ስለ ተክለሃይማኖቶች እና አባ ሰላማ

ደጀን የማነብርሃን

“ከሶርያዊው ሰላማ ኢትዮጵያዊው ተክለሃይማኖት ይቀርበናል” የሚለው አገላለፅ በትውልድ ከሆነ “አዎን” ነው መልሱ። ሆኖም ግን ስለ ትውልዳቸው ሳይሆን እየተወራ ያለው ስለ ክህነት፣ ተዋረድና ስርዓት ነው።

“አቡነ ተክለሃይማኖት” ምንኩስና የሌለው ፖለቲከኛ ሆኖ ሳለ “አቡነ” የሚል መዓርግ የተሰጠው ሰው ነው። አለፍ ሲልም ከሃያ አራቱ (24) ካህናተ ሰማይ፣ የሥላሴ መንበር ያጠናል ተብሎ ድርሰት የተደረሰለት ሰው ነው።

ለዚህም የአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ “ሃይማኖተ አበው ቀደምት“ ገጽ 9-10 መፅሓፍ ላይ እጨጌ ተክለሃይማኖት የሳይንት ተወላጅ ሲሆን ያገባ ሃብታምና መዐሰብ እንደነበረና ድንግል መኖክሴ እንዳልሆነ፤ የዛጐ መንግስት ለማፍረስ ለ12 ዓመታት እንደተጋደለና ተጋድሎው ለስጋ እንጂ ለነፍስ እንዳልነበረ የሚገልፀውን ማውሳት ይቻላል።

በተጨማሪም አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ “አስረጅ አማርኛ የግዕዝ ቁራኛ በ፬ እማኛ በ፭ኛ ዳኛ” በሚለው መፅሐፋቸው ገጽ 12 ላይ ደግሞ የደብረሊባኖሱ ተክለሃይማኖት የቀዳማዊው ተክለሃይማኖት ታሪክ ወስዶ እንጂ፣ ቅድስና እንዳልነበረው “ከግራኝ በኃላ ባፄ ሚናስ ዘመን ዕጨጌው ተክለሐይማኖት በሞቱ በ254 ዓመት የኋላ ሰዎች እናባ ዮሐንስ ከማ እንደ ቅኔና እንደ ድርሳን ቀምመው አጣፍጠው የጻፉት ገድል ግን የጻድቁን ሥራ ለጨጌው ሰጥቶ ፃድቁንና እጨጌውን በሙጫ ጸያፍ አጣብቆ ለጥቆ ባንድ ስም ጨፍልቆ አንድ ሰው አድርጎ ያልጠራ ያልበራ ድፍርስ ጨለማ ታሪክ ይተርካል በጻድቁና በጨጌው መካከል ሁለቱን የሚለይ ታላቅ ረዥም ገደል 550 ዓመት አለ” ሲል ያወሳል። እንግዲህ ወ እጨጌ መንበረ ተክለሃይማኖት ለሚለዉ መዓርግ መነሻ የሆነዉን ተክለሃይማኖት ማንነቱ እንዲህ በማያሻማ መልኩ ተከትቦ እናገኘዋለን።

ከገድለ ተክለሃይማኖት፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ አንቱ ከተባሉት የታሪክ ፀሐፊዎቹ እንደነ ፕ/ር ላጲሶ ገ. ደሌቦ “የኢትዮጵያ ታሪክ” በሚለዉ መፅሓፋቸው ከገጽ 10 ጀምሮ ፣ ተክለፃዲቅ መኩሪያ “የኢትዩጵያ ታሪክ ከልብነ ድንድል እስከ አፄ ቴዎድሮስ አንደኛ መጽሃፍ” ገጽ 15-16 ፣ ዶ/ር ሃብተማርያም አሰፋ ” የኢትዩጵያ ታሪክ ጥያቄዎችና ባህሎች ” መፅሃፍ ላይ ገጽ 282 -283 ብግልፅ እንደተቀመጠው፣ አንድ የምንረዳው ተመሳሳይ የታሪክ እውነት አለ።

