ክፍል ሁለት፡ በኢትዮ-ፎረም ለቀረበ ኣሳሳች ትንታኔ የተሰጠ መልስ፣ ትግራይ ለኢትዮጵያ የወንጌል ብርሃን እንደ ሰም ቀልጣ የእምነት ክርዋን ያስቀጠለች የኣቡነ ሰላማ ካሳቴ ብርሃን ቤት!

በ ሳሚኤል ኪዳነ
ክፍል ሁለት

ኢትዮ ፎረም የተባለ የዩትዩብ ሚዲያ “የትግራይ አባቶች ሕዝቡ ለሻቢያና የዐቢይ ጦር እንዳይገዛ አልገዘቱም” በሚል ርእስ ከኣድማጭ ተመልካች የተላከለትን ጦማር በንባብ ኣጋርታል። የዚኽ ጽሑፍ ዋና ኣላማ በጣብያው በኩል “በሕዝቦች መካከል ግጭት የማይፈጥር ገምቢ እና ለማሕበራዊ መቀራረብ ግብኣት የሚሆን የጣቢያችን ኤዲቶርያል ፖሊሲ የማይፃረር የትኛውንም ፅሑፍ ቢላክልን ለተከታታዮች በሚሆን መልኩ ኣጠናክረን እናቀርባለን” ባሉት መሠረት የተጻፈ ምላሽ ነው። ትላንት ክፍል ኣንደ በዚህ ሚዲያ የቀረበ ሲሆን ዛሬ ደግሞ ክፍል ሁለት እንደሚከተለዉ ቀርቦላችኋል፣ መልካም ንባብ።

“ኣቡነ ማትያስ፡ የትግራይን ህመም አብረው የታመሙ አባት”

ጦማሪው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን በትግራይ ላይ የተፈፀመው የዘር ፍጅት ያየችበትን መንገድ በፍቃዳቸው በግላቸው ተንሳሽነት ለማቃናት አቡነ ማትያስን ከመንፈሳዊ ኣባትነታቸው ይልቅ ትግራዋይነታቸውን ይበልጥ እንደ ማደራደሪያ ነጥብ በማቅረብ ያቀረቡት ሃሳብ ኣደግኛነቱ የታያቸው አይመስለኝም። ቤተ ክህነትዋ ኢ-ክርስትያናዊ በሆነ የጥፋት ሃዲድ ውስጥ የገባችው ከወንጌል ይልቅ፣ የግል ፖለቲካዊ ፍላጎታቸውን በሚያራምዱ ጳጳሳት መመራትዋ መሆኑ የኣደባባይ ሚስጥር ነው።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን እስከ ሲኖዶስ ውስጥ ያሉ የበላይ አመራሮችዋ በግላጭ የኦሮሞ ቄስም ካህንም የለም የሚሉ የጵጵስና መአርግ የደፉ ጳጳሳት የሚነድዋት ፀረ ሌሎች ብሄሮች አይደለችንም? የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ትግራይን ገፍታ ከጥፋት ኣፋፍ ላይ አላደረሳቻትንም? ፣የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን በተለያየ ኣድባራት፣ የሰንበት ትምህርት ቤቶች ወዘተ፣ የነበሩ ተጋሩ ኣገልጋዮች መንግስታዊው ፍረጃ ተቀብላ ጁንታ እያለች አላሳደድቻቸውም ወይ?

አቡነ ማትያስን ከፊት በማሰቀመጥ ነውጠኞቹ በጵጵስና መአርግ የተደበቁ ባለ ጥቁር ልብስ ሰብኣ ጥቁር ልቦች ከሃላ ኣስከትላ ወደ ትግራይ የምትገባበት ዕድል በራስዋ ፈቃድ ተዝግታል። ይኽ ቀላል የማታለያ ዘዴ ከአንድ በሌላ ክፍለ አለም የሚገኙ ህዝቦች ታሪክ ተመሳሳይ ሆኖ ነው የምናገኝው።

