‘የካቲት 11 – ድንቅ ታሪካዊት ዕለት!’

በ ፀጋዝአብ ለምለም ተስፋይ

የትግራይ ሕዝብ እንደማንኛውም የዓለም ሕዝብ የራሱ ኹለንተናዊ (ማህበራዊ፣ ባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ – – -) ታሪኮች ነበሩት። አሉት ይኖሩታልም። እያንዳንዱ ዕለት ኹለንተናዊ ፍጻሜ የተከናወነበትና የሚከናወንበት በመኾኑ ታሪካዊት ናት። ይህም ኾኖ ከዕለታት መሐከል የተለየ፣ የተመረጠና በልዩ ኹኔታ የሚታይ ዕለት እንደሚኖረው ኹሉ የካቲት 11፣ 1967 ዓ.ም የ20’ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ በኃላ – የትግራይ ሕዝብ ጨቋኝ፣ በዝባዥ እና አስከፊ የነበረን ሥርዓቶች ለመታገል ባሰቡ የትግራይ ሕዝብ ልጆች ወደ ደደቢት ያመሩበትና የትጥቅ ትግልን በንቃት በተደረጃ ለመታገል ሀ፣ ሁ . . . ብለው የጀመሩበት ዕለት በመኾኗ ልዩና ታሪካዊት ናት።

የካቲት 11 ለትግራይ ሕዝብ ብቻ ሳይኾን ለተቀረው የኢትዮጵያም ኾነ በምሥራቅ አፍሪቃ ቀጣና ዓበይት ፖለቲካዊ ጠቀሜታዎች እና ወሳኝ ማሕበራዊ ውጤቶች እንዲመጣ አድርጋለች። መሰረት ጥላለች። የካቲት 11 በብሔራዊ ደረጃ ሊከበር የሚገባው ታላቅ ዕለት ነው።

  1. ግን ለምን እናከብራለን? ለምንስ ማክበር አለብን?  

አንደኛ፡- የካቲት 11 – የትግራይ ሕዝብ የ20’ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ በኃላ societal milestones ስለኾነች እና የታሪኩ አንድ አካል ስለኾነች፤ 

ሁለተኛ፡– ከካቲት 11 ጀምሮ የትግራይ ሕዝብ ኹለንተናዊ የትጥቅ ትግልን በመሪው ድርጅት ህ.ወ.ሓ.ት (በዛን ዕለት ተ.ሓ.ህ.ት /ተጋድሎ ሓርነት ህዝቢ ትግራይ/) በኩል ሲያካሂድ ወታደራዊ፣ ኪነ ጥበባዊ፣ ሥነ ጥበባዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ደህንነታዊ፣ – – – አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎችን ለማፍራት ያስቻለች፡ በዚህም የትግራይ ሕዝብ፡ ብሔራዊ ዕሴቶች፡ በሥነ – ጽሑፋዊ ጥበቦች (ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ብሎም ፖለቲካዊ የኾኑ ማንነቶቹ የተገለጹባቸው ድርሰቶች (ልብ ወለዶችና ኢ ልቦለዶች) ፣ ግጥሞች፣ ተውኔቶች፣ ሥነ ቃሎች፣ መነባንቦች፣ ወዘተ) ፤ በእይታዊ ጥበቦች (የሥዕል፣ የፎቶ ግራፍ፣ የምልክት ሥራዎች፣ የፊልም፣ የድራማ፣ የጭውውት፣ ወዘተ) ፤ በትዕይንታዊ ጥበቦች (የሙዚቃ፣ የትያትር፣ የውዝዋዜ፣ የጭፈራ፣ ባሕላዊ የሐዘንና የደስታ መገለጫዎች የኾኑ ተግባራት፣ ለመንፈሳዊ አገልግሎት የዋሉ የሃይማኖት በዓላት መገለጫዎች)፤ በዕደ ጥበብ ሞያ (የቅርጻ ቅርጽ፣ የሃውልቶች፣ የአልባሳት /የታጋይ ልብስ መለያ/ — ወዘተ) ሥራዎች ላይ የተደረጉ ቀጥተኛ እና ቀጥተኛ ያልኾኑ ሥራዎች ላይ የራሷን ታላቅ አሻራ ያሳረፈች ዕለት ስለኾነች፤ 

