ኬንያ በኢትዮጵያ እየተካሄደ የሚገኘውን ጦርነት ወደሃገሯ ሳይስፋፋ ለመግታት የሚያስችል ምክክር ከሃገሪቱ የፖሊስ መኮንኖች ጋር አካሄደች።

ላለፈው አንድ አመት ሲካሄድ የቆየው የትግራይ ጦርነት ከወራት በፊት ወደ መዲናይቱ አዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኙ ቦታዎች ጦርነቱ መዘዋወሩን ተከትሎ ስጋት የገባው የኬንያ መንግስት የፖሊስ አዛዦችንና መኮንኖችን ጨምሮ በዕረፍት እና ከስራ ውጪ ያሉ የፖሊስ አባለትንም በሙሉ ወደ ስራ እንዲመለሱ ጠርቷዋል።

በዚህም መሰረት የፖሊስ አባላቱ እስከ ሰኞ ድረስ ወደ ስራ ተመልሰው ሪፖርት እንዲያደርጉም ትዕዛዝ ተላልፏል። የኬንያ መንግስት ጦርነቱን ተከትሎ ህገ-ወጥ የስደተኞች እና የጦር መሳሪያ ፍሰት በሰሜናዊው የሃገሪቱ ክፍል የንግድ እንቅስቃሴውን ሊያስተጓጉል ይችላል የሚልም ስጋት አለው።

የሁኔታዎች መባባስ ያሳሰበው የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤቱ በትናንትናው እለት በፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የተመራውን ስብሰባ ባካሄደበት ወቅት ሁሉም የጸጥታ አካላት የግንዛቤ ደረጃቸውን በማሳደግ ኃይላቸውን ማሰባሰብ እንዲጀምሩ መወሰኑ ነው የተነገረው።

የኬንያ የስቴት ሀውስ ቃል አቀባይ ካንዜ ዴና ማራሮ በሰጡት መግለጫ “ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በቀጠናው እየታየ ያለውን የፀጥታ ሁኔታ ተከትሎ በመላው ሀገሪቱ የውስጥ ደህንነት ተቋማት በንቃት ክትትል እንዲያደርጉ መመሪያም ሰጥተዋል ብለዋል።

ይህንን ተከትሎም በኬንያ እና ኢትዮጵያ አዋሳኝ 800 ኪሎ ሜትር ድንበር ላይ በወታደራዊ እና በብሄራዊ ፖሊስ ጥብቅ ክትት እንዲደረግ በትላንትናው እለት ከተስማሙበት ውሳኔዎች ሃሳቦች አንዱ ነው።

ከዚህም በተጨማሪ የብሔራዊ ፖሊስ አገልግሎቱ በህገ-ወጥ መንገድ ወደ ሀገሪቱ በድንበሮች በኩል ሊገቡ የሚችሉትን የውጭ ዜጎች እና የተኩስ መሳሪያዎች እንቅስቃሴን ለመቆጣጠር ኬንያን እና ኢትዮጵያን የሚያገናኙ ሁሉም መንገዶች እንዲዘጉም ተጠይቋል።

ከወዲሁ ከኢትዮጵያ እየመጡ ያሉት ስደተኞች መበራከታቸው ያሳሰባት ኬንያ በ1991 እ.ኤ.አ የሶማሊያው አምባገነን ሲያድ ባሬ ከወደቀ በኋላ ከተከሰተው ሁኔታ ጋር ተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ መግባት አትፈልግም ሲል ኔሽን አፍሪካ ዘግቧል።