ነገሩ እንዲህ ነው፣ ጥቅጥቅ ባለ በኣማዞንን ደን አቅራቢያ የሚኖሩ የብራዚል ባላባቶች እረኞቻቸው ከብቶቻቸውን ይዘው ከአንድ መስክ ወደ ሌላ መስክ የመኖርያ ቦታቸውን፣ አልያም በጊዝያዊነት የሚኖሩበትን ኣከባቢ መርጠው መሻገር የቆየ ልማዳቸው ነው። ወንዝ ሲሻገሩ የሚያስቸግራቸውን ፒረንያ የተባለ ዓሣ ሁልንም ከብቶቻችውን ጨርሶ እነርሱንም ጭምር እንዳይጨርሳቸው መጀመርያ ወንዙን እንድትሻገር የምትደረግ ኮስማና የመስዋእት ከብት ወደ ወንዙ ገፍተው ይካትዋታል።ፒረንያዎቹ ሚስኪንዋ የመስዋእት ከብት ላይ በደቦ ሲተሙ እረኞቹ ከብቶቹን ይዘው ፒረንያዎቹን ኣታልለው ወደ ፈለጉበት ቦታ በሰላም ይሻገራሉ።

የጦማሪው ብዕር የደፈቀው እውነታ የትግራይ ህዝብ ከውስጥም ከአገር ውጭም በላዩ ላይ በዘመቱበት ወራሪዎች ከመልኣከ ሞት ፊት ለፊት ብቻውን ሲጋፈጣቸው በመኖርና በሞት መሃከል በመጣጣር ላይ እያለ “ከመከላከያ ጎን እቆማሎሁኝ” ያለችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያንና የቅዱስ ሲኖዶስ አባሎቻችዋ የሞት ዳንኪራ ሲመቱ፤ ለብቻቸው ከትግራይ ህዝብ ጋር የቆሙትን ብጳኡነታቸውን እንደ መስዋእት በሬ የጥፋቶችዋ እና ሃጥያቶችዋ ስርየት የትግራይ ህዝብን ቁጣ ለማብረድ መጠቀም መሞከርዋ ኣሁንም መልእከቱ ሌላ ነው።


ቤተ ክህነትዋና ሲኖዶሱ እጃቸው በደም የተጨማለቀ የህሊናም የህግም እስረኞች ናቸው። ግፉ ግን በዚህ ኣላበቃም ነበር። ብጱእ አባታችን የትግራይን ህዝብ ግፍ ሲናገሩ ሲኖዶሱ በትብያ የግላቸው እንጂ የቤተክርስትያንዋ ኣቋም አይደለም እንዳላለን ፣ ፣አሁን ደርሶ ሃዘናቸውን ነጥቆ ተመልሶ በሃዘናቸው ትርፍ ለማግኘት ፣ ኣልያም ለይስሙላ በተጻፈ የ ይቅርታ ጦማር ሃጥያቱን ለማስተሰረይ መሞኮሩ በራሱ በመንፈሳዊ ቋንቋ ሃጥያት፣ በማሕበረሰባዊ ህገ ልቦናም ነውር ነው።

ጦማሪው የቄሳርን ለቄሳር ባሉበት ኣንደበት ለመጥቅስ ያልደፈሩት እውነታ የሲኖዶሱ ለሲኖዶስ የብጱእ አባታችን ለብጵኡነታቸው ብለው ለመፃፍ ለምን ወኒያቸው ከዳቸው?

እኔ ግን እላለሁኝ ብጳኡነታቸው ከትግራይ ህዝብ ጋር በጋራ ያዘኑት ሃዘን የብቻቸው እንጂ፣ ማንም የሲኖዶሱ አባል ሊጋራው የሚችል ኣለመሆኑን ነው። በታሪክም ለብቻው ቆሞ ሲወሳ የሚኖር፣ በመንፈሳዊ ሕግም በሕገ ልቦናም ደግ ኣባት ተብለው እንዲጠሩ የሚያስገድድ እውነታ ነው።

