ኣቶ ልደቱ ኣያሌው ለምን በኣማራ እና በትግራይ ህዝቦች የፀብ ትርክት መፈብረክ አስፈለገው?

ወደ ህወሓት መንደር ዳግም ብቅ ያለበት ምክንያትስ ምን ይሆን?

በ ተስፋኪሮስ ኣረፈ

እንደ መንደርደሪያ፡ ኣቶ ልደቱ እና የኣገር መፍረስ ጥሪ ደወል፡-

ኣቶ ልደቱ ከማህበራዊ መሰረታቸው ውጪ ሊያስደነግጥ የማይችለውን (ይልቅ ተስፋ ሊያሰንቅ የሚችልን) ኣጀንዳ በመምዘዝ ይታወቃል። የኢትዮጵያ መፍረስ የጋራ ስጋት ፣ ኢትዮጵያን ከመፍረስ መታደግም የጋራ ኣጀንዳ ኣይደሉም። እንዲያውም የኢትዮጵያ መፍረስ በበጎ ኣይን የሚያዩት እንዳሉ ለማወቅ ሩቅ ሳይኬድ ኣቶ ልደቱ ኣያሌው ከዳደ ደስታ ጋር TMH ላይ ባደረገው ቃለ መጠይቅ የጠቀሳቸው የኦነግ ኣመራር እንደ እማኝ መውሰድ ይቻላል፡፡

ይኸ የሆነበት ምክንያት የኢትዮጵያ መፍረስ የመነጠል ኪሳራ (separation cost) ይቀንሳል፣ የመጨፍለቅና የመስፋፋት ዓላማ ያነገቡ የፖለቲካ ሃይሎች ለእኩይ ኣላማቸው የሃገሪቱን ሰብኣዊ እና ቁሳዊ ሃብት ከመጠቀም ይርቃሉ ከሚል ምኞትና ስሌት ነው። ኣቶ ልደቱ ኣያሌው ባይሳካለትም `የመፍረስ የስጋት ኣደጋ ደወል ጥሪ የመዘዘው` የኣማራ የፖለቲካ ሃይሎችን በስጋት ኣስብርግጎ ለማነሳሳትና በኣጀንዳው ዙሪያ ለማሰለፍ ነበር።

ሆኖም ኣጀንዳው ኣቶ ልደቱን የባሰ ማህበራዊ መሰረት እና ሰሚ ኣልባ ኣደረገው እንጂ ያስደነገጠውና ያሰባሰበው ሃይል ኣልታየም። ለዛም ነው በህወሓት ኣንቀልባ ለመታዘል ዳግም የህወሓት በር ያንኳኳው ወይም ህወሓትን ለመታደግ ተልእኮ የወሰደው። የኣቶ ልደቱን ጭምብል የተጋለጠበት ጉዳይ ከመዳሰሳችን በፊት ግን ኣቶ ልደቱ ለምን የኣማራ እና የትግራይ ህዝብ በታሪክ ያልነበረ ጎናዊ ግጭት ውስጥ እንደገባ አስመስሎ ትርክት ፈብርኮ ማረጋብ ኣስፈለገው? የሚለውን እንይ።

ለዚህ ፅሁፍ መነሻ እና ግብኣት ኣቶ ልደቱ ‹‹ መስመር እዩ ሓይልና እስከ መቼ?›› የሚል መጣጥፍ በተለያዩ ሚዲያዎች ከተሰራጨ በኋላ፣ እርሱን ተከትሎ በርእዮት ሚድያ ከቴድሮስ ፀጋየ እንዲሁም በTMH ከዳደ ደስታ ጋር ያካሄዳቸው ቃለ መጠይቆች ተጠቅሜኣለሁ፡፡

1. ኣቶ ልደቱ የትግራይ ህዝብና ግዛት የመከፋፈል እርምጃ የኣማራ እና የትግራይ ህዝብ ጎናዊ ግጭት የወለደው ኣድርጎ ማቅረብ ለምን ፈለገው?

ሀ. የኣቶ ልደቱ የኣማራ የፖለቲካ ሃይሎችን ከተጠያቂነት የመታደግ ጥረቱና ኣላማ

የኣቶ ልደቱ ማህበራዊ መሰረት ኣማራ ነው። በፖለቲካ ጉዞውም የኣማራ ፖለቲካዊ ልሂቃን ወኪልና ኣርበኛ ሆኖ ቀርቦ ነበር። ነገር ግን ቅንጅት ውስጥ የተጣመሩ የፖለቲካ ድርጅቶች ለመዋሃድ ባደረጉት ጥረት በተጫወተው ኣፍራሽ ሚና በኣቶ ልደቱ ፖለቲካዊ ህይወት ላይ የማይጠገን ፖለቲካዊ ስብራት ፈጥሯል። ከዚህ ፖለቲካዊ ስብራቱ ለማንስራራት የኣማራ የፖለቲካ ሃይሎች በትግራይ ህዝብ ላይ የፈፀሙት የብሄር ፍጅት እና የብሄር ማፅዳት ክፉ ክዋኔ፣ እንዲሁም ብልፅግና የፈጠረላቸው እድል በመጠቀም በትግራይ ሉኣላዊ ግዛት የባእድ ኣስተዳደር መዘርጋታቸውን ማዳፈን ኣላማ ኣድርጎ ይዞታል።

ትግራይን የወረሩ እና በትግራይ ላይ ፍጅት የፈፀሙ ኣሰባስቦ እድል የፈጠረላቸው፣ የትግራይን ግዛት እና ህዝብ ከፋፍሎ ለኣማራ ተስፋፊዎች እንዲሁም ለሻዕቢያ (ህግዴፍ) ኣሳልፎ የሰጠው የኦሮሞ ሃይል ኣስኳል የሆነበት ብልፅግና ፓርቲ ነው። ሆኖም ከፍላጎት እና ከድርጊት ኣንፃር ከታየ በትግራይ ህዝብና ግዛት ላይ ጉዳት በማድረስ የኣማራ የፖለቲካ ሃይሎች በቀዳሚነት ይመደባሉ።

