በኢትዮጵያ መደገም የሌለባቸው የየፀጥታው ምክር ቤት የየመን ስህተቶች!

(ይህ ፅሑፍ በታጋይ ዶ/ር ሙሉጌታ ገብረሕይወት (ሙልጌታ ጫልቱ) በእንግሊዘኛ ቋንቋ በWorld Peace Foundation ገፅ የታተመ ሲሆን አኽሱማይት ሚዲያ እንደሚከተለው ወደ አማርኛ መልሶ አቅርቦላችኋል)።


በኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ያለው ጦርነት አሁን የአገሪቱ መንግሥት የፀጥታው ምክር ቤት አባላትን እንዲማልድ በሚያስገድደው ደረጃ ላይ እየደረሰ ነው፡፡ ጊዜው፣ምክር ቤቱን ጣልቃ እንዲገባና የውሳኔ ሐሳቦችን እንዲያስተላልፍ የሚጠበቅበትም ነው፡፡ይህ ግን በተሳሳተ መንገድ ከተጓዘ የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔ የሠላም እንቅፋት እንጂ የመፍትሔ መላ አይሆንም፡፡


በምድር ላይ ያለው የሃይል ሚዛን ልዩነትና የዚህ ልዩነት ትርጉም በግልጽ ከሚታይባቸው ቦታዎች ቁንጮው የፀጥታው ምክር ቤት ውስጥ ነው፡፡ ሁሉም የምክር ቤቱ አባላት ተስማምተው ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ካላቸው አምስት አገራት አንዷ ከተቃወመችው ምንም አይነት የውሳኔ ሃሳብ ሊኖር አይችልም። እስካሁን በትግራይ ጉዳይ ላይ የሆነውም ይህ ነው፡፡


የፀጥታው ምክር ቤት በትግራይ ጉዳይ ላይ አስራ አንድ ስብሰባዎችን አድርጓል፡፡ ነገር ግን ውሳኔ ማሳላፍ ኣይደለም አንድም ይፋዊ መግለጫ ለመስጠት እንኳን ተስማምቶ ኣያውቅም። ሩሲያ እና ቻይና ፍላጎታቸውን በሦስቱ አፍሪካውያን የምክር ቤት አባላት ጀርባ ከልለው የትግራይን ችግር የኢትዮጵያውያን የውስጥ ችግር ነው ብለው በመግለጽ እና አሳሳቢ የሆነ መግለጫ ሊያወጣ የሚችለውን ማንኛውንም ሂደት በማደናቀፍ ጉዳዩን ለኢትዮጵያ መንግስት እንተወው በማለት ምክርቤቱን ውጤትየለሽ አድርገውታል፡፡


በእርግጥም መንግሥት ሉዓላዊነት ማለት በቅድሚያ የራስን ህዝብ ደህንነትና ሰላምን ማስጠበቅ እንደሆነ ገብቶት የራሱን ዜጎች ደህንነትና ፍላጎት ለማስጠበቅ ቢሠራ ማንኛውም የኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ለኢትዮጵያ መንግሥት ሊተው በተገባ ነበር። የትግራይ ችግር የፀጥታው ምክር ቤት ጉዳይ ሊሆን የቻለበት ምክንያት የኢትዮጵያ መንግስት ሕዝብን መጠበቅ ስላቃተው ብቻ ሳይሆን በትግራይ ሕዝብ ላይ የዘር ማጥፋት ጦርነት በማወጁም ምክንያትም ነው። በዚህ ምክንያት ነው ጉዳዩ የኢትዮጵያ መንግስት የውስጥ ጉዳይ ነው ተብሎ መተው የሌለበት። ስለዚህም ነው የጸጥታው ምክርቤት ኣባላት በተለያዩ ምክር ቤቱ የሚወያይባቸው ጉዳዮች የሚይዙት አቋምና ውሳኔ ለሉዓላዊነት ከመቆርቆር ይልቅ በፖለቲካዊ ጥቅም እና በየራሳቸው መርህ ላይ የተመሰረተ መሆኑን መረዳት የሚቻለው።፡


ይህ መዋቅራዊ ማነቆ እያለ ቢሆንም ግን ምክር ቤቱ በተደጋጋሚ የዓለም የጋራ የደህንነት ጉዳዮችን የተመለከቱ በተደጋጋሚ ውሳኔዎችን ሲያሳልፍ ይታያል። አንዳንድ የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔዎች በጥሩ ሁኔታ የታሰቡ ቢሆኑም ይዘታቸው ግን መሬት ላይ ካለው ሀቅ ጋር የተጣሉ ናቸው፡፡ይህ ምክር ቤት በ2016 በየመን የፈፀመው ስህተት ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡

አሁን በትግራይ ጦርነት ላይ ያለው የሃይል ሚዛን ተቀይሮ ብልጫው በትግራይ ሠራዊት መዳፍ ላይ ወድቋል፡፡ይህ አዲስ ለውጥና እድገት ምክር ቤቱ አዳዲስ ውሳኔዎችን ለማሳለፍ ፍላጎት እንዲያድርበት ሊያደርግ ይችላል፡፡ ይህንን ከማድረጉ በፊት ግን ምክር ቤቱ ከቀደምት ስህተቶቹ እና በተለይም የመን ላይ ካሳለፈው ውሳኔ ቁጥር 2216 እና ውሳኔው ከፈጠረበት ማነቆ በቂ ትምህርት መውሰድ ይኖርበታል።

