ኢትዮጵያ ነገ…

አሌክስ ዋል (ፕሮፌሰር)

አሁን ባለው የተወሳሰበና ግራ አጋቢ በሆነው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ ውስጥ ሆነንም ቢሆን የተወሰኑ ነገሮችን በግልጽ መገንዘብ ይቻላል፡፡ 

ተጋሩ በጅምላ ጭፍጨፋ፣በመገለል፣በአስገድዶ መደፈርና በረሃብ እንዲጠፉ ዘመቻ ተካሂዶባቸዋል፡፡ ቀላል የማይባሉት በዚህ ምክንያት ጠፍተዋል፡፡ቁጥራቸው የበዛ ደግሞ እየተሰቃዩ ነው፡፡ሁሉም ተጋሩ ግን ስሜታቸው እንደተረበሸ ቀጥሏል፡፡ ልቦና ላለው ሰው አሁን መላ ተጋሩ የደረሰባቸውና እየደረሰባቸው ባለው ለመገመት የሚከብድ ስቃይና መከራ ማዘኑና የተጋሩ መከራ እንዲያቆም ማሰቡ አይቀርም፡፡ 

የትግራይ መከላከያ ሰራዊት በአንድ ዓመት ውስጥ እራሱን እየገነባና በገነባው ልክ ጠላቶቹን እየገጠመ  ጠላቶቹን በጠቅላላ ድል በማድረግ  በጦርነት ታሪክ ውስጥ አስገራሚ ሊባል የሚችል ነገር ፈጽሟል፡፡ የጦርነቶች መቋጫ የሆነ ወታደራዊ መፍትሄ የለም ከሚለው የተለመደ አባባል በተጻራሪ የትግራይ መከላከያ ሰራዊት በአንድ ዓመት ባካሄደው ጦርነት ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የኢትዮጵያ የሃገር መከላከያ ሰራዊትን አሸንፏል፡፡ በጦርነቱ የተሸነፉት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትና ጠቅላይ አዛዥ ብቻ ናቸው፡፡ሽንፈታቸው ሙሉ እና ለሌላ የማይተላለፍ የነሱ ብቻ ነው፡፡ የትግራይ መከላከያ ሰራዊት የገጠመው ጠቅላይ ጦር አዛዡና ተከታዮቻቸው ካዘመቱት ጦር ጋር እንጂ ከማንኛውም የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር አይደለም፡፡ የትግራይ መከላከያ ሃይል ያስመዘገበው ድንቅ ድል በወዳጆቹ አድናቆትና ክብር አትርፎለታል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ በአሁኑ የኢትዮጵያና የትግራይ ፖለቲካ ላይም ከወሳኞቹ ተርታ አስቀምጦታል፡፡

 ሕወሓት በብዙ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የማይታመንና አልፎ አልፎም የሚጠላ ድርጀት ነው፡፡ ይህ ችግር በትግራይ ውስጥም በተወሰነ መልኩ የሚታይ ችግር ነው፡፡ በትግራይ ክልል ያሉና ከህወሃት ጋር የትግራይ መከላከያን ሃይልን ተቀላቅለው በትግራይ ህዝብ ላይ የተቃጣውን የዘር ማጥፋት ዘመቻን ሲመክቱ የነበሩ ሶስት ተገዳዳሪ ፓርቲዎች በቅርቡ በይፋ እንደገለጹት በክልሉ የነበረውና ያለው በህወሃት ብቻ የሚዘወር ፖለቲካዊ ሁኔታ መቀየር እንዳለበት በይፋ አቋማቸውን ገልጸዋል፡፡  ተጋሩ ከማንኛውም ጊዜ በላይ ቀዳሚ ትኩረታቸው በክልሉ አካታች የሆነ የፖለቲካ ሁኔታ መፍጠር እንደሆነ ተገንዝበዋል፡፡ ተጋሩ በአስቸኳይ ወደ ፖለቲካዊ ባሕላቸው ገብተው ችግሮቻቸውን በግልጽነት፤ በመቻቻል እና አካታች በሆነ መንገድ ለመፍታት መሥራት ይገባቸዋል፡፡በቀጣይዋ ኢትዮጵያ ውስጥ የአድራጊ ፈጣሪነት ሚና የመጫወት ፍላጎትም ሆነ ጥልቀት ያለው አትኩሮት እንደማይኖረው የትግራይ አመራር ግልጽ አድረገዋል፡፡የትግራይ አመራሮች ሠላማዊት ኢትዮጵያ እንደምታስፈልጋቸው ያውቃሉ፤እንዲያም ሆኖ ግን በኢትዮጵያ ላይ እንደ ከዚህ በፊት ዓይነቱ ኢንቨስት እንደማያደርጉ መገመት ይቻላል፡፡ 