ሶስተኛ፡– የትግል ምዕራፎችን ለመጓዝ መሠረት የጣለች፡ ሕብረተሰብን በማነጽ ሂደት (reshaping society) ብቻ ሳይኾን ፍሬም ያፈራች ዕለት በመኾኗ፤ (የፍሬው መጠን፣ አድማስና ጥንካሬ ላይ ያሉ ኹለንተናዊ የፍላጎት አለመሟላቶች ተቃርኖዎች እንዳሉ ሳይዘነጋ)።  

ራተኛ፡– የትግሉን ሰማዕታት በትክክል ለማወቅ – ለመረዳት እና የነሱን አርዓያነት ለመከተል ያስቻለ/የምታስችል ዕለት በመኾኑ።

አምስተኛ፡- ዕለቱን ማክበር ላለፉ ብቻ ሳይኾን ኹለንተናዊ የሕይወት፣ የአካል፣ የጊዜ፣ የጉልበት፣ የዕውቀት፣ የስሜት፣ የመስተጋብር፣ ወዘተ መስዋዕትነት ከፍለው ለዚህ ያበቁንን ባለታሪክ አካላት ማወቅ፣ ማሳወቅ፣ ተገቢውን ክብርና ቦታ መስጠት የሚገባ በመኾኑ።

ስድስተኛ፡– ትግራይ እና የትግራይ ሕዝብ ራሱን define ለማድረግ፡ ራሱን በራሱ ለመረዳት/ለማሳወቅ – ለመግለጽ ብሎም ሌሎች ትግራይና የትግራይን ሕዝብ የሚመለከቱበትን የዕይታ መንገድ የቀየረ – የነበረውን ያዳበረ – ትግራዋይ በየትኛውም ቦታ ኾኖ የሥነ ልቦና ልዕልና፡ በራስ መተማመንና በታሪኩ የሚኮራ ተጨባጭ አብነትን ማቅረብ እንዲችል ያስቻለ በመኾኑ።  

ሰባተኛ፡- በዘመኑ ከነበረው በተሻለ የትግራይ ሕዝብን የትውልድ ቅብብል፣ ብሔራዊ ስሜት፣ patriotism እና ሕብረት ለማጠናከር ያስቻለ በመኾኑ።   

ስምንተኛ፡- የትግራይን ሕዝብ የውስጥና የውጭ፡ social capital ለማንቀሳቀስ፣ ለመጠየቅ፣ ለመመርመርና ለማዳበር ያስቻለ በመኾኑ።  

ዘጠነኛ፡– የትግራይን ሕዝብ የውስጥና የውጭ፡ political capital ለማንቀሳቀስ፣ ለመጠየቅ፣ ለመመርመርና ለማዳበር ያስቻለ በመኾኑ።  

አስረኛ፡– ትላንትም ኾነ ዛሬ ሌሎች ኹለንተናዊ የውስጥና የውጭ ኃይሎች፡ የትግራይን የፖለቲካ ኃይሎች የሚመለከቱበት ዕይታ፣ የስሙ፣ የእንቅስቃሴውና የተግባራት ኹለንተናዊ ተጽዕኖ፡ በተረክም፣ በዕሳቤም ኾነ በተግባር ለመፍጠር ያስቻለች ዕለት በመኾኗ። 

ስራ አንደኛ፡- ትግራይ እና የትግራይ ሕዝብ በትግራይም ኾነ ከትግራይ ውጭ አሁን ላለበት ኹለንተናዊ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ወታደራዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ፣ ሥርዓታዊ፣ ወሰናዊ፣ ሉዓላዊና ፖለቲካዊ ኹለንተናዊ አቅም ትልቅ መሰረት የጣለች በመኾኗ።

ዛሬ ምንም እንኳ በምንፈልጋት ትግራይና እንዲኾን በምንፈልገው የትግራይ ሚና፣ ተሳትፎ፣ ተጠቃሚነት፣ ተጽዕኖና የመሪነት ቦታ እና በተጨባጭ ባለችው ትግራይ መሐከል ሰፊ ልዩነት ቢኖርም ዛሬ ከጠላቶቿና ከወራሪዎች ጋር መገዳደር፣ መደራደርና ተጽዕኖ መፍጠር የቻለች ትግራይ እንድትኾን የካቲት 11 – የየካቲት 11 ፍሬዎች ውጤት መኾኑን ማስተዋል ተገቢ ይኾናል፡፡ በርግጥ አከባበር ላይ ከላይ የተቀመጡ ነጥቦች ትርጉም ባለው መንገድ እየታሰቡ፣ ትርጉም ባለው መንገድ እየታቀዱ ሲካሄዱ ነበር? ይካሄዳልን? የሚለው ሌላው ነጥብ ነው፡፡ 