ከፖለቲካ ልሂቃን ኣንፃር ካየነዉም፣ ከትግራይ ወገን ያልቆመው የኣማራው የፖለቲካ ልሂቅ ነው። ከሰዎስቱ ዋና የህዝብ ፍጅት ፈፃሚዎች፣ የብሄር ማፅዳት ከዋኞች፣ የግዛት ወረራ ዘማቾች እና ፈፃሚዎች ማለትም፥ (1) የብልፅግና ኣስኳል ሃይል (የአሮሞ ፖለቲካዊ ልሂቅ)፣(2) የኣማራ የፖለቲካ ልሂቅ እና (3) ህግዴፍ (ሻዕቢያ) ማህብራዊ መሰረቶች ካስተዋልን የኦሮሞ ሊሂቃን እና በተለይ ኤርትራውያን ከትግራይ (ከሃቅ) ጋር ወገነው ቆመዋል፡፡

ኣቶ ልደቱ ደግሞ ሁኔታውን ለራሱ የፖለቲካ ኣላማ ለመጠቀም ሲል የኣማራ ፖለቲካዊ ልሂቃን የፈፀሙት የብሄር ፍጅት፣ የብሄር ማፅዳት እና የግዛት ማስፋፋት ሳያነሳ፤ ትችቱን በዋነኝነት በሻዕቢያ፣ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በብልፅግና ላይ ማድረጉን ቀጥሎበታል። የትግራይ ፖለቲካዊ ልሂቃንም በመጀመሪያ ኣካባቢ የልደቱን የብልጣብልጥነት ፖለቲካ ሳይገለጥላቸው ከትግራይ ጎን እንደ ቆመ ኣድርገው የመደረዳት ኣዝማሚያ ኣሳይተው ነበር፡፡ ከዳደ ደስታ ጋር ያደረገው ቃለ መጠይቅ ግን የኣቶ ልደቱ ጭምብል ላይጠገን ያጋለጠ ሆነዋል።

የህወሓት ኣንጃዎች ለፕሮፓጋንዳ እስከ ጠቀማቸው ድረስ ልደቱን ሊታገሱትና ሊጠቀሙበት ይሞክሩ ይሆናል (ዳደ ፍንጭ ስጥቷል)። ለ ህወሓት በነበረውና እያደሰው ባለው ስልታዊ ድጋፍ ምክንያት በበጎ ሊያዩት ይሞክሩ የነበሩት ገራገር የትግራይ የፖለቲካ ልሂቃን ግን ኣይነጥላቸው ይገልጥላቸዋልና የማይጠገን የመለያየት ምእራፍ ላይ መድረሳቸው ኣይቀርም።

ለ. ኣቶ ልደቱ እና የኣማራ እና በትግራይ ህዝቦች መካከል የግጭት ትርክት የመትከል ኣላማው

ኣቶ ልደቱ ብልፅግና፣ የኣማራ የፖለቲካ ሃይሎች እና ሻዕቢያ ተቀናጅተው የፈፀሙት ወረራ፣ የብሄር ፍጅት፣ የብሄር ማፅዳት እና የግዛትና ህዝብ በሃይል መቆጣጠር በኣማራ እና በትግራይ ህዝቦች መካከል የተፈጠረ ግጭት ኣድርጎ ለመሳል ይጥራል። ይኸ የኣማራ ፖለቲካዊ ልሂቃን የትግራይን ህዝብ እና ግዛት ከፋፍሎ፣ የትግራይን ፖለቲካዊ ተሳትፎ እና የስልጣን ፉክክር ብቃት የማዳከም፣ የሸዋ የፖለቲካ ውርስ የወለደው የግዛት ማስፋፋት ኣጀንዳን የኣማራ ህዝብ ኣጀንዳ እንደሆነ ኣድርጎ ለማቅረብ ነው።

ለዚህ እንደ ማስረጃ መቅረብ የሚችሉ፡-

ኣንደኛ፡- ኣቶ ልደቱ ደጋግሞ በትግራይ እና በኣማራ ህዝቦች መካከል በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ጎናዊ ማህበረሰባዊ ግጭት (horizontal communal conflict) እንዳጋጠመ ይገልፃል። ነገር ግን በትግራይ ላይ ወረራ ሲፈፀም ከታሪክ የተለየ በኣማራ እና በትግራይ ህዝቦች መካከል የተፈጠረ ጎናዊ ማህበረሰባዊ ግጭት ኣልተፈጠረም። በፖለቲከኞች የተቀሰቀሰ፣ የተደራጀ፣ የታጠቀ እና የተመራ ታጣቂ እንጂ የኣማራ ህዝብ እንደ ማህበረሰብ ሆ ብሎ በትግራይ ላይ ኣልዘመተም፣ ወረራ ኣልፈፀመም። በብልፅግና እና በኣማራ ፖለቲካዊ ልሂቃ ሃይሎች ተገድቦ እንጂ ከወረራው በኋላም ማህበራዊ ግንኙነቱን በመሰረታዊነት ኣልተቋረጠም።

ሁለተኛ፥ በዘመናችን ያጋጠመው ወረራ እና የብሄር ፍጅት በኣፄ ምኒልክ፣ በኣፄ ሃይለ ስላሴ እና በደርግ ዘመነ መንግስታት ከተፈፀመው የተለየ ኣይደለም። ኣፄ ምኒልክ በትግራይ ላይ ባካሄዱት ዘመቻ ከፊታቸው ያገኙት በፆታው ወንድ የሆነ የትግራይ ሰው ሁሉ ተሰልቧል። ቤቶች እሳት እየተሰደደባቸው ተቃጥለዋል። ገዳማት ተዘርፈዋል (የተፈጠረው ነውር ለማፅዳት ጉዳዩ በተኣምረ ማርያም ውስጥ ሳይቀር እንዲፃፍ ተደርጓል)።