ለዚህም ነው ብጱእነታቸው ህመሙን አብረው ለተጋሩት፣ አብረውት ላለቀሱለት ህዝብ ከፕሪቶርያው ውል በኋላ መቐለ የመጡ ጊዜ፣ የትግራይ ብጱኣን ኣባቶቻችን የሚገባቸውን አባታዊም መንፈሳዊም አቀባበል አድርገው የተቀበልዋቸው። ምኽንያቱም ግልፅ ነው፣ አቡነ ማትያስ ወደ ትግራይ ጥቁር እንግዳ ሆኖው የሚገቡበት ምንም አይነት ምክንያት የላቸውም። ኣልነበራቸውም።

እዚህ ላይ ጦማሪው ምናልባትም ከቤተ ክህነት ኣካባቢ እንዳልሆነ በሚያሳብቅ መልኩ ሁለት ነጥቦች ኣንስቷል። የመጀመርያው ነጥብ፣ የአቡነ መርቆርዮስን “ትግራዋይነት” ከብጱእ አባታችን ትግራዋይነት ጋር በማነፃፀር ለብጱእ ኣባታችን የራራ የተጋሩ ልብ፣ ለምን በአቡነ መርቆርዮስ ብሎም በሌሎች ጳጳሳት ላይ ሲደርስ ደንደነ የሚል ሲሆን፤ ሁለተኛው ነጥብ ደግሞ፣ አቡነ መርቆርዮስን በብጱእነታቸው አይን ሚዛን አልያም ብጱእነታቸውን የሚታይበት ሚዛን ከአቡነ መርቆርዮስ ጋር እኩል መሆን አለባት ይሚል የጋለሞታ ፍርድ ነው። ጦማሪው እጅግ ተሳስቷል።

በትግራይ ህዝብ ላይ በደረሰው በደል አቡነ መርቆርዮስ “ትግሬ ገዳይ” እያለ ትግራይን ለማጥፋት የዘመተ የጥፋት ጦር በፊውተራሪነት ባርከው ከላኩ የሲኖዶሱ አባል ብቻ ሳይሆኑ በቤተ ክህነት ውስጥ መንፈሳዊ ጥንካርያቸው ሳይሆን ብሄራቸውን ተለይተው ተጋሩ እንዲጠቁ ያቀዱ፣ ያስተባበሩ፣ የመሩ ብሎም ያስፈፀሙ አይደሉም ወይ?

አቡነ መርቆርዮስ ሓምሌ 2004 ዓ/ም ኤርትራ ድረስ በመሄድ ከመንፈሳዊ አገልግሎታቸው ባለፈ ወታደራዊም ፖለቲካዊም ድጋፋቸው ሲገልፁ “ኣረመኔው መለስ ዜናዊ በሞተበት ሳምንት ከእናንተ ጋር እዚህ በመግኘቴ ታላቅ ደስታ ይሰማኛል” ብለው በመናገር የሚታወቁ በስላሴ አምሳያ ፍጥረት በሆኖው የሰው ልጅ ሞት ከመደሰት አልፈው ደስታቸውን በአደባባይ የሚገልፁ “መንፈሳዊ ኣባት” አይደሉም ወይ?

የትግራይ ህዝብ እኚህን ኣቡን በብሄርም ማለትም በትግራዋይነታቸውም በመንፈሳዊ አባትነትም እንዲቀበላቸው ቢቀርቡለት በግድ እንኳን ቢጋተው ስጋው ተመልሶ እንደሚተፋቸው ከሊቅ እስክ ደቂቅ ሁሉም የሚያውቀው ጉዳይ ነው።

ያመነም ያላመነም በሰይፍ!

“የሰሜኑ ጦርነት” የሚለው ስም ቤተክርስትያን ሳታላምጥ የዋጠችው የትግራይ ዘር ፍጅት መንግስታዊ የዳቦ ስም ነው። ቤተክህነትዋ በትግራይ ላይ የዘመቱ የአገር ውስጥም የውጭ አገርም ሠራዊት በመሬትም በሰማይም በትግራይ ህዝብ ላይ ለሚያዘንቡት የቦምብ እና መድፍ ዝናብ መግዢያ ይረዳት ዘንድ ከመከላከያ ጎን እቆማሎሁኝ በሚል የጥፋት መሪ ቃል ከአማኞችዋ የሰብሰበችው ረብጣ ብር፣ ዶላር፣ ዩሮ ወዘተ በገዛ ፈቃድዋ ለመንግስት ካዝና ገቢ ኣድርጋለች።