የየመን ቀውስ

እ.ኤ.አ በ2012 በወቅቱ የየመን ፕሬዚዳንት የነበሩት አሊ አብዳላህ ሳላህ ሥልጣናቸውን ለጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት እንዲያስረክቡና በምላሹም ያለመከሰስ መብታቸው እንዲጠበቅላቸው ተደረገ፡፡ከዚያም በአሊ ዘመን ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩት አብዲ ራቡ መንሱር ሀዲ የሽግግር አስተዳደሩን ለሁለት ዓመት እንዲመራ ሆነ፡፡ የሽግግር መንግሥቱ ዋና ተልዕኮ የመንን ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማዘጋጀት ቢሆንም፣አስተዳደሩ ግን ይህንን ሥራ እንደ ሙሉ ጊዜ ተግባር አልወሰደውም፡፡ሀዲ ወደ ሥልጣን እንደወጡ ሕጋዊ ቅቡልነትን የሚጠይቁ እርምጃዎችን በነፃነት ፈፀሙ፡፡የመንን የዓለም የንግድ ድርጅት አባል አደረጓት፡፡አዲስ መንግሥታዊ መዋቅርም አነበሩ፡፡


ይሁን እንጂ ሁለቱም እርምጃዎች በብዙ የየመናውያን፣ የውጭ ሃይሎችን ጥቅም ለማስጠበቅ እና ጥያቄ የሚያነሳውን የአገሪቱን ሕዝብ በድህነት እና በአስተዳደራዊ በትር ለማንበርከክ የተደረገ አይን ያወጣ ጥረት ተደርጎ ይወሰድ ነበር። በዚህ ምክንያት የመኖች በተለያየ መልኩ ጊዜያዊ መንግስት የሚወስናቸውን ውሳኔዎችና እርምጃዎች መቃወማቸውን ቀጠሉ፡፡ሕዝባዊ ቁጣው እያየለ በመጣ ጊዜም የሽግግር መንግሥቱ የሥልጣን ዘመኑን ከተቀመጠለት ቀነ ገደብ ውጪ አራዘመ፡፡ ይህ እርምጃ ደግሞ በአሜሪካ፣በባሕረሰላጤው አገራት ሕብረት- GCC (ሁለቱም የሽግግር ስምምነቱ ኣዋላጆች የነበሩ ናቸው)- የተደገፈ ነበር። በዚህም በአገሪቱ ያለውን ሕዝባዊ ተቃውሞው አጠናከረው፡፡ የአምላክ ታዛዦች በመባል የሚታወቀውና በወቅቱ በሕቡዕ የሁቲ ንቅናቄ በሚል ሥም የሚጠራው የትጥቅ እንቅስቃሴ እ.ኤ.አ በነሀሴ 2014 አብዛኛውን ሰሜናዊ የመን እና ዋና ከተማዋን ሰነዓን ተቆጣጠረ።ልክ የፀጥታው ምክር ቤት 2216 የተባለውን የውሳኔ ሐሣብ ይፋ ሲያደርግ የየመን የርስበርስ ጦርነትም ተባባሰ፡፡


የውሳኔ 2216 ቁልፍ ችግሮች


ውሳኔው ጥሩ ሀሳቦችን ስለመያዙ መካድ አይቻልም፡፡ ይሁን እንጂ የውሳኔ ሀሳቡ አንዳንድ አንቀፆች ግን መሠረታዊ ችግሮችን ያዘሉና የአገሪቱን ቀውስ ከድጡ ወደ ማጡ ያስገቡ ነበሩ፡፡ እነዚህም፡


1-ያለቅድመ ሁኔታ ለመንሱር ሐዲ መንግሥት እውቅና መስጠት፣
2-ሀውቲዎች ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ ትጥቅ እንዲፈቱ መጠየቅ፣
3-ሀውቲዎች ከ2014 በፊት ወደነበሩበት ግዛትና ሁኔታ እንዲመለሱ ማድረግ፤ የሚሉት ነበሩ፡፡

እነዚህ የውሳኔው ድንጋጌዎች ያመጡትን ጣጣ በዝርዝር እንመልከተው፡፡

1-ያለቅድመ ሁኔታ ለመንሱር ሐዲ መንግሥት እውቅና ቅቡል ማድረግ፣

ውሳኔ 2216 በመግቢያው ላይ የፀጥታው ምክር ቤት የየመንን ፕሬዝዳንት አብዶ ራቦ ማንሱር ሃዲ ህጋዊነት እንደሚደግፍ እና ሁሉም ፓርቲዎች እና አባል ሀገራት የአገሪቱን አንድነት፣ ሉዓላዊነት፣ ነፃነት እና የግዛት አንድነት የሚጎዳ ማንኛውንም እርምጃ ከመውሰድ እንዲቆጠቡና የየመኑን ፕሬዝዳንት ሕጋዊነት ማንም አካል ጥያቄ ውስጥ እንዳይከት ያሳስባል። ይህንን ሃሳብ በማጠናከር የውሳኔው አንቀጽ 1(d) ሁቲዎች ‹‹በሕጋዊው የየመን መንግሥት ሥልጣን ላይ ያነሱትን የትኛውንም ዓይነት ድርጊት እንዲያቆሙ›› ይጠይቃል፡፡