 ሕወሓት ከኦሮሞ ነፃነት ሠራዊትና ከሌሎች ሰባት አነስተኛ ድርጅቶች ጋር በመሆን የኢትዮጵያ ፌደራሊስትና ኮንፌደራሊስት ሃይሎች ጥምረት መሥርቷል፡፡  የሥምምነታቸው መሠረትም ሆነ ሒደት ገና ግልጽ አይደለም፡፡ብዙዎች ግን ያለ በቂ ምክክርና ድርድር እየተወሰነ ያለ የፖለቲካ አጀንዳ እያስቀመጠ ሊሆን ይችላል የሚል ፍራቻ አላቸው፡፡  

ተጋሩ የእንደገና መነሳታቸውና ማቸነፋቸው ሚስጥር የራሳቸው የተባበረ ትግል ብቻ እንደሆነ ጠንቅቀው ይገነዘባሉ፡፡ የተባበሩት መንግስታት፤ የአፍሪካ ህብረት፤ እንደዚሁም አለም አቀፉ ህብረተሰብ በአጠቃላይ የተጋሩ እልቂት እንዲገታ የህግ የሞራልና የፖለቲካ ሀላፊነታቸውስ በተገቢው መንገድ ስላልተወጡ ይህንን ውድቀታቸውን በይፋ ተገንዝበውና አርመው መንቀሳቀስ እስሚጀምሩ ድረስ የትግራይ አመራር በሚወስነው ጉዳይ ላይ ለኖራቸው የሚችል ተጽእኖ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ 

 ጦርነቱ የሚያዋልደው ነገር ምንም ይሁን፣ተጋሩ እራሳቸውን በራሳቸው ለማስተዳደር የሚወስኑት ውሳኔ የሚያስከትለው ውጤት ምንም ይሁን ተጋሩ የራሳቸውን ቀዋሚ ደህነንት በራሳቸው ለማረጋገጥ መፈለጋቸው አይቀሬ ነው፡፡ ሌሎች ኢትዮጵያዊያን ወደዱም ጠሉትም ይህንን የተጋሩ ፍላጎትን እንዳላዩ ማለፍ አይችሉም፡፡ ተጋሩ ትጥቃቸውን አይፈቱም፡፡ 

ትግራይ እራሷን መልሳ ለመገንባትም ከዓለማቀፉ ማሕበረሰብ እገዛ ትፈልጋለች፡፡የፀጥታ ሀይሏን ማቀብ ብቻ ሳይሆን የውጭ እርዳታን በቀጥታ የመጠየቅ፤ የማግኘትና፤ የመቀበል መብት እንዲኖራትም ትሻለች፡፡

 ዐቢይ አሕመድ ሙሉ  በሙሉ ተሸንፈዋል፡፡ ይሔ ጦርነት የእርሳቸው ነበር፡፡ ጦረኝነታቸው፣ ውሸታምነታቸውና ወንጀላቸው መልሶ እራሳቸውን እየበላቸው ነው፡፡ ጠቅላይሚኒስትሩ በቅዠት ዓለም የሚኖሩ  (Confabulist)፤ እውነተኛ አማኝ (True believer)፤ የተሳሳቱ ህልመኛ (Misguided dreamer)፤ ወይም ያልተገደበ የስልጣን ጥማት ያላቸው (Megalomaniac) ሊሆኑ ይችላሉ።አሁን ያላቸው ምርጫ እጅ ለመስጠት መደራደር   አለያም እስከ መጨረሻው በመፋለም መራራውን  ፍጻሜ መጋት ነው፡፡

