በመንግስት ጫና ምክንያት ለመዘጋት እና ሰራተኞቹን ለመበተን የተገደደው የአውሎ ሚዲያ የተሰጠ መግለጫ

የኢትዮጵያ መንግስት ላለፉት 3 አመታት የአውሎ ሚዲያ ጋዜጠኞች በተደጋጋሚ ሲያስር መቆየቱ ይታወሳል። ሰኔ 23ም በተመሳሳይ ጋዜጠኞቹን ለእስር ድርጅቱንም ለመታሻግ ያበቃው ይህ ነው የሚል ምክንያት የለም። ሆኖም ሰኔ ላይ የተቋረጠው የሚድያው ስርጭት እስካሁን አልተከፈተም።

በመሆኑም ድርጅቱ ይህንን ግፎች አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ሰኔ 23/2013 ዓ.ም መንግስት የፌዴራል ፖሊሲን በመላክ በርካታ የድርጅቱን ንብረቶችን በመውሰድ ፤የስራ ቦታውን ሙሉ በሙሉ በማሸግ እና የድርጅቱን ሰራተኞች ኢ ፍትሃዊ በመሆነ መንገድ በአፋር ክልል አዋሽ ሰባት የፈዴራል ፖሊስ ተቋም ውስጥ በማሰርና በማፈን ከፍተኛ ግፍ ፈፅሞባቸዋል ሲልም ተቃውሞውን ገልጿል፡፡

ምንም እንኳ ፍርድ ቤቱ የድርጅቱ ሰራተኞች እንዲለቀቁ እና የሰራተኞቹ የግል ንብረት እንዲመለስ እንዲሁም ፖሊስ ያሸገውን የድርጅቱን ቢሮ እንዲከፈት ቢወስንም እስካሁን ድርስ ከፌዴራል ፖሊስ ምላሽ አልተገኘም በማለት ፤ስለሆነም መንግስት በተፈጠረው ችግር ምክንያት ድርጅቱ ሰራተኞችን ሙሉ በሙሉ አሰናበቷል ሲል አውሎ ሚዲያ በመግለጫው አስፍሯል፡፡

መግለጫው አክሎም ለድርጅቱ ሰራተኞች እና ለአውሎ ሚዲያ ተታታዮች ባስተላለፈው መልዕክት ሚዲያው በሚያቀርባቸው ፕሮግራሞች በርካታ የሃገር ውስጥ እና ከሃገር ውጭ የሚኖሩ ተመልካቾችን ቀልብ ቢስብም የኢትዮጵያ መንግስት በኩል ሆን ተብሎና ታስቦ በድርጅቱ ላይ ባደረሰው ኢ ፍትሃዊ በደልና ከአቅም በላይ በሆነ ችግር ምክንያት ወደ ስራ ለመመለስ ባለመቻሉ ይቅርታ በመጠየቅ ለነበረው የ3 አመት የአብሮነት ጊዜም አመስግኗል፡፡