የቐዳማይ ወያነ ኣመፅ ተከትሎ በኣፄ ሃይለ ስላሴ ዘመነ መንግስት ገበያዎች በጦር ኣውሮፕላኖች ተደብድቧል። በገበሬ ቤት ወታደሮች ተመድበው ብዙ ግፍ እንዲያደርሱ እና ጥሪቱን እንዲያራቁቱ ተደርጓል። ህዝብ ከመሬቱ ተፈናቅሏል። መሬቱ ተቀምቷል፣ በሰሜን በታሪክ የማይታወቀውን ቀላድ የሚል የመሬት ኣስተዳደር ስርኣት ተዘርግቷል። እናቶች እና ህፃናት ከእነ ሂወታቸው በእሳት ላይ ተጨምረዋል።

በደርግ ጊዜም በኣፄ ሃይለ ስላሴ ዘመነ መንግስት እንደተደረገው በገበያ ቀን ህዝብ ተጭፍጭፏል። የ ብልፅግና መንግስት እያደረገው እንዳለ፣ ህዝብ እርዳታ እንዳይደርሰው በማድረግ በረሃብ እንዲሞት ተደርጓል። ኣሳን ለመግደል ውሃውን ማድረቅ. . .“ በሚል የሚታወቀው የጆኖሳደሮች ፖለቲካዊ ፖሊሲ የትግራይ ህዝብ በግድ ወደ ሰፈራ እንዲጓዝ ተደርጓል። ኣፈፃፀሙ በዋሉበት መግፈፍ ስለነበር ቤተ ሰብ ተበታትኖ ማህበራዊ ቀውስ ኣጋጥሟል። በኣጠቃላይ ከጦርነት፣ከረሃብና ከሰፈራ ጋር በተያያዘ ከ500,000 በላይ ህዝብ ለሞት ተዳርጓል።

በእነዚህ መንግስታትም እንደ አሁኑ የልፅግና ዘመን ህዝብ በትግራይ ላይ እንዲዘምት ተቀስቅሷል፣ ተደራጅቷል፣ ታጥቋል፣ ዘምቷል። ነገር ግን በትግራይ እና በሚጎራበተው የኣማራ ህዝብ መካከል ጎናዊ ማህበረሰባዊ ግጭት ኣልተከሰተምል።

ኣቶ ልደቱ የታሪክ ተማሪ ስለሆነ እነዚህ ፍፃሜዎች ለማወቅ ኣይገድበውም። ነገር ግን የኣማራ ፖለቲካዊ ልሂቃን ትግራይን ከፋፍሎ የማዳከም የፖለቲካ ውርስ የኣማራ ህዝብ ጉዳይ እንደሆነ ኣድርጎ ለማቅረብ ስለ ሚፈልግ በኣማራ እና በትግራይ ህዝቦች መካከል የተለየ ክስተት እንዳጋጠመ ኣድርጎ ለመተረክ ነው ፍላጎቱና፣ ለፖለቲካዊ ግቡ እስካ ገለገለው ድረስ ለሃቅና ለህዝቦች ግንኙነት ሲጨነቅ አልታየም።

ሐ. ኣቶ ልደቱ የኣማራ የፖለቲካ ልሂቃን የግዛት ማስፋፋት ኣጀንዳ ለመጋራት የፈበረከው ትርክት

ትግራይ የሸዋ ስርወ መንግስት ነገስታት በ20ኛው ክፍለ ዘመን መግቢያ ወይም በ19ኛው ክፍለ ዘን መገባደጃ የማእከላይ መንግስት ስልጣን እስኪቆጣጠሩ ድረስ ግዛቷ የታወቀ እና በተለይ የኣማራ ህዝብ በቀደምት ነዋሪነት ይሁን በጭፍለቃ (assimilation) ቋንቋው በተስፋፋባቸው ኣጎራባች የሆኑት የኣማራ ኣገር (ወሎ/ደቡብ ወሎ)፣ ኣንጎት/የጁ (ሰሜን ወሎ) እና በጌምድር (ጎንደር) ድንበሯ ታውቆ እና ተከብሮ በሰላም ትኖር ነበር። የትግራይ ታሪካዊ ኣስተዳዳራዊ ባለቤትነት እና የህዝቡ ብሄራዊ ኣንድነት መለወጥ የጀመረው የሸዋ ነገስታት የማእከላይ መንግስት ስልጣን ከተቆጣጠሩ ጀምሮ ነው። በየዘመነ መንግስታቱ የሆነውን ዘርዘር ኣድርገን እንመልከት፦

ኣንደኛ፡ የኣፄ ምኒልክ ዘመነ መንግስት

የኣፄ የሃንስን መስዋእት ተከትሎ ንጉስ ምኒልክ ያለ ጠንካራ ተቀናቃኝ የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት ለመሆን ወደ ጣሊያን መንግስት የፃፉት ደብዳቤ ‹‹የትግራይ ሰዎች በባህር በኩል መሳሪያ በማስገባት ተጠናክረው ስልጣን ይገባናል እንዳይሉ የጦር መሪዎችህ ኣስመራን በፍጥነት እንዲቆጣጠሩ ትእዛዝ ስጣቸው›› የሚል ነበር።