 የኢትዮጵያ መከላከያ ሃይል ባሳለፍነው ሰኔ በወሳኝነት ተሸንፏል፡፡ጠቅላይሚኒስትር ዐቢይ ይህንን የጦርሜዳ እውነት ከመቀበልና ወደ ድርድር ከመግባት ይልቅ  መዋጋትን መርጧል፡፡በዚህም ምክንያት የትግራይ መከላከያ ሃይል ከሞላ ጎደል መደበኛ ሰራዊት ይዞ ከተቀረው የደምብ ልብስ ከመልበሱ በስተቀር መደበኛ ካልሆነ ከሀገሪቱ ጦር፣ ከአማራ ሚሊሺያና ሌሎች ሃይሎች የተውጣጣ ጦርን በሰው ማዕበል፤ኢላማ በሌላቸው የአየር ድብደባዎች፤ረሀብን እና የፕሮፓጋንዳ ጦርን አጣምሮ የሚዋጋ ኢመደበኛ ሀይል ነው የገጠመው።፡ ከተበታተኑ በኋላ እንደገና የተሰባሰቡት የአገሪቱ መከላከያ ክፍለጦሮች ከነባሩ ሠራዊት ጋር የሚመሣሰሉት በዩኒፎርማቸውና በአሰላለፋቸው ብቻ ነው ማለታ ይቻላል፡፡ ይህ ሰራዊት የሚመስል ስብስብ የዐቢይን  መንግስት ወታደራዊ ውድቀትን ለአንድ ወይም ለሁለት ወር አራዝሞታል።ምናልባትም በሽምቅ ውጊያም ሊቀጥል ይችላል፡፡ 

ጦርነት የሚደራጅበት መንገድ አንድ መንግሥት የሚዋቀርበትን መንገድ ያመለክታል። በዚህም ምክንያት የዐቢይ አይነት ጦርነት፤ አወቃቀሩና አካሄድ የሚያመለክተው የብልጽና ፓርቲ ምንም መልኩና ይዘቱ ስልጣን ላይ መቀጠል እንኳን ቢችል የተማከለ መንግስት  መሆኑ እንዳበቃለት ነው፡፡ ከዚያ ይልቅ ሁኔታው የሚያመለክተው ከአሁን በኋላ ኢትዮጵያ በብልጽና ስር ሆና የተማከለ መንግስት ሳይሆን አስመሳይና እወደድ ባይ የብሔር ፖለቲከኞች፣የጦር ቡድኖችና ቅጥር ነፍሰ ገዳዮች ለሥልጣን የሚራኮቱባት የፖለቲካ ገበያ መሆኗ አይቀርም፡፡  የፀጥታ ተቋሞቿ የነበራቸው ወጥነት የነበረው አደረጃጀታቸው ጠፍቶ የተበታተኑ የብሄር መፈክር የያዙ ለስልጣን ድርሻ የሚራኮቱ ቅጥረኞችና የጦር አበጋዞቸ ወደመሆን አቅጣጫ መጓዝ ጀምሯል፡፡

ዐቢይ አህመድ አገርን ተረክበው የዚህች አገር ንጉስ የመሆን ህልም አንግበው በሂደቱ ግን አገርንም የንግስና ህልማቸውንም ያጡ መሪ ተብለው መዘከራቸው አይቀርም፡፡ 

የዐቢይን ተባባሪዎች በሆነ ቡድን ውስጥ ማስቀመጥ አይቻልም፡፡ጽንፈኛ አማሮች፣ከሥልጣኑና እርሱ ከሚያስገኘው ጥቅም ለመቋደስ ብለው የዐብይን ወደ ስልጣን መምጣት ያመቻቹና በሂደቱ የግልና የቡድን ጥቅማቸውን ያሳኩ የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ሰዎች፣ እና የሀገሪቱ ልማት አመላካች የሆኑት የልማት ተቋማት በዐብይ መንግስት ሲሸጡ  እነዚህን ተቋማት በሀራጅ ዋጋ የመግዛትና የማዝረፍ ህልም የነበራቸው በልማታዊ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ያገኙ ባለሀብቶች ናቸው፡፡ 