የዘር ማጥፋት ዘመቻው የፋይናንስ እክል እንዳይገጥመው ሙዳይዋን ዘርግታ ለጦርነቱ ብር ስብስባለች፤ ካህናቶችዋ ልብሰ ካህናት አስለብሳ በአደባባይ ሰልፍ አሰልፋ “ድል ለጥምር ጦሩ!” ድል ለመከላከያ፣ ድል ለአማራ ፋኖ፣ ድል ለክልል ልዩ ሃይሎች፣ ድል ለኤርትራ ሰራዊት፣ ድል ለአረብ ኤምሬትስ ድሮን ተካሾች ብላ አስነግራለች።

ትግራይ ውስጥ ያሉትን ያመኑም ያላመኑም ሁሉ ሰይፍ እንዲያርፍባቸው ተከታዮችዋን አስከትላ “የሰሜኑን ጦርነት” እያለች ዘምታለች። ታዲያ የትኛውን ትግራዋይ ነው ይህችንን ቤተክርስትያን የኔም መጠለያዮ እና መታመኛዮ ቤት ነች ብሎ እንዲቀበላት ጦማሪውም ሲኖዶሱም የሚጎተጉቱት?

ውድ ጦማሪው!

መራራው እውነት ልንገርዎት፤ ያቺ ከአብርሃ ወአጽብሃ ዘመን ጀምሮ ለመላው አቢሲንያ (ኢትዮጵያ) የወንጌል ብርሃንዋን ራስዋ እንደ ሰም እየቀለጠች የእምነት ክርዋን ያስቀጠለች የአቡነ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ቤት፣ ትግራይ ጓዳዋን ኣፅድታ ወደ ቀደምት መተዳደሪያ መንበርዋን ለመመለስ የመጨረሻው መጀመርያ መንግድ አጋምሳዋለች።

እርስዎ በትብያ የውስጥም የውጭም የመንበረ ሰላማ ጠንሳሾችና ኣስተባባሪዎች ያልዋቸው የሃይማኖት አባቶቻችን ደጉም ክፉውንም ከህዝባቸው ጋር ሲካፈሉ ቆይተው እርስዎን ቢያጡትስ ብለው ያሰጋዎትን የቤተ ክህነት ወርሃዊ ደሞዝ ተጠይፈው የመንፈስ አርነትን ሊያስረክቡን ቆርጠዋል።

አባቶቻችን በአራተኛው ክፍለ ዘመን የተተከለውን መንበረ ሰላማን፣ ነገር ግን በኣስራ ሶስተኛው ክፍለ ዘመን በተቋቋመው መንበረ ተክለሃይማኖትን እንዲኮሰምን የተደርገበትን ኣሰራር ፍትሃዊ ኣለመሆኑን በግልጽ በማስርዳት፣ በሰይጣን መመራት የናፈቀውን መንበረ ተክለሃማኖትን ለባለ ቤቶቹ ትተው፣ አባራውን ጠርገው፣ ወደ ራሳቸውን ቤት በመመለስ ላይ ናቸው።

መንበረ ተክለሃይማኖትን ከስምንት ክፍለ ዘመን ዕድሜ በላይ የሚበልጠው መንበረ ሰላማ ወደ ነበረበት ለመመለስ መስራት፣ መምራት፣ ማስተማር በማንኛውንም መንፈሳዊም ህጋዊም ሚዛን ሃጥያት የሚያሰሪ፣ የመንፈስ እርካታ የሚግናፅፍ የተቀደሰ ተግባር ነው። ለዚህ ቅዱስ ተልእኮ ሰማእት መሆን መታደል ነው። ምክንያቱም ለራስ መንፈሳዊ አርነት ሲባል እስከ የህይወት መስዋእት ቢከፈል፣ በትውልዶች ሲታወስ የሚኖር የሚያኮራ የልበ-ብርሃኖች ስራ ነውና።

ኣመሰግናለሁኝ።