ይኸንን ደብዳቤ ሁለት ወር ባልመላው ጊዜ በውጫሌ ውል ኣንቀፅ 3 የትግራይ ንኡስ ግዛት የነበረውና በባህር ነጋሲ ማእረግ የሚተዳደረው ኣካባቢ (የጣልያ መንግስት ኤርትራ የሚል ኣዲስ ስም የሰጠው) ለጣሊያን መንግስት ኣሳልፈው ሰጡት። በውጫሌ ውል ሳይካተቱ ከትግራይ ጋር ቀርተው የነበሩት ኣከለ ጉዛይ፣ ሰንዓፈ፣ በዓሰብ በኩል እና በምእራብ (ሱዳን ኣስተዳዳሪው እንግሊዝ መንግስትና ለጣልያን) ደግሞ ከዓድዋ ውጊያ ማግስት ለጣሊያን ተላልፈው ተሰጡ። ኣፄ ምኒልክ በዚህ ብቻ ኣላበቁም፣ የቀረችውን ትግራይ ከኣንድ ኣስተዳዳር ኣውጥተው በኣራት ገዢዎች እንድትተዳደር ነበር ያደረጉት።

ሁለተኛ፡ የኣፄ ሃይለ ስላሴ ዘመነ መንግስት

ኣፄ ሃይለ ስላሴ የኣፄ ምኒልክን ትግራይን ከፋፍሎ የማዳከም፣ ከፖለቲካ ተሳትፎ እና ፉክክር ውጪ የማድረግ ውርስ ተከትለው መጀመሪያ የውስጥ ኣስተዳደርዋን ለተለያዩ መሳፍንት እና መኳንት በመስጠት የጠቅላይ ገዢነትን (ኣስተዳዳሪነትን) ስልጣን ኣጠፉ። በመቀጠል በ1938 ዓ.ም ምእራብ ትግራይን (ሑመራ፣ ወልቃይት፣ ፀገደ፣ ዋልድባ፣ ፀለምቲ፣ ስሜን) ወደ በጌምድር ቀላቀሉት። በ1949 ዓ.ም ደግሞ ከራያ ዓዘቦ ኣውራጃ ሁለት ወረዳዎች (ቆቦ እና ኣላማጣ) ቆርሰው ወደ ወሎ ጠቅላይ ግዛት ኣስገቡት።

የወሎ እና የበጌምድር የበላይ ጠባቂ የነበሩት (በተለይ የእናታቸው ኣገር ወሎን ዓፋር እንዳለ እና የትግራይ ግዛት ኣካል የነበሩት ላስታና ዋግን ጭምር ኣካተው ትልቅ ጠቅላይ ግዛት ያደረጉት) ኣልጋ ወራሽ ኣስፋወሰን ሃይለ ስላሴ ነበሩ። ወሎ እና በጌምድር ጠቅላይ ግዛቶች በተናጠል ሲገዙ የነበሩት ደግሞ የሸዋ መሳፍንት እና መኳንንት ነበሩ። ለምሳሌ ምእራብ ትግራይን ወደ በጌምድር የቀላቀሉት በ1936 ዓ.ም የበጌምድር ኣስተዳዳሪ ሆነው የተሸሙት ራስ እምሩ ነበሩ። ለዚህም ነው የበጌምድር እና የወሎ ነዋሪዎች በትግራይ ግዛቶች የይገባናል ጥያቄ ኣንስተው የማያውቁት እና ወደ ግጭት የማያመሩት።

የትግራይ ህዝብ ኣስተዳደራዊ ኣንድነትን የመመለስ የትግል መነሻ የሆኑት እነዚህ የሸዋ ነገስታ እርምጃዎች ናቸው። ጉዳዩ ኣቶ ልደቱ እንደሚለው በ1987 ዓ.ም የተተከለው ህገ መንግስት ወይም በ1984 ዓ.ም የተከናወነው ኣከላለል የፈጠረው ሳይሆን ታሪካዊ መነሻ እና ሂደት ኣለው።

የሸዋ ነገስታት የትግራይን ግዛት ቆርሰው ወደ ወሎ እና በጌምድር ሲጨምሩ በኣማራ እና በትግራይ ህዝቦች መካከል ጎናዊ ማህበራዊ ግጭት ኣላጋጠመም። የትግራይ ህዝብ ግዛቱን እና ብሄራዊ ኣንድነቱን ለማስመለስ ባደረገው ትግል የሸዋ ነገስታት እንጂ የኣማራ ህዝብን ተጠያቂ ኣላደረገም። ትግሉም ስርኣቱ ላይ ያነጣጠረ ነበር። የኣማራ ህዝብም የተወሰዱባችሁ ግዛቶች ለማስመለስ ለምን ትታገላላቸው ኣላለም። ይልቅ የፀረ ደርግ ትግሉን ተቀላቀለ።

በ1984 ዓ.ም በተደረገው ኣከላለልም በኣማራ እና በትግራይ ኣጎራባች ህዝቦች መካከል ግጭት ኣልተፈጠረም። የትግራይ ህዝብን ከታሪካዊ ባለቤትነት ኣንፃር በወሎ እና በጎንደር የቀሩት ግዛቶች ቢኖሩም ህወሓትን ተጠያቂ ከማድረግ ውጪ ወደ ግጭት ኣላመራም። በፖለቲካ የተደራጁ ሃይሎች ካልሆነ በስተቀር የጎንደር እና የወሎ ነዋሪም የይገባኛል ጥያቄ ኣነስቶ ኣያውቅም። ይልቅ በተለይ በወሎ ውስጥ ያሉ ነዋሪዎች ተደጋጋሚ ጥያቄ ለትግራይ ኣስተዳዳሪዎች እጀንዳ እንዲያደርጉት ኣቀርበዋል። ከወሎ ጋር የቀረችው ኣንዲት ወረዳ (ቆቦ) ስለሆነች ህዝቡ ወደ ጥንት ኣስተዳደሩ ወደ ራያ ዓዘቦ (ትግራይ) መመለስ ፍላጎት ኣለው።