  • ተክለሃይማኖት የዛግዌን ሥርወ መንግሥት ሐሰተኛ የፕሮፓጋንዳ መንገድ በመጥረግ ይኩኖ አምላክን ለንግስና ስላበቃ ለውለታው እጨጌ (በቤተ ክህነት ውስጥ የቤተመንግስት ወኪል ማለት ነው) የሚል መዓርግና፣ ሲሶ መሬት ለቤተ ክህነት የተቸረው እንደ ዘመናችን ጭሉሌዎቹ እንጂ ጳጳስ አልነበረም። ጳጳስ ነበር የሚል ካለ ደግሞ እገሌ የሚባል ፓትሪያሪክ/ጳጳስ ተሾመ ወይም መንበር ዘርግቶ እነ እገሌ የሚባሉ ደቀ መዛምርት/ተማሪዎችን አፈራ፣ የሚል ማስረጃውን ማቅረብ ይችላል። የዚህ የፖለቲካና ሃይማኖት መቀላቀል ውርስ ነው እንግዲህ ዛሬም ጳጳሳቱ ከእግዚአብሄር ይልቅ ለቄሳር አድልተው፣ መንፈሳዊነት ርቋቸው ከፖለቲከኞቹ በላይ ጨካኞች ሆነው ያየናቸው።
  • ተክለሃይማኖት የቤተ መንግሥትና የቤተ ክህነት የመጀመርያው ጋብቻ አስፈፃሚ ከመሆኑም በላይ “ወመሃሮሙ ጋኔን ልሳኖሙ ለሰብኣ አገው፤ እስመ ሰብአ አገውሰ ኃያላን እኩያን እመንቱ” ፣ “የአገው ህዝብች በሰለሞናዊው ዙፋን መቀመጥ የማይገባቸው ሰርጎ ገብ ወንበዴዎች ናቸው” ፣ እና “የላስታ የዛጉዬ መንግስት በእግዚአብሔር ያልተፈቀደ የተረገመ ነው” የሚሉ ፕሮፖጋንዳዎች በመንዛት ለመጀመሪያ ጊዜ ጥላቻንና ዘረኝነትን ወደ ቤተ ክህነት ያስገባ፣ ለዛሬው ተቋማዊ ምስቅልቅል ትልቁ ድርሻ የነበረው ሰው ነው።
  • በገድለ ተክለሃይማኖትም ሆነ በብዕለ ነገሥት መጨረሻ ላይ “ተክለሃይማኖት ይኩኖ አምላክን ቅብኣ መንግስት ቀብተው ከይትባረክ ጋር ጦርነት እንዲገጥም ላኩትና ተዋግቶ ገድሎት በእግዚአብሔር ፈቃድና በ አቡነ ተክለሃይማኖት ልመና ነገሠ” በማለት ወደ ጦርነት በመስቀል ባርኮ ዝመት የሚል ሌጋሲ በመተው ለዘንድሮዎቹ ጦረኛ ጳጳሳትና ካህናት አርአያም ነው።

ስለ ተክለሃይማኖት ብዙ ማስረጃዎች ማቅረብ ይቻላል። ለጊዜው እዚሁ ይብቃንና ለምንድን ነው መንበረ ሰላማ እየተባለ ያለው ለሚለው እንደሚከተለው መልስ እንፈልግለት።

አቡነ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን (ሶርያዊው) በእስክንድሪያ ፳ኛው ፓትርያርክ ቅዱስ አትናቴዎስ አንብሮተ እድ የተሾመና ወደ አገር ቤት ተመልሶም ጳጳስ ፣ ካህናትና ዲያቆናት በመሾም እንዲሁም ወንጌል በማስፋፋት ትልቅ ውለታ የዋለ ቅዱስ ስለሆነና መንበሩም አክሱም ስለነበረ ነው።

በምን ምክንያት ቢሉ፣ አራቱ ታላላቅ የክርስትና መንበራት የተጠሩት በሰበኳቸው ወንጌላውያን ነውና፣ አቡነ ሰላማም ወንጌል ስላስፋፉ ነው በእሳቸው መጥራት ተገቢ የሚሆነው። ለምሳሌ የእስክንድሪያ (ግብፅ) ቤተ ክርስቲያን መንበር፣ ወንጌል በሰበከላት በቅዱስ ማርቆስ ይጠራል፣ የህንድ ቤተ ክርስቲያን መንበር፣ ወንጌል በሰበከላት በቅዱስ ቶማስ ይጠራል፣ የአርመንያ ቤተ ክርስቲያን መንበር፣ ወንጌል በሰበከላት በቅዱስ ግሪጎሪ ዘኢሉሚናተር (ጎርጎሪዎስ ከሳቴ ብርሃን እንደማለት ነው) ይጠራል ፣ . . . የሌሎቹም እንደዚሁ ነው።

ታድያ እንዲያ እንደሆነ እየታወቀ፣ ለምን በ4ኛው ክፍለ ዘመን ወንጌል ለመጀመሪያ ጊዜ ያስፋፋውንና መዓርገ ጵጵስና ያለውን አቡነ ሰላማ ተትቶ የምንኩስና ሂወት ባልነበረው እና በወንጌል ፈንታ ጥላቻንና ዘረጅነት እንዲሁም የጭፍጨፋ ወንጀልን ባስፋፋ የ13ኛ ክዘመ ፖለቲከኛ ስም መንፈሳዊ መንበር መጥራት ተፈለገ ለሚለውን የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት መልስ ይስጡበት።

ወስብሓት ለእግዚአብሔር ፣ ወለ ወላዲቱ ድንግል ፣ ወለ መስቀሉ ክቡር አሜን!

—————————————————————————————————-

ደጀን የማነ ተኽለ፣ አውስትራልያ በሚገኘው ኒው ሳውዝ ዌልስ ዩኒቨርሲቲ የፒኤችዲ ተማሪ ሲሆን፣ በመቐለ ዩኒቨርሲቲ፣ የጤና ኮሌጅ ስፔሻላይድ ሆስፒታል መምህርና ተማራማሪ ነው።