 የአማራ ጽንፈኞች አፄያዊ ስርዓትንም አጥተው የዳበረ የአማራ ማንነትም ሳይኖራቸው ቀርተዋል፡፡  በ1960ዎቹ በነበረው የተማሪዎች ንቅናቄ ውስጥ የተሳተፉና የአማራ ህዝብን ለተወሰነ ጊዜ የመሩት ተራማጅ ሀይሎች ባለፉት ጥቂት ዘመናት ሊገነቡት የሞከሩት ሲቪክና ዲሞክራሲያዊ ብሄረተኝነት ቢሆንም አማራው እንደሌላው ኢትዮጵያዊ ከልማታዊ መንግስቱ ቱርፋቶች እንዲጠቀም አድርገውታል፡፡ ሆኖም ግን አብዛኛው የአማራ ፖለቲከኛ ያልማት የነበረችው ኢትዮጵያ በምስሉ የተቀረጸች ስለነበረች የነበረው ሲቪክ ብሄረተኝነት ተቀልብሶ ጽንፈኛ በሆኑ ሀይሎች የሚመራ አክራሪና አግላይ ብሄረተኝ ነት የአማራን ፖለቲካ የሚዘውርበት ሁኔታ ተፈጥሯል;  

ለቀጣዩ አጭር ጊዜ የአማራ ፖለቲከኛች ለሂደቱና ለደረሰው ጉዳት በተጠያቂነት ጉዳይ መጠመዳቸው ምንም ጥርጥር የለውም፡፡በውሸት ፕሮፖጋንዳ ተነሳስተው ልጆቻቸውን በገፍ ወደ ጦር ሜዳ ልከው ያለቁባቸው ቤተሰቦች ልጆቻችን የት ሄዱ ብለው መጠየቃቸውና ለሀገርና ለወገን ደህንነት ያላቸው ስሜትና ቁርጠኝነት በተሳሳተና ውጤት አልባ በሆነ መርቶ የከፈሉት ዋጋ ለከንቱ እንዲሆን ያደረጋቸውን ሀይል መጠየቃቸው  አይቀርም፡፡ ብዙዎች በስማቸውና በአገራቸው ተጠርተውና ተመርተው የተፈጸሙ ገደብ የለሽ አሳፋሪ ግፎች በአለም ፊት በፈጠሩት አስከፊ ገጽታ እየተሳቀቁ መሆራቸው አይቀርም፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ከአዲስ አበባና በማሕበራዊ ሚዲያ ካዳሚዎቻቸው እየታዘዙ በፈፀሙት ጅምላ ጥቃት መጠየቃቸው አይቀርም፡፡ከአማራ ውጪ ያሉት የሕብረተሰብ ክፍሎች በተለይም ተጋሩ፣ኦሮሞዎች፣እንደ አገውና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብሎም ቅማንት የደረሰውን መከራ እንዲደርስ በአንዱ ወይም በሌላ መልኩ ተዋናይ ለነበሩት ሀይሎች በሙሉ ይቅር ላይሏቸው ይችላሉ፡፡

ቀጣዩ ፖለቲካ መዋቅርና ቅርጽ የሚወልደው ቅንነት ላለው ያለፈ ችግርን የመገምገሚያ ስልጡን ምክክር?  ወይስ ከሀላፊነት ለመሸሽ የሚደረግ የውስጥና የውጭ ተጠያቂነትን ሀይሎች ፍለጋ ላይ ያተኮረ የእጅ መጠቋቆም? የሚታወቅ ነገር የለም፡፡   

የአማራ ሚና የሌለባት ኢትዮጵያ ልትኖር አትችልም፡፡ የአማራ ፖለቲከኛች በመካከላቸው ያለውን መበታተንና መናቆር መልክ አስይዘው ለስልጡን ምክክርና ክርክር እራሳቸውን ማዘጋጀት ለራሱ ለአማራ ህዝብ ድህንነትና ትግራይን ጨምሮ ለጎረቤቶቻቸው ሠላምና ፀጥታ  ወሳኝ ነው፡፡ ይህ ሀላፊነት በትልቁ  የሚወድቀው የዐቢይን ወንጀልና አገዛዝ በመቃወም ላይ በነበሩ ጥቂት የአማራ ፖለቲከኞች ላይ ነው፡፡ 

ኢትዮጵያ መብቶቻቸው ስለመከበሩና ህልውናቸው ዋስትና ስለማኘቱ ቅቡልነት ያለው ፍራቻ ያላቸው የበርካታ አነስተኛ ብሂረሰቦች አገር ናት፡፡ 

