም ይሞቱለትም ነበር። ይኽ ኣጼ ዮሃንስ ቦሩ ሜዳ ላይ ተዋህዶ የቤተ ክርስትያንዋ የስነ-መለኮት ትምህርት ኣስኳል እንዲሆን እስካስ ወሰኑበት ድረስ የነበረ እውነታ ነው።

ይኽ ከመሆኑ በፊት ቋረኞቹ ሸዋን ወግተዋል፣ ጎጃምም ከቋራም ከሸዋ ተዳምቷል፣ በተመሳሳይ ትግራይ ከጎጃምም ከሽዋም ተዋግተዋል። ይኽ እወነት ነው። ነገር ግን ይኽ ለተሳሳተ እና ፖለቲካዊ አንደምታ ላለው ትርክት ማዋል ቅጥፈት ነው። ምክንያቱም ዛሬን ትላንትን በምታይበት መነጽር ለማየት ስትሞክር የተዛባ ምስል ስለሚሰጥ ትክክለኛ ሰዕል ኣያሳይም።

የጦማሪው ትልቁ ስህተት ዛሬ (ከጥቅምት 24/2013 ዓ/ም) ጀምሮ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ከርስትያን ከመከላከያ ጎን እቆማሎሁኝ ብላ ያስጨፈጨፈቻቸው ተጋሩ በምንም መለኪያ ቤተ ክህነት ከመንግስት ጋር በነበራት ቀደምት ጣምራ ያልተደረገ ወንጀል ነው።

ቤተ ከህነትዋ ኣድባራትዋ ሲቃጠሉ፣ ኣማኞችዋ ሲታርዱ፣ ከቀያቸው ሲፈናቀሉ አጥፊው በህግ ባልተለየበት ሁኔታ እንዲኽ ያለ ኣቋም መያዝዋ፣ ተጋሩ የራሳችሁን ቤተ ክህነት ኣቃኑ ማለት መሆኑን ለማወቅ እንዴት ጳጳሳቶችዋ ለማወቅ ይከብዳቸዋል?

ይባሰ ብሎ ትግራይ በውጭ ወራሪ ሃይሎች ስትወረር፣ ዓላማቸው ምንድ ነው ገና ያልተለየ የሶማሊያ (ሞቃድሾ) ቅጥረኛ ወታደሮች፣ የኣረብ ኤሚሬት ሰው ኣልባ ድሮኖች ቤተ ክህነትና ኣማኞችን የእሳት ዶፍ ሲያዘንብባቸው ለተቋቋመችበት መንፈሳዊ ተልእኮ ከመቆም ይልቅ፣ ኣሁንም ከመከላከያ ጎን እቆማሎሁኝ ስትል በገዛ ፈቃድዋ የትግራይን ቤተ ክህነት ከውስጥ ጉዳይዋ ወደ የውጭ ጉዳይዋ እንደገፋቻት ማን በነግራት። የሆኖውም ይኽ ነው።

መንግስታዊ ሽብር

የደቂቀ እስቲፋኖስ እንቅስቃሴ መነሻም መዳረሻም የታወቁ ናቸው። የእንቅስቃሴው ጠንሳሾች እና መሪዎች ከትግራይ ቢሆኑም እንቅስቃሴው በያዘው የተቃና ትምህርት እና ይዘት ተከታዮቹ ከትግራይ ኣልፎ ኣሁን ትግራይ ካለችበት ኣከባቢ ሺ ኪሎሜትሮች ርቀው በሚገኙ የኢትዮጵያ ኣከባቢዎች ሊዳረስ ችላል።

ውድ ኣንባቢያን፣ በግብረ ሃዋርያት የሚያምን የትኛውን ኣካል ነው በምንፍቅና የሚከሰሰው? የፍትህ የበላይነት፣ የዜጎች እኩልነት፣ መሪዎች ከልክ ባለፍ ከሰዎች በላይ ከፈጣሪ እኩል ተድርግው የሚታዩበትን መንገድ ትክክል ኣይደለም ከፈጣሪ በላይ መሪ የለም ማለቱ ምኑን ነው መናፍቅነት?