እንዲህ ዓይነቱ ሙሉ እና ፍፁም የሆነ ዕውቅና መሰጠቱ የተባበሩት መንግስታት ልዩ መልዕክተኛ ግኑኝነቱ እውቅና ካለው ‘ህጋዊ’ መንግስት ብቻ እንዲወሰን ኣድርጎ አጠበበው። ከውሳኔ ቁጥር 2216 በኋላ ብዙም ሳይቆይ ሀውቲዎች ትግላቸውን በማፋፋም አብዛኛውን የየመንን ክፍል ተቆጣጠሩ፡፡


የመንግስት ቁጥጥር በስፋት የነበረባትን የኤደን የወደብ ከተማ ለመቆጣጠ ተንቀሳቀሱ። ብዙም ሳይቆይ ከኤደን ከተማ የሃዲ መንግስት ተጠራርጎ ወጥቶ ኣካባቢውን ኢስላህ በሚል የሚጠራ ሌላ ሁቲዎችን የሚቃወም ሃይል ተቆጣጥሮት የሀዲ መንግስት የስደት መንግስት ወደመሆን ተሸጋገረ።
በዚሁ የውሳኔ ሐሣብ ላይ በአንቀጽ 7 የሠፈረው ሐሳብ ደግሞ ሁሉም ወገኖች በሪያድ ለሚደረገው ጉባኤ የየመኑ ፕሬዚዳንት የሚያቀርቡትን ጥያቄ በአወንታዊነት እንዲቀበሉ ያስገድዳል፡፡ ይህ ድንጋጌ ሁሉም ፓርቲዎች የመንግሥትን ቅቡልነት የተስማሙት አስመሰለው፡፡ይሁን እንጂ ሀውቲዎች ለመንግሥት ያላቸው አተያይ ያበቃለት ነበር፤እንዳለም መቁጠር ካቆሙ ቆይተዋል፡፡በዚህም ምክንያት በፕሬዚዳንቱ ለሚመራ ብሔራዊ ውይይት ለመቀመጥ እንደማይገደዱ ወስነዋል፡፡


የተባበሩት መንግስታት ልዩ መል እክተኛ የስራ ዋናው የስራ መመርያ ምንጭ የጸጥታው ምክርቤት በጉዳዩ ላይ ያሳለፈው ውሳኔ ነው። በዚህም መሰረት ማንኛውም የተመድ የየመን ልዩ መልእክተኛ የስራ መመርያ ምንጭ የጸጥታው ምክርቤት ውሳኔ ቁጥር 2216 በየመን ጉዳይ ነው። በዚህም መሰረት የየመን የተመድ ልዩ ልኡኩ ውሳኔ 2216 ህጋዊነትን በብቸኝነት የሰጠውን የሀዲ የስደት መንግስትን ትቶ ከኣዲሶቹ ተዋናዮች ለመነጋገርም ይሁን ሀውቲዎች ይሁኑ ሌሎቹ ተቃዋሚዎች በሚቆጣጠርዋቸው የሚሰሩዋቸውን የመንግስትና የመንግስቲ የሚመስሉ ስራዎች ላይ ገንቢ የሆነ ንግግርና ውይይት ማካሄድ ኣይችልም። ይህን ማድረግ የሚቻለው ውሳኔ ቁጥር 2216ን የጸጥታው ምክርቤት በሌላ ውሳኔ ካሻሻለው ብቻ ነው። በጥቅሉ የያኔው የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔ እንደ በጎ የሚታይ ሆኖ ቢጀመርም ቀዳሚውን ዓላማ ሳያሳካ ተጠናቀቀ፡፡


2-ሀውቲዎች ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ ትጥቅ እንዲፈቱ ማድረግ፣


የውሰኔው አንቀጽ 1(a) የሀውቲ አማጽያን ውጊያ እንዲያቆሙ ያዛል፡፡በአንቀጽ1(c) ላይ ደግሞ ሀውቲዎች ከመከላከያና ደህንነት ተቋማት የማረኩትን ትጥቆች እንዲመልሱ ይመክራል፡፡ይህ ደግሞ በአማጽያኑ እጅ የነበሩትን ሚሳኤሎች ይጨምራል፡፡ በተጨማሪም 1(e) ላይ ሀውቲዎች ለየትኛውም ጎረቤት አገር ሥጋት ከመሆን እንዲታቀቡ፣ ትንኮሳ እንዳይፈጽሙና የጦር መሣሪያዎቻቸውን በአጎራባች አገራት ድንበር ላይ ማከማቸት እንደሌለባቸው ያስጠነቅቃል፡፡