ማንኛውም ኹለንተናዊ ትግል ምዕራፎች እንጂ መጨረሻ የለውም፡፡ የማይቋረጥም ኹለንተናዊ ሂደትም ጭምር መኾኑ ሊስተዋል ይገባል፡፡ የካቲት 11 ኹለንተናዊ ትግል – ከቀደሙ ትግሎች የተማረና ልምድ የቀሰመ፤ ከመሰል ድርጅቶች የትግል ሂደት ልምድ የወሰደ – ተዋግቶም ድል ማድረግ የቻለ፤ በዘመኑ በነበረው ዓለም አቀፍ – ሀገር አቀፍ ርዕዪተ ዓለማዊ እንቅስቃሴ ተጽዕኖ ውስጥ ኾኖ በዘመኑ ከነበሩት ድርጅቶች በተሻለ ውጤታማ የኾነ ነው፡፡ የካቲት 11’ን ስናስብ – ስንገመግም – ስንመረምርም ኾነ ስንመለከት የሕዝባዊ ትግሉን ኹለንተናዊ ባህሪያትና ጠባያት ማስተዋል የሚያስፈልግ ይኾናል፡፡ የካቲት 11 ትግል በዋናነት በሶስት ዋነኛ – አበይት ምዕራፎች ሊታይ ይችላል፡፡ 

ይህም፡- 

I. ሥርዓት የማፍረስና የመጣል ምዕራፍ፤ 

II. የሽግግር ሥርዓት የማካሄድ ምዕራፍ፤ 

III. ሥርዓት የመገንባት ሂደት ምዕራፍ፤ 

 እያንዳንዱ ኹለንተናዊ ዋነኛ የትግል ምዕራፍ በውስጡ ኹለንተናዊ ንዑሳን ምዕራፎች ነበሩትም፡፡ አሉትም፡፡ ይኖሩታልም፡፡ ስለኾነም ማንኛውም አካል የካቲት 11’ን ሲመለከት በምዕራፎች ከፍሎ ሊገመግም፣ ሊመለከትና ሊመረምር የተገባ ይኾናል፡፡ በትክክል የካቲት 11 ሁለቱን ምዕራፎች ያለምንም ጥርጥር በብዙ ቃላት ከሚገልጹት በላይ በኾነ ኹለንተናዊ የሕይወት፣ የአካል፣ የጊዜ፣ የጉልበት፣ የዕውቀት፣ የስሜት፣ የመስተጋብር – – – ወዘተ መስዋዕትነት ከሌሎች መሰል ድርጅቶች በተለየ ውጤታማ እና ስኬታማ ኾኗል፡፡ ይህም በተግባር – በዕሳቤ – በሥርዓት ግንባታም በተጨባጭ የታየ፡ major significant and important  

ተጽዕኖውንና ሚናውን በዓለም አቀፍ ቅርጽና ይዘትንም ማላበስ ያስቻለ ነው፡፡ 

በወቅታዊ የትግራይ ሕዝብ፡ ከተፈጸመበት የዘር ማጥፋት፣ የጦር ወንጀሎችና ኹለንተናዊ ወረራዎች በመነሳት ያጋጠሙ ኹለንተናዊ የማህበራዊ፡ የኢኮኖሚያዊ፣ የፖለቲካዊ አመራር ውድቀቶችን፤ ያሉ መሰረታዊ የመልካም አስተዳደር ችግሮችና ጥያቄዎችን፤ የግዛትና አንድነትን ከማስጠበቅ አንጻር ያጋጠሙ ውድቀቶችን፤ የትግራይና የትግራይ ሕዝብን ሉዓላዊነትን በተሟላ መንገድ ማረጋገጥ አለመቻልን፤ ከባሕልና