አሁን የኢትዮጵያ መንግሥትነቱ ዕጣ ፈንታ በኦሮሞዎች መዳፍ ላይ ነው፡፡ ኦሮሞዎች ኢትዮጵያ እስከሚቀጥለው ትውልድ የምትጓዝበትን የፖለቲካ መንገድ የመወሰን ዕድል በዘላቂነት አለያም ለአንድ ትውልድ ያክል የመወሰን እድል አገሪቱ ያለችበት ተጨባጭ ፖለቲካዊ ሁኔታ የሠጣቸው አጋጣሚ ነው፡፡ከተጋሩ ጋር ለጊዜውም ቢሆን አሀዳዊት ኢትዮጵያን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመቅበር ያላቸው ፍላጎት አንድ ያደርጋቸዋል፡፡ አሁን ይህ የጋራ ምክንያታቸው ለትብብር ሰበብ ይሆናቸዋል፡፡ይሁን እንጂ ኦሮሞዎች የትግራዮች እገዛ የሌለበትና በራሳቸው የፀጥታ ሃይል የተመሰረተ የበላይነት ይፈልጋሉ፡፡  ከሁሉም በላይ ደግሞ የኦሮሞ ፓርቲዎች የኢትዮጵያ ብሔሮችና ህዝቦች በአንድ ላይ ተሰባስበው ከንጉሳዊ አገዛዝ በኋላ የመሰረቱበትን ሁኔታ የስምምነት ሁኔታዎቹን እንደገና ሰርተው ለማደስ ይፈልጋሉ፡፡

ኢትዮጵያ ፌደራላዊ ሥርዓት ወይም ኮንፌደራላዊ አለያም የጋራ ኢኮኖሚያዊ ብልጽግና ያላቸው ክልሎች ወይም ሌላ አይነት የሕብረት አይነት የምትከተል ልትሆን ትችላለች፡፡ከጎረቤት አገራት ጋር በተለይም እንደ ኤርትራና ሶማሊያ ካሉት ጋር እንዴት እንቀጥል የሚለውም ሌላ የውይይት አጀንዳ ነው፡፡

በቀጣይ የሚኖሩት የኢትዮጵያ ክልላዊ ግዛቶች ትግራይ በፀጥታም ሆነ በቀጥታ ከዓለማቀፉ ማሕበረሰብ የፋይናንስ ድጋፍ ለማግኘት የምትከተለው አካሄድ እንደ አርዓያ ወስደው ሊከተሉት ይችላሉ፡፡ እነዚህና እነዚህ በመሳሰሉ ምክንያቶች ቀዳሚ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ያሉ አማራጮችን ለመፈተሸ ለሚደረግ ዉይይት ክርክርና ድርድርን እንጂ የአቋራጭ መፍትሄ የሚያስገኙ የሚመስሉ ህገመንግስታዊን ተመሳሳይ አሳሪ ስምምነቶችን ለማድረግ መሆን የለበትም፡፡ ዘላቂ ሕገ መንግስት ለመንደፍ ባለሙያዎች ከሚያደርጉት ጥረት ይልቅ ግልጽ ውይይትና ስምምነት ቅድሚያ የሚሰጠው ረጅም የሽግግር ሂደት ሊያመጣ ይችላል። በዚህ ምክንያትም የሚካሄደው ውይይትና ድርድር ብዙ እንድምታ በሚኖራቸው ህጋዊና ህገመንግስታዊ ከሆኑ ጉዳዮች ማተኮር ትቶ ስልጡን በመቻቻልና መግባባት ለይ የተመሰረቱ የጋራ የስምምነት አጀንዳዎችን ለመለየትና እንደዚሁም ከልዩነቶች ጋር አብሮ የመኖርን ባህል ለማዳበር በሚጠቅም ውይይት ላይ ማተኮር አለበት፡፡  ይህ ጉዳይ ረዘም ላለ ጊዜ በሚቆይ የሽግግር ጊዜ እና ቀዋሚ ለሆኑ የህግና ህገመንግስታዊ የስምምነት ነጥቦች ለመድረስ ከማተኮር ይልቅ አገሪቱ ባሉዋት ችግሮችና መፍትሄዎቻቸው ሰፊ ህዝባዊ ስምምነት መፍጥርን ቅድሚያ ሰጥቶ በሚካሄድ ሰፊና አካታች ብሄራዊ የውይይት፤ የድርድርና፤ የስምምነት ሂደት የሚፈጸም ይሆናል፡፡ 