ሁቲዎች ግን ሊያሳኩ የፈለጓቸውን ፖለቲካዊ ዓላማዎች ለማግኘት ትግላቸውን ቀጠሉ፡፡ ሁቲዎች ትጥቅ ማራገፍ የሚችሉት የፖለቲካ ዓላማቸው መፈጸሙን ካመኑ እና/ወይም የፖለቲካ ዓላማቸው በሰላማዊ ድርድር ሊሳካ እንደሚችል ካረጋገጡ ብቻ እንደሆነ መገመት ይቻላል። በዚህም ምክንያት ነው ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ትጥቅ እንዲፈቱ መጠየቅ እመሬት ላይ ካለው እውነታ የራቀ የሚሆነው። ሀውቲዎች ከጎረቤት ኣገራት ለሚሰነዝርባቸው የአየርና ተመሳሳይ ጥቃቶችን ለመከላከል የሚያሽቸል ምንም ዓይነት ዋስትና ባልሰጠበት ሁኔታ ሀውቲዎች ወደ ጎረቤት አገር ምንም ዓይነት የሚሳኤል ጥቃት እንዳይፈጽሙ መከልከልም እንዲሁ ከእውነት የተጣላ ነበር፡፡ ሀውቲዎች የሚሳይል ጥቃትን ማቆምን ከጎረቤት አገራት የሚነሳውን የአየር ጥቃት ሲቆም ለማቆም እንደሚስማሙ ገልጸው ነበር ሆኖም ግን የየመን መንግስት ሁቲዎች የሚሳይል ጥቃቱን ለማስቆም የጠየቁት የአየር ጥቃትን ሙሉ በሙሉ ማስቆም የሚለው ተመጣጣኝ ኣይደለም በሚል ጥያቈውን ውድቅ አድርጎታል። ከነዚህ ጉዳዮች በመነሳት ማለት የሚቻለው ትጥቅ ማስፈታትና የጦር መሣሪያ ቁጥጥር በዝርዝር እቅዶች ሊመራ የሚገባውና ጥንቃቄን የሚሻ ተግባር መሆኑን ነው፡፡


በትኩረትና እርጋታ በተሞላበት አካሄድ ከተሰራ ትርጉም ያለው ውጤት ይገኝበታል፡፡ ለምሳሌ ሀውቲዎች የሚሳኤል ጥቃት ማቆምን የአየር ጥቃት በማቆም ለመለወጥ ያነሱትን አካሄድ እንደ ኣካሄድ ተቀብሉ። መጀመርያ የየመን መንግስት በቅድሚያ የሚሳይል ጥቃት እንዳይፈጸምባቸው የሚፈልጋቸው የተመረጡ ቦታዎች ሁቲዎች በቅድሚያ የአየር ጥቃት እንዳይፈጸምባቸው ቦታዎች በመለየት በትንሹ ጀምሮ የእያንዳንዱን ተግባራዊነት በመመልከት እያሰፉ ሄዶ መላ የመንን ከሚሳይልና ከአየር ጥቃት ነጻ የምትሆንበትን መንገድ መቀየስ ይቻል ነበር። የተመድ የጸጥታው ምክርቤት ውሳኔ ቁጥር 2216 ግን ለእንደዚህ አይነት ቀስ በቀስ ተግባራዊ እየሆነ ስለሚሄድ የመሳርያ ቁጥጥር ለማሰብ ዕድል አይሰጥም ውሳኔው ሀውቲዎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ትጥቃቸውን እንዲያራግፉ የሚጠትቅ ስለሆነ።

3-ሀውቲዎች ከ2014 በፊት ወደነበሩበት ግዛትና ሁኔታኢ እንዲመለሱ ማድረግ፤


በውሳኔ ሐሣቡ አንቀጽ 1(b) ላይ የሰፈረው ድንጋጌ ደግሞ ሀውቲዎች ሰንአን ጨምሮ የያዟቸውን ቦታዎች ለቀው ከ2014 በፊት (ግጭቱ ከመጀመሩ በፊት) ወደነበሩበት ግዛት እንዲመለሱ ጥሪ ያቀርባል፡፡ በዚህ ወቅት ግን የሀውቲ አማጽያን የያዙትን ግዛት እስከ ኤደን አስፍተው በርካታ ቦታዎችን ተቆጣጥረዋል፡፡ከዚህ በተጨማሪም ሀውቲዎች ከአገሪቱ መንግሥት የማረኩት በርካታ ሚሳኤልና የጦር መሣሪያ እጃቸው አስገብተው ነበር፡፡
እዚህ ጋር የሚነሳው ጥያቄም ሀውቲዎች ከ2014 ወደ ነበሩበት ቦታ የሚመለሱት በምን ምክንያት ነው?ይህንን ሲያደርጉስ በምላሹ ምን ይደረግላቸዋል? የሚለው ነበር፡፡ ሁቲዎች የተኩስ ማቆም ስምምነት ለማቆም እንኳን በሳውዲ ይመራል የሚሉት ጥቃትና ወረራ ሙሉ በሙሉ እንዲቆምና እንደ የሁዴዳ የባህር ወደብንና የሰንአ አየር ማረፍያን ጨምሮ ሙሉ በሙሉ ለአገልግሎት ክፍት እንዲሆኑ እንደቅድመ ሁኔታ ይጠይቃሉ። ይህ ካልሆነ ተኩስ እንደማያቆሙ አስረግጠው ይናገራሉ፡፡


በአጠቃላይ፣ የተባበሩት መንግስታት ውሳኔ 2216 በስራ ላይ እስካለ ድረስ፣ የተባበሩት መንግሥታት ልዩ መልዕክተኛ ከሃውቲዎች እና ሌሎች በመሬት ላይ ካሉ ሃይሎች ጋር ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመንቀሳቀስ ተቸገረ፡፡በወቅቱ ከስደተኛው የሃዲ መንግሥት ይልቅ ሁቲዎችና ሌሎች ከመንግስት ውች ያሉ ፀረ ሁቲ ሃይሎች የላቀ ስልጣንና ቁጥጥር ነበራቸው፡፡ እንዲህ እያለ ልዩ መልዕክተኛው የጸጥታው ምክርቤት ውሳኔ ቁጥር 2216 እጃቸውን አስሮት በየመን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ መሰረት የጦር መሣሪያ ለመቆጣጠርና ለማስተዳደር የሚያስችሎ ዘዴዎችን ለማሰብ የሚያስችል ሥልት ማፍለቅ ተሳናቸው፡፡ ይህ ከ2014 በፊት ሁቲዎች ወደ ነበሩበት ቦታቸው እንዲመለሱ የሚጠይቀው ውሳኔ 2216 እስካልተሻረ ድረስ አማራጭ እና ተጨባጭ የሃይል ማሰማራት መንገዶችን ለማየትም ተቸገሩ፡፡