በምእራብ ትግራይ በኩል ህወሓት ብኣዴንን ለማዳን የግጨው ጉዳይን የህዝብ ጥያቄ ኣስመስለው ለማቅረብና ለመፍታት በሞከሩበት ጊዜ ህዝቡ ጥያቄ እንዳልነበረውና እንዳያጋጩት ግን ስጋት እንዳደረበት ፊት ለፊት ገልፆላቸው ነበር። ይኸ በምስልና በድምፅ የተላለፈ ሃቅ ነው። የትግራይ ኣጎራባች ህዝብ የድንበር ጥያቄ ኣልነበረውም በሰላም ይኖር ነበር። ከዛ በኋላም ማህበረሰባዊ ግጭት ኣላስከተለም።

ኣቶ ልደቱ የታሪክ ተማሪ እንደመሆኑ መጠን ከዚህ የተለየ ማስረጃ ካለው እንዲያቀርብ ይበረታታል። እንደማያመጣ እና ሃቅ እያዛባ እንዲሁም እየፈበረከ የሚተርክ መሆኑ ቢታወቅም፣ በማስረጃ የመከራከር ልምድ ለማዳበር ያህል ማስረጃ ይዞ እንዲቀርብ እጋብዘዋለሁ። በፅሁፍም ይሁን በሚድያ ቀጥታ ክርክር ለመቅረብም ዝግጁ ነኝ።

ሶስተኛ፡ ኣቶ ልደቱ ከህገ መንግስታዊ ስርኣትና ኣሰራር ውጪ ይፈታ የሚል ሙግት ማቀረብ ፈለገ?

ኣቶ ልደቱ ከዳደ ደስታ ጋር ባደረገው ውይይት የፌዴራል ህገ መንግስት ባልቀበለውም እገዛበታለሁ ብሏል። ዳደ ደስታ ከኣቶ ልደቱ ጋር ያደረገው ውይይት ከጠበቅኩት ኣቋም በታች ነበር። ከዳደ ጋር ያን ያህል ትውውቅ ባይኖረኝም የተደራጀ ሃሳብ ያለው ሰው ኣድርጌ እቆጥረው ነበር። ሆኖም ከኣቅም ማነስ የተነሳ ኣቶ ልደቱን ያለ ልጓም እንዲጋልብ እድል ፈጥሮለታል። ነገር ግን ኣላማው ልደቱ ለወደፊቱ ህወሓትን በሚጠቅም መልኩ ለማሰራት ከትግራይ ፖለቲካዊ ማህበረሰብ (ኣገላለፁ ከልሂቅ ሳይሻል ኣይቀርም) ለማስታረቅ ይሆናል ብየ በጠረጠሩኩት ኣግባብ፣ በብልፅግና እና በኣማራ ተስፋፊ ፖለቲከኞች ቁጥጥር ስር ያሉ የትራይ ንኡስ ግዛቶች እና ህዝብ ኣስመልከቶ ከህገ መንግስት ኣንፃር ለኣቶ ልደቱ ጥያቄ ቀረበለት።

ኣቶ ልደቱ ከጥያቄ ለመሸሽና ለማምለጥ ብዙ ሙከራ ኣደረገ። ነገር ግን ዳደ ጉዳዩን ኣጠንክሮ እና ደጋግሞ በማቅረቡ የኣቶ ልደቱ ጭምብል ተጋለጠ። ድመት መልኩሳ ኣመልዋን ኣትረሳ . . . እንዲሉ ባላምንበትም እገዛበታለሁ ባለው ህገ መንግስት መሰረት በሃይል የተያዘው የትግራይ ህዝብና መሬት ወደ ትግራይ ይመለስ ማለትን እንደማይቀበለው ኣረጋገጠ። ከህወሓት ኣንጃዎች ሊጫወተው ያሰበው የብልጣብልጠነት ፖለቲካ ጭምብሉ ተጋለጠ (ያው ለኣንጃው እስከ ጠቀመ ከልደቱ ጋር እንደሚቀጥሉ ዳደ ደስታ ፍንጭ ሰጥትዋል።

ኣቶ ልደቱ ህገ መንግስቱ በሃይል መጣስ የለበትም እንዲሁም የትግራይ ግዛት status quo ante ይጠበቅ ማለትን ያልመረጠው ለምንድ ነው?

ኣንደኛ፡ ኣቶ ልደቱ የትግራይን ህዝብና ግዛት በመከፋፈል የማዳከም በውርስ ፖለቲካ የሚነዳው የኣማራ የፖለቲካ ልሂቃን የግዛት ማስፋፈት ኣጀንዳ ይደግፋል።

ኣቶ ልደቱ የጉዳዩ ታሪካዊ ሂደቶች ሆን ብሎ በመዝለል፣ የወልቃይት እና የራያ ጉዳይ የ1987 ዓ.ም ህገ መንግስት ወይም የ1984 ዓ.ም ክልላዊ ኣደረጃጀት የፈጠረው ነው በማለት ደምድሟል። ይኸ ደግሞ ለግዛት ማስፋፋት ኣላማው ሃቆችን እየተወ እና ሃቆችን እየፈበረከ እንዲሁም እያዛባ ነው።

ሁለት፡ ኣቶ ልደቱ ብልፅግና ትግራይን ከፋፍሎ የማዳከም የሸዋ ነገስታት ፖለቲካ ተከትሎ የትግራይ ግዛትና ህዝብ ለኣማራ ተስፋፊዎች የሰጠበት ሁኔታ እንዳለ እንዲጠበቅለት (ነባራዊ ሃቅ ሆኖ እንዲቀጥል) ይፈልጋል። ባላምንበትም እገዛበታለሁያለውን ህገ መንግስት በትግራይ ግዛት ላይ ሲሆን ግን ሸብረክ ያለው ያለ ምክንያት ሳይሆን ብልፅግና ለኣማራ ተስፋፊ ፖለቲከኞች የፈጠረላቸው እድል ለመጠቀም ነው።