 የኦሮሞ መሪዎች ይህንን ለማድረግ ብቁ ናቸው ወይ የሚለው ጥያቄ መነሳት አለበት፡፡መከፋፈልና ጥቅመኝነት የኦሮሞ ፖለቲካ ዋነኛ ድክመቶች ሆነው ቆይተዋል፡፡ ወሳኝ በሆኑ የታሪካ አጋጣሚዎች ለምሳሌ በ1966/67፣በ1983 እና 2010 ዓመንግስታት ተዳክመው ስልጣን ወሳጅ በሚፈልግበት ሰዓት ይህ የኦሮሞዎች የፖለቲካ ድክመት የሚፈልጉትን እንዳያገኙ እንቅፋት ሆኖባቸዋል፡፡ የኦሮሞ አመራሮች ብዙውን ጊዜ ጥያቄያቸውንና መልሳቸውን ውጫዊ አድርገው የማሰብ ድክመት ይታይባቸዋል፡፡  መርህ ተከል እና ዴሞክራሲያዊ የሆኑት መሪዎችም ቢሆን ለውይይትና ስምምነት ለሚያመጡ ሂደቶችን ቅድሚያ ያለመስጠት እጥረት የሚታይባቸው ሲሆን ሌሎች ብዙዎች ደግሞ ቶሎ ብለው ስልጣን ካለው ሀይል የመጣበቅና ቶሎ ብለው የፖለቲካ መነሻቸን ነው የሚሉትን ህዝብ ወደጎን ትተው የግልና የቡድን ጥቅማቸውን የማሳደድ ድክመት ይታይባቸዋል፡፡ 

 ከ2007-10 ዓ.ም የተካሄደው የኦሮሞ ተቃውሞ እንቅስቃሴ የዴሞክራሲያዊ ተሃድሶ ተስፋ ከመሪዎቹ ድርጅታዊ አቅም በላይ የሆነ ጥምረት ነበር።አሁንም ይሄ አመራር ሶስት ፈተናዎች ተደቅነውበታል፡፡የመጀመሪያው ያንን ስሜት መልሶ ወደ ዴሞክራሲያዊ አጀንዳዎች መመለስ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የኦሮሚያ ክልል አብዛኛው ሙሰኛና ብልሹ አስተዳደሪ በሆኑና እራሳቸውም አባል በሆኑበት ሰዎች እየተመራ መሆኑን አውቆ የኦሮሞ ህዝብ ፍላጎትና ጥቅምን ማእከል ያደረገ አስተዳደርን መዘርጋት መቻል ነው፡፡ ሶስተኛ በቁጥር ብልጫ ያለውን የኦሮሞ ሕዝብ የሚመሩት እነዚህ የኦሮሞ መሪዎች ለሕዳጣን የኢትዮጵያን ሕዝቦች እንደ ሥጋት አለመሆናቸውን በተግባር ማሳየት ናቸው፡፡ የፌደራሉ ርዕሰ መዲናን ጉዳይ፣የማንነት፣ የወሰን፣ የሕገ መንግስታዊነትና አስተዳደር ወዘተ ላይ ያሉ ጥያቄዎችን በመመልስ ሂደት እላይ የተመለከቱት ሶስት ጥያቄዎችን በአግባቡ ለመመለስ በሚያስችል መልኩ መፈጸም ያስፈልጋል።

ኢትዮጵያ የሕዳጣን/አናሳ ቁጥር ያላቸው ብሔሮች/ አገር ናት፡፡እነዚህ ሕልውናቸውና መብታቸው በሌሎች እንዳይዋጥ የሚሰጉም ናቸው፡፡ከብሔር ፌደራሊዝም ውጪ ያለው የትኛውም ዓይነት ፖለቲካዊ አካሄድ ሊጎዳቸው ይችላል። ብጥብጥና ወታደራዊ ፖለቲካ ደግሞ የህልውና ስጋት ሊፈጥሩባቸው ይችላሉ።በዚህ ሥጋትና አደጋ ውስጥ ከወደቁ የኢትዮጵያ ዜጎች መካከል በምዕራቡና ደቡባዊው የአገሪቱ ክፍል ላይ የሰፈሩ አማሮች ይጠቀሳሉ፡፡