በቀላል አነጋገር የፀጥታው ምክር ቤት የየመንን ችግር ለመፍታት ያፀደቀው የውሳኔ ሃሳብ በየመን ሰላም ለማምጣት የሚያደርገውን ጥረት አበላሸበት።ይህ ምክር ቤት በኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ላይ ውሳኔ ከማሳለፉ በፊትም ከዚህ የየመን ስህተቱ መማር ይገባዋል፡፡

ጦርነት በትግራይ

የዚህ ጦርነት መሠረታዊ ምክንያት የፌደራሉ መንግሥት የአገሪቱን ሕገመንግሥት ጥሶ የራሱን አሀዳዊ ሥርዓት ለመዘርጋት ማሰቡ ነው፡፡ ይህ መሠረታዊ የጦርነቱ ምክንያት ደግሞ የአዲስ አበባው አገዛዝና አጋሮቹ ሕግ ጥሰው በትግራይ ላይ ያወጁት የዘር ማጥፋት ጦርነት የትግራይን ሕዝብ ወደ ሕልውና ትግል አስገባው፡፡አሁን የትግራዩ ጦርነት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ምክንያቱም የፌደራል መንግሥቱና አጋሮቹ ከትግራይ ተሸንፈው ከወጡ በኋላ የትግራይ ሠራዊት የሚያካሂደውን ትግል ወደ አማራና አፋር ክልል አስፍቷል፡፡


ከዚህ በኋላ ምንም ይሁን ምን የትግራይ ሠራዊት እና የትግራይ ህዝብ ያልተሸነፈ መሆኑን እና የአዲስ አበባ እና የአስመራው ስትራቴጂ ሊያሸንፍ እንደማይችል አሳይቷል። ኢትዮጵያ አሁን ወደ ከፋ የእርስ በርስ ጦርነት እና የመንግስታዊ ውድቀት አፋፍ ላይ ትገኛለች። ይቺ ከ110 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያላት ሀገር ተጨማሪ መንሸራተትን እና ፍፁም ውድቀትን ለመከላከል ለተቀናጀ አለምአቀፍ እርምጃ ዝግጅት የሚደረግበት ወቅት ነው።
የትግራይ መንግሥት የተሟላ ወታደራዊ ድልን ከማምጣት ባሻገር የሚፈልጋቸውን ጥቅሞቹን የሚያስከብርለት ፖለቲካዊ መንገድ እንዲኖር ምኞቱ መሆኑን ደጋግሞ ተናግሯል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን የአዲስአበባው መንግሥት ለድርድር እስኪዘጋጅ ድረስ ወታደራዊ መንገዱን ይገፋበታል፡፡

በዚህ ሁኔታ ውስጥ ግን የአዲስ አበባው አገዛዝ የአፍሪቃ ሕብረትንና የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤትን ፖለቲካዊ በሆነ መንገድ እንዲከላከሉት እየማለደ የድርድር መንገዶችን ሊያወሳስባቸው እየጣረ ነው፡፡ ለዚህ ነው የፀጥታው ምክር ቤት በትግራይ ጉዳይ ላይ ውሳኔ ለማሳለፍ በሚያደርገው አዲስ ጥረት ከየመን ስህተቱ መማርና ጥንቃቄ መውሰድ ያስፈልገዋል የሚል ሐሣብ የሚመጣው፡፡ ጥንቃቄን ከሚሹ ጉዳዮች ቁልፍ ነጥቦቹ የሚከተሉት ናቸው፤


1-እውቅና መስጠትን (ሁሉንም ተፋላሚ ሃይሎች) በተመለከተ
2-የሃይል አሰፋፈርን በተመለከተ እና
3-ትጥቅ ማስፈታትንና ጦር መሣሪያ ቁጥጥርን በተመለከተ


1-በፍልሚያ ውስጥ ያሉትን በትክክለኛ ስማቸው መጥራት

ተሸምጋይ ወገኖችን በትክክለኛ ስማቸው መጥራት መደበኛ አሠራር፣ የተለመደ ጨዋነት እና ለማንኛውም ድርድር ቀዳሚ መስፈርት ነው።ከዚህ አንፃር የፀጥታው ምክር ቤት በትግራዩ ጦርነት የሚፋለሙትን ሃይሎች እራሳቸውን በሚጠሩበት ስም በቅጡ መጥራት ሊጠነቀቅበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡የትግራዩን የዘር ማጥፋት ጦርነት በመከላከል ረገድ እየተፋለመ ያለውን ሃይል የሚመራው የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ነው፡፡የትግራይ መንግሥት ብለን ልንጠራው እንችላለን፡፡የትግራይ ሠራዊት በትግራይ መንግሥት ሥር ሆኖ የሕልውና ጦርነቱን የሚያካሂድ ወታደራዊ ክንፍ ነው፡፡የትግራይ መንግሥት ለሕዝቡ መሠረታዊ አገልግሎቶችን (ለአብነት ሥርዓት ማስያዝን፣ እንደ መብራት ያሉ መሠረተልማቶችን ማቅረብንና መሰል መንግሥታዊ ተግባራትን) እያቀረበ ያለ አካል ነው፡፡ ይህ ደግሞ እንዲህ ያሉ አገለግሎቶች በማዕከላዊ መንግሥት ሳይሆን ለአገሪቱ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሉዓላዊነት የሰጠውን የኢፌዴሪ ሕገመንግሥትን የተከተለ ነው፡፡