እዚህ ላይ የፌዴራል ህገ መንግስት የትግራይን ኣስተዳደራዊ ድንበር ኣያውቅለትም የሚል ሙግት ለመምዘዝ ሞክሯል። በዚህ መሰረት ኣቶ ልደቱ ሶስት ህፀፆችን ፈፅሟል።

ሀ. ክልሎች የተዋቀሩት የፌዴራል የሽግግር መንግስት በወጣው ኣዋጅ በ1984 ዓ.ም ከህገ መንግስቱ መደንገግ በፊት ነው። የፌዴራል መንግስት የትግራይን ኣስተዳደራዊ ወሰን ያውቀዋል ብቻ ሳይሆን ራሱ ነው የቀረፀው።

ለ. በ1987 ዓ.ም ህገ መንገስቱ ሲፀድቅ በ1984 ዓ.ም በኣዋጅ የተቋቋመች ትግራይን እውቅና ሰጥቶ ነው የፌዴሬሽኑ ኣባል ያደረጋት። ትግራይን ኣውቆ በህገ መንግስት ሲያካትት ከእነ ኣስተዳደራዊ ወሰኗ ነው።

ሐ. የፌዴራል መንግስት ግዛት (territory) ስለ ሌለው የክልሎች ኣስተዳደራዊ ወሰን የኢትዮጵያ ሉኣላዊ ግዛት እንደሆነ ይደነግጋል። ክልሎች ፌዴሬሽኑን በጋራ ሲፈጥሩት ኣስተዳደራዊ ወሰናቸው ታውቆና ይዘው ነው።

ሶስት፡ የኣማራ ተስፋፊ ፖለቲከኞች የውርስ ፖለቲካ እንጂ የታሪካዊ ባለቤትነት (ኣስተዳዳረዊ ታሪክ)፣ የህዝብ ብዛትና ማንነት (demography) እና ህጋዊ ድጋፋ እንደሌላቸው ያውቃሉ። ስለዚህ ልደቱም እንደ ኣንድ የግዛት ተስፋፊነት እና ትግራይን ከፋሎ የማዳከም የውርስ ፖለቲካ ተጋሪ ፖለቲከኛ ታሪክ፣ ማንነት እና ህግ ስለማይደግፉት የወልቃይት እና የራያ ጉዳይ ከህገ መንግስታዊ ድንጋጌ እና ኣስራር ውጪ (extra constituional) መስተናገድ ኣለበት የሚል የብልጣብልጠነት ሙግት ለመምዘዝ ተገደደ።

2. ኣቶ ልደቱ ወደ ህወሓት ጉዳይ እና መንደር ዳግሞ ብቅ ያለበት ምክንያት

በ1997 ዓ.ም ከቅንጅት ኣባል ድርጅቶች እንዲሁም ከራሱ ድርጅት ኢዴፓ ኣመራር ጋር የፈጠረው ውዝግብ ተከትሎ ልደቱ የኣግላይ ጠቅላዩ የፖለቲካ ጎራ ኣይንህ ላፈር ብሎት ነበር። ይኸን ተከትሎ እርሱና ፓርቲው ኣስቸጋሪ ጊዜው እንዴት መሻገር እንደሚችሉ ገምግመው መወጣጫ መንገድ ኣበጁ።

በግምገማቸው መሰረት የተቃውሞ ጎራው እና ኢህኣዴግ ሊያጠፏቸው እንደሚችሉ ደመደሙ። ከሁለቱም ግን ለድርጅታዊ ህልውናቸው ወሳኝ ሚና የሚጫወተው ኢህኣዴግን በኣደገኝነቱ በኣደኛነት መደቡት። ከዚህ የተነሳ ኩፉን ጊዜ ከኢህኣዴግ ጋር ተመሳስለን እንለፈው፣ ከኢህኣዴግ ጋር መላተም ወይም መጋጨት እናቁም፣ ወዘተ የሚሉ ውሳኔችን ኣሳለፉ። ለዚህ ስልት ደግሞ ሶስተኛው መንገድ የሚል ስያሜ ሰጡት። ይህ ውሳኔ እና ስልት የሚከተሉትን ውጤቶች አስገኙ።

ኣንደኛ፡ ኢዴፓ ከፖለቲካ ድርጅት ወደ የጥናትና የምርምር ተቋም (Think Tank) ወረደ

ኣሁንም ኣቶ ልደቱ በሚድያ ደጋግሞ እንደሚያንፀባርቀው ተቋማዊና ተፊካከሪ የፖለቲካ ድርጅት ሆነው ሲያበቁ ኢህኣዴግን በምክንያት እንደግፋለን፣ በምክንያት እንቃወማለን ማለትን ጀመሩ። እንግዲህ የፖለቲካ ድርጅት ጥምረት ካልፈጠረ የተፎካካሪውን የፖለቲካ ድርጅት ኣቋምና ስኬት እንዲደግፍ ኣይጠበቅም። ጠንካራ እና ደካማ ጎኑን ኣውጥቶ ምክረ ሃሳብ ወይም መፍትሄ የመሰንዘር የጥናትና የምርምር ተቋማት ወይም የገልለተኛ ምሁራን ሚና ነው።