ከዕሴት አንጻር የሚፈለገውን ያክል አለመሰራት፤ በሥርዓት ግንባታ ሂደት ኹለንተናዊ ተቋማዊነትን በተሟላ መንገድ አለመያዝን፤ ትርጉም ባለው መንገድ የትግራይና የትግራይን ሕዝብ ኹለንተናዊ ልዕልናና ሥልጣኔ በሚያረጋግጥ መንገድ የፓርቲና የመንግሥት አለመለያየት፤ ነጻ፣ ገለልተኛና ጠንካራ የፍትህ ሥርዓት ካለመገንባት፤ ከፖለቲካ ተሳትፎ – ዲሞክራሲያዊ ባሕልና አሰራርን ከማጎልበት አንጻር ያሉ ክፍተቶችን፤ የትግራይን ሕዝብ በተሳሳተ ፖለሲ በመምራት ከሩብ ክፍለ ዘመን በላይ መርቶ ከድህነት ማላቀቅ አለመቻል – በኹሉም ዘርፎች ዘላቂና አስተማማኝ ትራንስፎርሜሽን ማምጣት ካለመቻል – – – ወዘተ በመነሳት እጅግ serious frustrations እንደማሕበረሰብ ያጋጠመን በመኾኑ መደነጋገሮችና ስሜታዊነት የፈጠራቸው ድምዳሜዎች እንደተጠበቁ ኾነው እስከዛሬ ድረስ በትግራይ ያልተነሱ ጥያቄዎች – ስሜቶች – ዕይታዎች – ድምዳሜዎች መነሳት ጀምረዋል፡፡  

ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተገናኘ ምናልባት አንዳንዶች የሚያነሱት የማክበርና ያለማክበር ጉዳይ በዋናነት ከሶስተኛው ምዕራፍ ጋር በተገናኘ ያለውን መሰረት በማድረግ ነው፡፡ (በርግጥ ጥቂቶች ለየካቲት 11 መሠረት የኾኑ ሥርዓቶች ተጠቃሚ፣ ደጋፊና መሪ ብሎም ራሱን የካቲት 11’ን ታግለው ማሸነፍ ያቃታቸው አካላት እንዳሉም ሳይዘነጋ፡)  

ይህም አንድ መሰረታዊ ነጥብን ያፋርሳል፡ ይህም ኹለንተናዊ የትግል ባሕሪያትና ጠባያትን ካለማስተዋል፤ የትግል ምዕራፎችን ከመቀላቀል የተነሳ በመኾኑ አመክንያዊ ካለመኾኑም ባሻገር ከዕውነት (truth)ና ከእውነታ (reality) የራቀ ነው፡፡ ለዚህም መፍትሔው የሕዝባዊ ትግሉን ጅማሬ፣ ሂደት ከማስተዋል ባሻገር ፍጻሜ የሌለው መኾኑን መረዳት ነው፡፡ 

2. እንዴት እናክብረው?  

 የካቲት 11 መከበር ይኖርበታል፡፡ ከተከፈለው ኹለንተናዊ መስዋዕትነት አንጻር ማክበርም ሞራላዊ ማሕበረሰባዊ ግዴታ ነው፡፡ ሌላው ወሳኝ ነገር – አከባበሩ ነው፡፡ የካቲት 11’ን ማክበር ትርጉም ባለው መንገድ ሊኾን ይገባል፡፡ አከባበሩም በኹለንተናዊ መንገድ ትርጉም ያለው ይኾን ዘንድ አከባበሩ ራሱ በሶስት ምዕራፎች ላይ ተመርኩዞ – በደማቅ ኹኔታ በምክክር፣ በጥናትና ምርምር መድረኮች፣ በደስታ – በጭፈራ – በመዝሙር ብሔራዊ በኾነ: የትግራይን ሕዝብ ኹለንተናዊ social and political capitals በሚገነባ መንገድ ሊከበር ይገባል፡፡ 

በዚህም፡- በመጀመሪያው ምዕራፍ፡- ሥርዓት የማፍረስና የመጣል ሂደትን በትክክል ታሪኩን የመዘከር፣ በትክክል ባለታሪኩን የማስታወስ፤ በትክክል ታሪካዊ ፍጻሜዎችን የመሰነድ፤ በትክክል የትግሉን ኹለንተናዊ ሂደት የማሳወቅ – የማደራጀት ሥራዎች ላይ ትኩረት ሊያደርግ ይገባል፡፡