የትግራይን መንግሥት ሕወሓት እያሉ መጥራትና የትግራይን ሠራዊት የሕወሓት ጦር እያሉ መጥራት ትልቅ ስህተት ነው፡፡ ይህ ማለት የኢትዮጵያን መንግሥት ብልጽግና እያሉ እንደመጥራትና የኢትዮጵያን መከላከያ ሠራዊትም የብልጽግና ጦር ብሎ እንደመጥራት ነው፡፡ ብልጽግና የራሱ ሠራዊት እንደሌለው ሁሉ ሕወሓትም የግል ጦር የለውም።

2- የሕጋዊነት ጉዳይ

በተለምዶ በእርስበርስ ጦርነት ውስጥ ያሉ ሃይሊች አንዱ ለሌላው እውቅና አይሰጡም፡፡የፀጥታው ምክር ቤት በተለምዶ ስልጣን ላይ ያሉ መንግስታትን ቅቡልነት እንዳላቸው መንግስታት አድርጎ የመውሰድ ኣካሄድ አለበት። ይህ ግን ቅቡልነትንና ህጋዊነትን የመንግስት ስልጣንን ከመቆጣጠር ጋር አንድና ያው አድርጎ የሚመለከት ብልህነት የጎደለው መመዘኛ ነው፡፡ብዙ ኢትዮጵያዊያን ብልጽግና ፓርቲን እንደ መንግሥትነት ብቻ ሳይሆን እንደ ፖለቲካ ድርጅትም ሕጋዊነቱ ላይ ጥያቄ አላቸው፡፡የትግራይ ክልል መንግሥትን ጨምሮ ሌሎች ተቃዋሚዎቹም እንደሚሉት ደግሞ የብልጽግና ፓርቲ ሕጋዊ መንግሥትነቱ መስከረም 2013 አብቅቷል፡፡ፍፁም አጨቃጫቂ በሆነ መንገድ የኮሮና ወረርሽኝን እንደምክንያት ወስዶ ሥልጣኑን አራዝሞ በመንበሩ ላይ መክረሙ በርካታ የፖለቲካ ድርጅቶቸ ቅቡልነቱን ጥለውበታል፡፡


የትግራይ መንግሥት ይህንን ሕገወጥ የሥልጣን መራዘም ተቃውሞ በክልሉ ምርጫ አካሂዷል፡፡በዚህም 2.7 ሚሊዮን ተጋሩ ድምጽ ሰጥተው የክልሉን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሥርተዋል፡፡ የፌደራሉ መንግስት የትግራይን ምርጫ እና በዚሀም ምክንያት የተቋቋመውን ክልላዊ መንግሥት ሕገወጥ ነው ብሎታል፡፡ከዚህ በተጨማሪም ይህንን ክልላዊ መንግሥት ለማግለልና ለማስገደድ የተለያዩ እርምጃዎችን ሲወስድ ቆይቷል፡፡

ይህም በጀት መከልከል ብቻ ሳይሆን በእርዳታ የሚመጡ እንደ ሴፍትኔት መርሃግብር ያሉ የውጪ ረድኤቶችን ወደ ትግራይ እንዳይገቡ አድርጓል፡፡በኋላም በጥቅምት መጨረሻ ላይ ወደ ተሟላ ውጊያ ገብቶ በትግራይ ላይ ጦርነት ከፈተ፡፡ከዚህ የምንረዳው የትግራይም ሆነ የፌደራሉ መንግሥት ያላቸውን የሕጋዊነት ጣጣ ነው፡፡

የአፍሪቃ ሕብረት ከዚህ አንፃር በኦባሳንጆ የሚመራ የምርጫ ታዛቢ ልኮ ለዐቢይ መንግሥት እውቅና በመስጠት ወሳኝ ስህተት ሠርቷል፡፡ሕብረቱ የሰኔውን ምርጫ እውቅና መስጠቱ ሳያንስ ይህንን እውቅና የሰጡትን ግለሰብ ደግሞ በምርጫ ምክንያት የተፈጠረን ጦርነት እንዲያሸማግሉ መደባቸው፡፡ይህ እልም ያለ አድሏዊነት ነው፡፡እንዲህ ላለ ብልሹ የፖለቲካ ሂደት እውቅና የሰጠ አካል በቀጣይ ምን ዓይነት ዝግጁነት እንዳለውም የሚያሳይ ነው፡፡የፀጥታው ምክር ቤት ይህንን ስህተት መድገም የለበትም፡፡ምክር ቤቱ እንዲህ ባለ ጉዳይ ላይ ከመግባት ይልቅ እውነተኛውንና መሬት ያለውን እውነታ ሊገነዘብ ይገባዋል፡፡የዓለማቀፉ ማሕበረሰብ በአጽንኦት መግፋት ያለበት የኢትዮጵያን ችግር በሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ድርድርና ውይይት እንዲፈታ ነው፡፡ ብዙዎች የአገሪቱ ሕብረትና ግዛታዊ አንድነት ሲያሳስባቸው ተስተውሏል፡፡ ለተጋሩ ደግሞ የፌደራሉ መንግሥት ሁሉንም ክልሎች፣የኤርትራን ሠራዊትና ሌሎች የውጭ ሃይሎችን በማስተባበር ከምድር ለማጥፋት እንደተሰማራ ተደርጎ ነው የሚታየው፡፡