 በየትኛውም የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ጉዞ ውስጥ በማሕበራዊ ሚዲያ የሚደረገው እንቅስቃሴ በጨዋነት መጓዝ ይጠበቅበታል፡፡የማሕበራዊ ሚዲያው ያለ ገላጋይና ያለ ምህረት ጦርነት የሚካሄድበት ሜዳ ሆኗል፡፡የጥላቻና ጽንፈኝነት ሜዳ ነው፡፡ያቺን ተምኔታዊና አሀዳዊት አገር ለመመለስ የተደረገው ጥረት  በጦርሜዳና በገሀዱ ዓለም ከተሸነፈ በኋላም ይህንን ሐሳብ በማሕበራዊ ሚዲያው ላይ መከራከሪያ ለማድረግ የሚደረግ ጥረት መኖሩ አይቀርም፡፡በዚህም ፌስቡክንና ትዊተርን የተመለከተ አዲስ ፖሊሲ ያስፈልጋል፡፡

 የኢትዮጵያ ታሪክ በአንድ ማእከል የተማከለ አስተዳደር የመሆኑን ያክል የተለያዩ የተሰንጣጠቁና የተበታተኑ መስተዳድሮች የነበሩባቸው የታሪክ አጋጣሚዎችንም የሚያካትት ነው፡፡ ይህ ሂደት በሚገባ የተጠና ሂደት አይደለም፡፡ ማዕከላዊነት በተጠረነፈ ሥልጣን ብቻ ሳይሆን በተበታተነና በተሰነጣጠቀ የመንግሥትነት ታሪክም የሚታወሱ ምዕራፎች ያሉት ነው፡፡ ይህ በእኢትዮጵያ ታሪክ እየተደጋገመ የሚከሰት የደካማና እውናዊነት የሌለው ማዕከላዊ መንግሥት የመከሰት ጠንቅና ጉዳቱ እንደዚሁም መፍትሄው በእኢትዮጵያ የፖለቲካ አጥኚዎች ረገድ በሚገባ ተመርምሯል ማለት አይቻልም፡፡

አሁን አጼያዊው የተማከለ አስተዳደር በኢትዮጵያ የማያዋጣና የወደቀ መሆኑ አይቀሬ ሆኗል ምናልባትም ከዚህ በኋላ በእኛ እድሜ ተመልሶ ላናየው እንችላለን፡፡ አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ የምናየው ፖለቲካ ከህግ እና አሰራር ይልቅ ገንዘብና ሀይልን በቅድሚያነት የሚጠቀም የፖለቲካ ገበያ የሚመራው ያልተማከለና ያልተቀናጀ ያስተዳደር ዘይቤ መሆን ይችላል፡፡ ይህንን እውነታ ላለማየት ዐይንን ከመጨፈን ይልቅ እውነታውን ተቀብሉ በእንደዚህ ዓይነት ማህበረ፟ ኢኮኖምያዊ ሁኔታ የተሻለ የሚባለው አካሄድና አማራጭ የትኛው ነው ለሚለው ዐይኑን ከፍቶ አማራጫቺችብ ማየት ነው፡፡ 

የአሁኑ የኢትዮጵያ ሕገመንግሥት –እኛ  የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የራሳችንን እድል በራሳችን የመወሰን መብታችንን ተጠቅመን በነፃ ፍላጎታችን ላይ የተመሰረተ አንድ የጋራ ፖለቲካ ማሕበረሰብ እንገነባለን– ብሎ ይጀምራል፡፡ በዚሁ ሕገመንግሥት አንቀጽ8 ደግሞ ሉዓላዊነት ሲተረጎም ‹‹የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የኢትዮጵያ ሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤቶች ናቸው›› የሚል ነው፡፡  በዚህ አውድ ኢትዮጵያዊያንም ሆኑ ዓለማቀፉ ማሕበረሰብ ስለ ሉዓላዊነት ሲናገር ሉዓላዊነት ከፌደራል መንግሥቱ ማዕድ እንደማይቆረስ ማወቅ አለበት፡፡  

አሁን አሀዳዊቷ ኢትዮጵያ እያበቃላት ነው፡፡ይሁን እንጂ የፖለቲካዊ አማራጮች እጥረት አለ፡፡ የትኞቹም የፖለቲካ መሪዎች ይህንን ክፍተት እንደ እድል ወስደው ኢትዮጵያን በቀጣይ ምዕራፍ እንደገና የመፈልሰፍ ሃሳብና ድፍረት ያላቸው ሁሉ፣ በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ ሀገሪቱን ለመምራት የተሻለ ቦታ ይኖራቸዋል።