በሁለተኛ ምዕራፍ፡ የሥርዓት የሽግግር ሂደት ከየካቲት 11 መነሻ ዓላማዎች እና ከትግራይ ሕዝብ ኹለንተናዊ ተጠቃሚነት አንጻር ትርጉም ባለው መንገድ መፈተሸና መመርመር ያስፈልጋል፡፡ የትግራይ ሕዝብ በሽግግር ሥርዓቱ ሂደት የነበረው ተሳትፎ ምንድነው? ምን ማግኘት ነበረበት? ምን አገኘ? ምን ያክል በተጨባጭ በምን በምን ዘርፎች ላይ ሚናውን ከመወጣት ባሻገር ተጠቃሚነቱን አረጋገጠ? – – – የሚለው ሊታይ ይገባል፡፡ 

በሶስተኛው ምዕራፍ፡- የካቲት 11’ን የትግራይን ሕዝብ: በማሕበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ፣ በባህላዊ፣ በፖለቲካዊ፣ በሥርዓት – ተቋማዊነት ግንባታ፣ በሉዓላዊነት፣ በተሳታፊነት፣ በኹለንተናዊ ዘላቂ ተጠቃሚነት፣ በግዛት ማስጠበቅ፣ በነጻነት፣ ራስን በራስ በማስተዳደር፣ በመሠረተ ልማት ግንባታና ዝርጋታዎች፣ በዲፕሎማሲ – –  – ወዘተ የትግራይ ሕዝብ ምን አገኘ? ምን ማግኘት ነበረበት? ማግኘት የሚገባውን ያህል እንዳያገኝ እንቅፋት የኾነበት ምንድነው? ለዚህ ተጠያቂው ማነው? ለወደፊቱስ የትግራይ ሕዝብ ኹለንተናዊ ጉዞ ከየካቲት 11  ወዴት ነው? – – – በሚል ትርጉም ባለው መንገድ በሥልጣኔ ሊወያይበት፣ ሊመካከርበት፣ ሊከራከርበት፣ ሊመራመርበት፣ ሊደሰትበት፣ ሊኮራበት፣ ሊጨፍርበት፣ በአደባባይ የሥነ ልቦና ልዕልናውን የሚያሳይበት – የመንፈስ አንድነቱን የሚያጠናክርበት፤ በራስ መተማመኑን – የገጽታ ግንባታውን ከኹለንተናዊ የsocial and  political capitals ጋር አስተሳስሮ የሚጠቀምበት፤ ብሔራዊ ክብሮቹንና ዕሴቶቹን ለዓለም በሚያሳይበት ከፍታ በድምቀት ሊያከብረው የሚገባ ይኾናል፡፡  

 የካቲት 11’ን ማሰብ – ማስታወስና መዘከር፡ የትግራይ ትውልዶችን ትርጉም ባለው መንገድ ለማስተሳሰር የሚጠቅም ከመኾኑም ባሻገር የትግራይን ትላንት በትክክል ለመረዳት – የትግራይን ዛሬ በትክክል ለማስተዋል እንዲሁም የትግራይን ነገና ከነገ ወዲያ በትክክል imagine ለማድረግ በሚያስችል የንቃት ደረጃ – በብሔራዊ ስሜት ማክበር ተገቢ ይኾናል፡፡ ትላንቱን በትክክል የማያውቅ ማሕበረሰብ – ዛሬውን በትክክል የማያስተውል ማሕበረሰብ እና ስለነገው በትክክል የማይጨነቅና እንቅልፍ የማይነሳው ሕብረተሰብ ህልውናውን ለማረጋገጥ፣ ተጽእኖውን ለማጉላት – የውስጥና የውጭ ተጽዕኖን ለመቋቋም፣ ሚናውን ለመወጣት፣ ተወዳዳሪ ለመኾን ከኹሉ በላይ ለመሠልጠንና የሥልጣኔ ኹለንተናዊ ተጠቃሚ ለመኾን ይቸገራልና ይህን ትርጉም ባለው መንገድ ማሰብ ለትግራይና ለትግራይ ሕዝብ እጅግ አስፈላጊ ይኾናል፡፡ 

ዘልኣለማዊ ክብርን ሞገስን ንሰማዕታትና!