ቢቻል የትግራይ ተወላጆች ሁሉንም ባሳተፈ ውይይት ላይ ለመሳተፍ (ከሌሎች ነገሮች በተጨማሪ) እድል ለመስጠት ዝግጁ ናቸው።ለፀጥታው ምክር ቤትም ሆነ እና ለአለም ህዝብ ግን ግልፅ መሆን ያለበት የኢትዮጵያ መንግስት ይህን አይነት የውይይት ሙከራ አደራጅቶ ለመምራት ብቃት እንደሌለው ነው።የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን ሀላፊነት ወስዶ አካታች የውይይት መድረክ እንዲያዘጋጅ እድል መስጠት ግን አጀንዳውን ከጅምሩ መግደል ነው የሚሆነው፡፡የውይይቱ ቅርጽ፣አደረጃጀትና አመራር የድርድሩ አካል ነው መሆን ያለበት፡፡

3-የሃይሎች መልሶ ስምሪት የፖለቲካ ሂደቱን የተከተለ መሆን አለበት፡፡

በትግራይ የተጀመረው ጦርነት አሁን በተለያዩ የአማራና የአፋር አካባቢዎች ሰፍቷል፡፡ የአሜሪካ መንግሥትና የአውሮጳ ሕብረት ተፋላሚ ሃይሎች ከጥቅምት 24-2013 በፊት ወደነበሩበት ወታደራዊ ቦታ ይመለሱ የሚል ተደጋጋሚ መግለጫዎች አውጥተዋል፡፡ በቅርቡ ደግሞ የአፍሪቃ ሕብረት የኢትዮጵያ መንግሥትን አቋም ይዞ የትግራይ ሠራዊት ከጥቅምት 2013 በፊት ወደነበረበት እንዲመለስና በምላሹም የሰብዓዊ አገልግሎት መስመሮች እንደሚከፈት የሚገልጽ ሐሳብ አምጥቷል፡፡


የዚህ ሐሣብ ቀዳሚ ችግር ሰብዓዊ አገልግሎት መስጪያ መሥመሮችን መከፍት ከተኩስ ማቆም ጋር ማገናኘቱ ነው፡፡የሰብዓዊ አገልግሎትን ለማድረስ ተኩስ ማቆምን እንደ ቅድመ ሁኔራ ማስቀመጥ የዓለምን የሰብዓዊነት ሕግ የሚጥስ ነው፡፡

የሰብአዊ እርዳታ ምንም ይሁን ምን መከናወን አለበት፡፡ አስገድዶ መድፈር እና ወሲባዊ ጥቃት በማንኛውም ሁኔታ የተከለከለ ነው፡፡ቀጣይነት ያለው ጦርነት ቢኖርም እንኳን ሰላማዊ ዜጎች ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል፡፡በነዚህ ምክንያቶች ሠራዊቶችን ወደነበሩበት መመለስም ሆነ ተኩስ ማቆም የሰብዓዊ አገልግሎት ማሳላጫ መስመሮችን ለመክፈት እንደ ቅድመ ሁኔታ መቀመጥ የለባቸውም፡፡


የዚህ ምክረ ሐሣብ ሁለተኛው ችግር የትግራይ ሠራዊት ወደ አማራ ክልል የገባበትን ምክንያት አለመረዳቱ ነው፡፡የትግራይ ሠራዊት ወደተጠቀሱት ክልሎች የገባው የጅቡቲ-ሰመራ-መቀለን መስመር ለማስከፈትና የሠብዓዊ እርዳታዎቹን ለማግኘት ብቻ አይደለም፡፡በትግራይ ላይ ያለው ከበባ እንዲያበቃና በአማራ ሃይሎችና በኤርትራ የተያዙ የትግራይ መሬቶች ተለቀው ሁኔታዎች ወደ ጥቅምት 2013 እንዲመለሱ ለማድረግ ነው፡፡ከዚህ በተጨማሪም በትግራይ የተፈፀመውን ዘር ማጥፋት ወንጀል ያከናወነ ሃይል ሙሉ ተጠያቂነት እንዲኖርና ዳግም እንዳይፈፀምም ያለመ ወታደራዊ ዘመቻ ነው-የትግራይ ሠራዊት እያካሄደ ያለው፡፡ ትግራይ ሙሉ በሙሉ ነፃ ሳትወጣና ዳግማዊ ወረራ እንደማይካሄድባት ማረጋገጫ ሳይገኝ የትግራይን ሠራዊት ወደ ክልልህ ተመለስ ማለት የማይታሰብ ነው፡፡