ኢህኣዴግ ደግሞ የኢዴፓን ኣካሄድ ተመችቶት ፖለቲካ ማለት የእነ ልደቱ ነው ማለትን ተያያዘው። በተለይ የህወሓት ኣባላት ወይም በኣጠቃላይ የትግራይ ተወላጆች ለኣቶ ልደቱ በጎ ስሜት ማሳደር ጀመሩ። መፈናፈኛ ኣልነበራቸውምና ለጊዜው እንቅስቃሲያችሁን ከመገደብ (hibernate ከማድረግ) ይልቅ ድርጅታችሁን ለማንሰራራት የምትመክሩት ማህበራዊ መሰረታችሁ የት ሊሆን ነው? የሚል ጥያቄ በወቅቱ ስሰነዝርባቸው፤ ትግራይ የሚል ነበር መልሳቸው። የትግራይ ወጣት እኮ ለህወሓት/ኢህኣዴግ ያሳያችሁት የተለሳለሰ ኣቀራረብ ነው በበጎ የሚያያችሁ እንጂ የ ፖለቲካ ድጋፍ ኣይደለም የሚል ኣስተያየት ነበር የሰጥኋቸው። ትግራይ ውስጥ እግር ለመትከል ሙከራ ቢያደርጉም እንዳልኩት ኣልተሳካላቸውም። በጣት የሚቆጠሩ የማህበራዊ ሚድያ ኣክቲቪስቶችም ኣብረው መቀጠል ኣልቻሉም።

ሁለተኛ፡- በትግራይ የኢዴፓ ወኪል ወይም መሪ የነበረው ኣቶ ተክሌ በቀለ ህወሓት/ኢህኣዴግ የማይታገል ፖለቲካ ኣልቀበልም በማለት ከድርጅቱ ለቀቀ፡፡

ሶስተኛ፡ ህወሓት/ኢህኣዴግ ከኢዴፓ የሚጠብቀውን ሲያጣ ያኮርፍ ጀመር። እንደ ኣብነት፡- የሽብር ኣዋጅ ሲደነገግ ኣቶ ልደቱ ኣምርሮ በመቀወሙ ህወሓት/ኢህኣዴግ የኢዴፓን ኣመራር ኣኮረፋቸው።

ኣራተኛ፡ ሶሰትኛ መንግድ በስትራቴጂ የታገዘ ስላልሆነ ኢዴፓን ሩቅ ሊያስኬደው ኣልቻለም።

ኣቶ ልደቱ ህወሓቶች ርእዮተ ኣለማቸው እንዲቀይሩ ቢወተውትም እርሱ ራሱ የፖለቲካ ተሳትፎ ከጀመረበት ጀምሮ ርእዮተ ኣለሙን ኣልቀየረም። እያደረገ ያለው ስልታዊ መተጣጠፍ እንጂ ስትራቴጂካዊ ክለሳ ኣይደለም። ህወሓትን ከመስመር እዩ ሓይልና ወደ ዴሞክራሲ እዩ ሓይልና ተሸገሩ የሚለው ልደቱ፣ ሳስበው የፕሮግራም ይዘት ለውጥ ሳታደርጉ በኣቀራረብና በቃላት ኣጠቃቀም ተጣጠፉ ለማለት ይመስላል። ይህ ስልት የትግራይ ወጣት የለውጥ ኣካል ተድርጎ እንዲቆጠርና ከህወሓት እንዳይርቅ ለመያዝ እንዲያገለግለው እንጂ ህወሓት ርእዮተ ኣለሙ ሳይለውጥ ዴሞክራሲን ሊዘምር እንደማችል ይጠፋዋል ብየ ኣልጠብቅም።

እነ ኣቶ ልደቱ ሶስተኛ መንገድ ሲሉ ይኸንን ኣስተሳሰብ ለማስተናገድ በፕሮግራማቸው ላይ ያደረጉት ለውጥ ኣልነበረም። ፕሮግራማቸው ቅንጅት ይጠቀምበት ነበረው የበፊቱ ፕሮግራም ነው።

እግረ መንገዴን ለመጥቀስ ያህል ግን ኣቶ ልደቱ በሓርነት/ኣርነት እና በነፃነት (Liberation / Independence) ያለው ልዩነት በቅጡ ሳይረዳው ህወሓትን ስሙን ሳይቀይር ‹‹ በነፃነት›› የቀጠለ በማለት ተችቶታል። ‹‹ ትምክህት፣ ጠባብነት›› የ66ቱ ትውልድ ከማርክሲዝም ሌኒኒዝም ስነ ሃሳብ የወሰዳቸው መሆኑ እየታወቀ ለህወሓት ለማሸከም መሞከሩም ኣግባብ ኣይደለም።

የደርግ ህገ መንግስት ራሱ ‹‹ትምክህት እና ጠባብነት›› እንታገላለን ይላል። ህወሓትን የጥላቻ ምንጭ ማድረጉም ኣግባብ ኣይደለም። ኣሳሳች ነው። የህወሓት ፖለቲካዊ ፍረጃ ከርእዮተ ኣለም የሚመነጭ ነው። በጦብያ ውስጥ ጥላቻ፣ የፖለቲካ ባላንጣነትና ጅምላ ፍረጃ የጀመሩት የሸዋ ነገስታት ናቸው። ኣቶ ልደቱ የኣፈ ቀይሳር ኣፈወርቅ ገብረየሱስን መፅሃፍ ኣላነበበም ተብሎ ኣጠበቅም። ከ20ኛው ክፍለ ዘመን በፊት በሊሂቃን መካከል የስልጣን ፉክክር እንጂ ብሄር (ዘር) ቆጥሮ መፈረጅና ማጥቃት የተለመደ ኣልነበረም። በተለይ በትግራይ፣ በኣገው እና በኣማራ መካከል። ኣቶ ልደቱ ራሱ ከጅምላ ፍረጃ ያልተላቀቀ ወይም የሸዋ ፖለቲካዊ ባህል ተፅእኖ እንዳለበት የሚጠቁመው ለኣቦይ ስብሓት ለልጆቻችሁ ኣገር ኣትተውላቸውም እንዳላቸው ተናግሯል። ደምና ኣጥንት ተቆጥሮ የኣቦይ ስብሓት ልጆ (በኣውድ ከታየ ደግሞ የትግራይ) ልጆች ዋጋ እንከፍላለን ማለት ነው። የሆነውም እርሱ ነው።