መነኮሳት በመንፈስም በስጋም ይፀኑ ዘንድ ማሕበረሰቡን በቀለብና ስንቅ ኣቅረብልኝ የማያባራ ጉትጎታ እንዳያስቸግሩት ራሳቸውን እንደ ኣቅማቸው የሚችሉበትን ስራ ይሰሩ ዘንድ ማስተማሩ ምኑ ላይ ነው መናፍቅነት?

ኣማኞች ባልተገባ ከእምነቱ ኣስተምህሮዎች ውጭ በልማድ በተዋረድ የመጣ ኢ-ክርስትያናዊ ብሎም ኢ-ኦርቶዶክሳዊ የመስዋእት ተግባራት እንዳይፈጽሙ መከልከል ምኑን ነው መናፍቅነት?

በኢትዮ ፎረም በኩል የተነበበው ጦማር መልእክቱ ሌላ ነው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ዘመናዊ ትምህርት በተማሩ ኣማኞችዋ የሓሳብ አመንጪነትና ድጋፍ እንዲሁም የለየላቸው በፀረ ትግራይ ኣቋማቸው የሚታወቁ ሰዎች በፊውታራሪነት የሚመራ ማሕበረ ቅዱሳን በመባል የሚታወቅውን ማሕበር፣ ትግራይ ውስጥ የሚገኙ በደቂቀ እስቲፋኖስ የተገደሙ ገዳማት፣ ደብሮችና የገጠር አብያተ ክርስትያናት ባሉብት ቆሞው እንዲዝጉ፣ በዕድሜ ብዛት ያረጁትን ደግሞ በተፍጥሮኣዊ ሂድታችው እንዲማሙ ያስችል ዘንድ ጥገና እና እርዳታ ሲነፍጋቸው ቆይታል።

ለዚኽ እማኝ ምስክሮች ጉንዳጉንዶ፣ አሲራ መቲራ ወዘተ በዚህ ማሕበር ጥርስ ከተነከሰባቸው ሰንበት ያሉ ጥንታውያን ገዳማትና ኣብያተ ክርስትያናት ናቸው። ዳሩ ግን እነዚህ ቤተ እምነቶች መንፈሳዊም ቁሳዊም ፋይዳቸው ሳይለቁ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገሩ የትግራይ ህዝብ ትልቅ ውለታ ውላል። ምኽንያቱም እነኚህ ቅርሶች ተጋሩ ከቀድሞ ኣያቶቻችው በአደራ የተቀበልዋቸው መልሰውም ተንከባክበው በመያዝ ለሚቀጥለው ትውልድ የማስረከብ መንፈሳዊም ሞራላዊም ግዴታ ስላለባቸው ነው።

ታድያ ይኽንኑ ተግባሩ ምኑ ላይ ነው ምንፍቅና የሚያስብለው?

ከትግራይ ውጭ ያሉትን በርከት ያሉ ገዳማትና፣ ኣድባራት ቤተ ክርስትያኖች በሌሎች ህዝቦች እንዲሁ ተመሳሳይ እንክብካቤ እና ጥበቃ እየተደረገላችው እስከ አሁን ዘልቀው የለም እንዴ?

ሊተላለፍ የተፈለገው መልእክት ከመንፈሳዊ ይዘቱ ባለፈ ፖለቲካዊ ትርፉ ተሰልቶ ሆን ተብሎ በቀመር የተጻፈ ጦማር ነው። የሲኖዶሱ አባላት ራሳቸውን በዘርኣያ ቆብ ዙፋን ኣምሳያነት በ ብልጽግና መንግስት ወንበር በመቀመጥ የትግራይ የሃይማኖት ኣባቶችም በኣባ እስቲፋኖስ ወይም ደቂቀ እስቲፋኖስ ቦታ በማስቀመጥ የሲኖዶሱ ጳጳሳት (አብረሃም ወ ጴጥሮስ) ራሳቸው ኣልያም ኣስሰርገው ባስገብዋቸው ሰዎቻቸው በኩል የቀደምቱ የመንፈስ አባታቸው ኣጼ ዘርኣያቆብ ውርስ የሆነውን መንግስታዊ ሽብር እንዲፋፋምባቸው ማድረግ ነው።

ክፍል ሁለት፣ ይቀጥላል . . . !