ከዚህ አንፃር የተሟላ ፖለቲካዊ መፍትሄ ለማምጣት ሶስት ቅደም ተከተሎችን መከወን ያስፈልጋል፡፡የመጀመሪያው፣ ደረጃ ፈጣን እርምጃ ሲሆን ይህም የሚከተሉትን ያካትታል፡፡የሰብአዊ አገልግሎቶችን ያለገደብ ማቅረብ፣ አስፈላጊ አገልግሎቶችን መልሶ ማስጀመር፣ የኤርትራን ጦር እና የአማራን ሚሊሻ ከትግራይ ማስወጣት፣ የጥላቻ ፕሮፓጋንዳንና የአመፅ ማነሳሳትን ማቆም፣ የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት የሚሉት ከድርድሩ ጅማሮ በፊት እንደ አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታ መታየት አለባቸው፡፡

ሁለተኛው መንገድ ደግሞ የፌደራሉ መንግሥትና የትግራይ ክልል መንግሥታት የሚፈጽሙት ተኩስ አቁም ሲሆን ይህም ያፖለቲካ ችግሮቹ በሚፈቱባቸው መርሆዎች፤ ዘላቂ የፓለቲካ ችግሮችን ለመፍታት የሚኖሩ ዋና ዋና ማመላከቻ መርሀ ግብሮች፤ እኒዚህ የሚፈጸሙበት የጊዜ ሰሌዳና የመሳሰሉ ነገሮች ድርድፍ የሚገረግበት ምዕራፍ ነው፡፡

ሶስተኛው ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ውይይት ማድረግ ናቸው፡፡እነዚህ ወደ ፖለቲካዊ መፍትሄ የሚወስዱ መንገዶች ናቸው፡፡

4-ከትጥቅ መፍታትና ጦር መሣሪያ ቁጥጥር ጋር የተገናኙ ጉዳዮች

ጦርነቱ ሁለት መደበኛ ወታደራዊ ሃይሎችን የፈጠረ ነው፡፡የትግራይ ሠራዊት ባለፉት አስር ወራት የሜካናይዝድ መሣሪያዎችን ጨምሮ በርካታ ትጥቆችን ማርኮ ታጥቋል፡፡ ታንክ፣መድፍ፣ሚሳኤልና ተሸከርካሪዎች ታጥቋል፡፡የትግራይ መከላከያ ሠራዊት ከጦርነቱ በፊት አልነበረም፡፡ትግራይ ላይ የተከፈተውን ጦርነት ለመመከት የተመሠረተ፣ጦርነቱ የወለደው ወታደራዊ ሃይል ነው፡፡አሁን ይህ ሠራዊት እየተዋጋ ያለው የትግራይ ሕዝብ የራስን መንግስት ከመመስረት ጀምሮ የራስን በራስ የማስተዳደር መብት ለማስጠበቅ ነው፡በዚህ ሂደት ውስጥ አሁን ያለው የዘር ማጥፋት ጦርነት ሊደገም የማይችል መሆኑን ማረጋገጥ ይፈልጋል።

የትግራይ መንግሥትና ሠራዊቱ የዐቢይ መንግሥት የአገሪቱን አንድነት ሰባብሮታል ከሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል፡፡ይህንን የተሳባበረ አንድነት ለመመለስ በሚመለከታቸው ወገኖች የሚደረግን ጥረት ግን አይቃወምም፡፡ በመሆኑም የሆነ የሽግግር ዘመን ተዘጋጅቶ የመልሶ ግንባታ ሥራዊች፣የወንጀል ተጠያቂነቶች፣ብሔራዊ የፖለቲካ ውይይቶች መካሄድ እንዳለባቸው የትግራይ መንግሥትና ሠራዊቱ ያምናሉ፡፡በመሆኑም የሽግግር ዘመኑ ሳያልቅ ትጥቅ ስለማስፈታት ማሰብ የማይቻል ነው፡፡የትግራይን ሠራዊት እጣፈንታ የሚወስነው በሽግግር ዘመኑ ውስጥ የሚሆነው ፖለቲካዊ ውጤት ነው፡፡እንዲያም ሆኖ ሥለ ጦር መሣሪያ ቁጥጥርና አስተዳደር መነጋገር ይቻላል፡፡


በአጠቃላይ የፀጥታው ምክር ቤት በትግራይ ጉዳይ ጣልቃ መግባት ከፈለገ ከየመን ስህተቱ መማር ይገባዋል፡፡የትግራዩ ጦርነት የዘር ማጥፋት ጦርነት ነው፡፡ተጋሩ እየተፋለሙ ያሉት ከዚህ የሕውልና አደጋ ለማምለጥ ነው፡፡በአስር ሺህ የሚቆጠሩ ንፁሃን በጥይትና በረሃብ ሞተዋል፡፡ተደፍረዋል፤ሁሉም ዓይነት የጦር ወንጀሎች ተፈጽመዋል፡፡ ተጋሩ የሃይማኖትም ሆነ የፖለቲካ አለያም ሌሎች ልዩነቶቻቸውን ትተው ራሳቸውን ለማዳን በትግራይ ሠራዊት ሥር ሆነው እየታገሉ ነው፡፡ በትግራይ ያለውን ጦርነት በፖለቲካዊ መፍትሔ ለመቋጨት የሚደረጉ ሙከራዎች ይህንን ተረድተው በጥንቃቄና በኃላፊነት መጓዝ አለባቸው።