ኣምስተኛ፡ ኣቶ ልደቱ ህወሓትን ለመታደግ የመጣበት ሁለት ምክንያቶች ኣሉት

ሀ. በትግራይ እና በህወሓት ላይ የተፈፀመው ነገር ኣመንጪዎቹ እነርሱ ቢሆኑም፣ የኢህዴን/ብኣዴን መስራቾች ህወሓት ከፖለቲካዊ ምህዳሩ ከጠፋ ኢትዮጵያ ትፈርሳለች የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል ይባላል። በተለይ በህወሓት ኣመራር ውስጥ የተፈጠረው መሳሳብ እና የስልጣን ፉክክር ሳያሳስባቸው ኣልቀረም። ኣቶ ልደቱም የዚህ ስጋትና ኢትዮጵያን ለመታደግ ህወሓትን የማዳን ኣጀንዳ ተጋሪ ሆኖ ነው ‹‹ በምክንያት የመደገፍ እና በምክንያት የመቃዎም›› የቲንክ ታንክ ወይም ገለልተኛ ምሁራን ባርኔጣው ከወደቀበት ኣነስቶ ተላብሶ እየቀረበ ያለው።

ለ. የኢህዴን/ብኣዴን መስራቾች ኣይደለም የትግራይ ወጣት ጋር ሊቀርቡ የህወሓት ጓዶቻቸው ለማግኘትም በጣም ከብዷቸዋል። ነገር ግን የሚገናኙበትና የሚመክሩበት መንገድ ኣያጡም። ስለዚህ ኣቶ ልደቱ የመጣው በዋኝነት በህወሓት እና በትግራይ ፖለቲካ ማህበረሰብ የተፈጠረውን መራራቅ ለመጠገን ነው። ህወሓት የፖሊት ቢሮ እና የማእከላይ ኮሚቴ ግምገማ ባጠናቀቀት ሁኔታ የኣቶ ልደቱ የመገምገሚያ ነጥቦች ዋጋ ኣይኖራቸውም። ለኔ ዋነኛ ነጥብ ህወሓት ከትግራይ ፖለቲካዊ ማህበረሰብ ጋር ተቀራቦ ይገምግም ያለው ነው።

በመጨረሻም ልደቱ በቃለ መጠይቆቹ ካላቸው እየተወሰኑ ነጥቦች ላክል፣ በተለይ በኢትዮጵያ ሃገረ መንግስት ግንባታ ሂደት የትግራይ ሚና በሚመለከት፣

ኣቶ ልደቱ ትግራይ በኢትዮጵያ ሃገረ መንግስት ግንባታ የነበራት ሚና ወሳኝ (core) እንደነበር ገልፅዋል። ልክ ነው ትግራይ የኢትጵያ ሃገረ መንግስት ጥንስስ (nucleus) እንዲሁም እንደ core state እና እንደ ክልል ለክርስቲያናዊ ኣፄኣዊ ግዛት (Christian Empire) ግንባታ ወሳኝ ሚና ተጫውታለች። ነገር ግን ኣቶ ልደቱ የሳተው ወይም ሆን ብሎ የዘለለዉ ጉዳይ ከ1882 ዓ.ም ጀምሮ ትግራይ ከኢትዮጵያ ጋር የነበራት ግንኙነት የኣበርክቶ ሳይሆን የትግል ነው።

የሸዋ ነገስታት ኣፄኣዊ ክርስቲያናዊ ግዛቱን ወደ ሃገረ መንግስት ግንባታ ሲቀይሩት በኣማራ ክርስቲያን ላይ ስላቆሙት የትግራይ ፖለቲካዊ ልሂቃን ከቤተ መንግስት የተገለሉ ባይተዋር ብቻ ሳይሆን ተገዳዳሪ ስብእና እንዳይገነቡ ለጥቃት ተጋልጠዋል። ታሪካቸው ተዛብቷል። የትግራይ ሃይል ለኣስተዳደራዊ ኣንድነትና ኣስተዳደራዊ ነፃነት ከኢትዮጵያ ጋር ወደ ግጥሚያ ገብቷል። ከ1882 እስከ 1983 ዓ.ም በኢትዮጵያ እና በትግራይ መካከል የነበረው ግንኙነት የትግል ነው። ኣሁንም እንደ ዘመነ የሸዋ ነገስታትና መንግስታት ብልፅግና ወደ ስልጣን ከወጣ ጀምሮ ከኢትዮጵያ ጋር ወደ የትግል ግንኙነት ከገባን ይኸው ኣምስት ኣመታት ደፈንን።

ልደቱ ኣሁን የተፈጠረው ጥላቻ በህወሓት/ኢህኣዴግ ፕሮፓጋንዳ ነው ሲል ይደጋግማል፣ ራሱን ከተጠያቂነት ለማዳን ካልሆነ በስተቀር የጥላቻ፣ የጅምላ ፍረጃ እና የባላንጣነት ፖለቲካ በመንዛት በዋነኝነት ትውልዱን የመረዙት የግል ጋዜጦችና ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ናቸው። የግል ጋዜጦች በትግራይ ህዝብ ላይ የፃፉት ጥላቻ እኮ በታሪክ ሰነድነትና የምርምር ህትመቶች ጭምር የተቀመጠ ነው። የእነ ጃዋር መሓመድ የቶላና-ሓጎስ ትርክት የተጫወተው ሚናም ቀላል እንዳልሆነ ሳንረሳ ማለቴ ነው።

በደርግ ዘመነ መንግስት ኣዲስ ኣበባ ውስጥ ህዝብ በየቀበሌው ተሰብስቦ የፍየል ወጠጤ እየተዘፈነለት በየመንደራችን ካሉት የትግራይ ተወላጆች መግደል እንጀምር የሚለውን እንደ ኣጀንዳ መወያያ ሆኖ እንደነበር በፅሁፌ ሳላወሳ ባልፉ ታሪኩን ያልተሟላ ያደርጓል።

ኣመሰግናለሁ።