በኢትዮጵያ አሁናዊ የፖለቲካ ሁኔታ ከሶማሊ ጉዳይ ኮንግረስ (Congress for Somali Cause) የተሰጠ መግለጫ

የሶማሊ ህዝብ እኩልነትን፣ ፍትህን እና ክብርን ለመጎናጸፍ እንዲሁም ብሔራዊ ማንነቱን ለማስከበር ከተከታታይ የኢትዮጵያ መንግስታት ጋር መራራ ትግል ሲያደርግ መኖሩ ይታወቃል፡፡ ባለፉት ስድስት አስርት ዓመታትም በሺህዎች የሚቆጠሩ ሶማሊዎችን ለሞት የዳረገ እና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩትን ኑሮ ያወደመ የፖለቲካ ቀውስ በኢትዮጵያ ተፈጥሯል። 

አሁን ያለው የኢትዮጵያ መንግስት አካሄድም ካለፉት መንግስታት ጎጂ አካሄዶች ያልተማረ እና ያልተለየ ለመሆኑ ካለፉት ሶስት ዓመታት ጀምሮ በሀገሪቱ ውስጥ እየተፈጠሩ ያሉ ማህበረ-ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች በቂ ማሳያዎች ናቸው። የብልጽግና ፓርቲ የመመስረቻ ሰነዶች፣ ወጥነትና መርህ የሚባል ነገር ፈጽሞ የማይሸትባቸው የፓርቲው መግለጫዎችን እንዲሁም እርስ በርሱ የሚጋጩ የአመራሮቹን ንግግሮች ላጤነ ሰው ፓርቲው በ1987 የጸደቀውን ለብሔር ብሔረሰቦች ማንነትና ራስን በራስ የማስተዳደር መብት እውቅና የሚሰጠውን የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥትና በህገመንግስቱ የተደነገገውን ስርዓት ማለትም ፌዴራላዊ አደረጃጀት ለመናድ እና በአሃዳዊ ስርዓት ለመተካት ያለውን መሻት ይረዳል። ይህ ሀገር አፍራሽ እንቅስቃሴ የሶማሊ ህዝብ ከግማሽ ምዕተ-ዓመታት በላይ ሲያደርግ የቆየውን ትግል እና ያስመዘገበውን እድገት ወደኃላ የሚወስድ የአድህሮት አካሄድ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡

 በሶማሊ ጉዳይ ኮንግረስ እይታ ይህ የአንድ ብሄር፣ ቋንቋና እምነት የበላይነትን ለማረጋገጥ የተነደፈ አሃዳዊ የፖለቲካ ስርዓት በተግባር ከዋለ የሶማሊ ህዝብና ክልሉ የጥፋቱ ዋነኛ ገፈት ቀማሽ እንደሚሆን ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ይህንን የምንልበት አንደኛው ምክንያት አሁን ላይ የሶማሊ ክልል ፕሬዝዳንት የሆኑት አቶ ሙስጠፌ ዑመር በንጉሠ ነገሥቱ እና በደርግ ዘመን የተፈጸሙ የግፍ ታሪኮችን በማድበስበስ እንዲሁም ዛሬም ድረስ የሶማሊን ህዝብና መሪዎቹን በተመለከተ የሚንጸባረቁ ትርክቶች ባልታረቁበት ሁኔታ የግፉ ፈፃሚዎችንና የርዕዮቶቻቸው አራማጆችን በማወደስ ስራ ላይ መጠመዱ፣ በተቃራኒው ደግሞ አሁን ያለውን የፌዴራሊዝም መዋቅር ለማንኳሰስ የሄደበት ርቀት እጅግ አስደንጋጭ በመሆኑ ነው። በቅርቡም በጂቡቲ ተገኝቶ ያደረገው ንግግር ይህንኑ የሚያንጸባርቅ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡

ስለዚህም የሶማሊ ጉዳይ ኮንግረስ በኢትዮጵያ የአሃዳዊ መንግስት ራዕይን እና ግላዊ አምባገነን ስርዓትን ለመጫን የሚደረገውን ሙከራ አጥብቆ ያወግዛል፡፡ በተጨማሪም በአሁኑ ሰዓት የክልሉ መሪዎች በሺህዎች የሚቆጠሩ የሶማሊ ወጣቶችን “የምኒሊክ ዘመቻ” ተብሎ በተሰየመው የጥፋት ጦርነት ተካፋይ እንዲሆኑ ለማድረግ እያደረጉት ያለውን እንቅስቃሴ አጥብቀን የምናወግዝ መሆኑን ለማሳወቅ እንወዳለን፡፡ እኛም እንደ ጀግኖች አባቶቻችን የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦችን እኩልነት ለማስከበር፣ ማህበራዊ ፍትህን፣ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብትን ለማስከበር መስዋዕትነት እንከፍላለን እንጂ ቃላቸውን አጥፈን፣ የከፈሉትን መስዋዕትነት ከናካቴው ዘንግተን ዓላማቸው በከንቱ እንዲቀር አንፈቅድም። ለሰብአዊ ክብር፣ ለሕግ የበላይነት፣ ለነፃነት እና ለእኩልነት ያለን ቁርጠኝነት መቼውኑም የማይናወጥ ነው። በሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች ይሁንታ ያልተመሰረተ ሕገ-ወጥ የጭቆና አገዛዝ ሥርዓት እንዲሰፍን ከቶ አንፈቅድም፡፡ እስከመጨረሻውም እንታገለዋለን፡፡ 

ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በሀገሪቱ የሚስተዋለው የፖለቲካ እና የጸጥታ ቀውስ በፍጥነት እየተባባሰ ሄዶ የመንግስትን ብቻ ሳይሆን የሀገሪቱንም ህልውና ጭምር አደጋ ላይ ጥሏል። የዘር ማጥፋት መገለጫ የሆኑ የግፍ ወንጀሎች በትግራይ፣ በኦሮሚያ፣ በቤንሻጉል ጉሙዝ እና በቅማንት ህዝቦች ላይ ተፈጽሟል። መንግስት በትግራይ የመገናኛ አገልግሎትን ጨምሮ ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶችን ወደነበሩበት ለመመለስ ፈቃደኛ ባለመሆኑ እንዲሁም የምግብ እና አስፈላጊ መድሃኒቶች አቅርቦት የሚመቻችበት ሁኔታ እንዳይኖር በማድረጉ እየተፈጸመ ያለው ግፍ የዘር ማጥፋት ወንጀል ሊባል በሚችል ደረጃ ደርሷል። በአፋር እና በሶማሊ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈጠሩ ግጭቶች የበርካታ ሰዎችን ህይወት ሲቀጥፍ በስልጣን ላይ ያለው አገዛዝ ሁኔታውን በቸልተኝነት ሲመለከት እንደነበር የቅርብ ግዜ ትውስታችን ነው፡፡ 

የእርስ በርስ ጦርነቱ አላስፈላጊ ደም መፋሰስና ተጨማሪ ሰብዓዊ አደጋዎችን ያስከተለ ቢሆንም፣ መንግሥት ፖለቲካውን ወታደራዊ ለማድረግ ቁርጠኛ የሆነ ይመስላል። ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች ከህግ አግባብ ውጭ መታሰራቸውን ቀጥለዋል፡፡ ይባስ ብሎም የጸጥታ ሃይሎች የትግራይ እና ኦሮሞ ተወላጆችን ከሌላው ማህበረሰብ በመነጠል ወደ ማጎሪያ ካምፖች እየከተቷቸው ይገኛል፡፡ “የህግ ማስከበር ዘመቻ” ተብሎ የተጀመረው ወታደራዊ ዘመቻ ክእርስ በርስ ግጭት አልፎ ንፁሃን ዜጎች ካለፍርድ ተይዘው ወደሚሰቃዩብት፣ ወደሚገደሉበት ህግ አልባ ሁኔታነት ተቀይሯል። በሀገሪቱ ውስጥ እየተካሄደ ያለው ጦርነት ክልላዊ ግጭት እና አስከፊ ሰብአዊ ቀውስ መፈልፈያ ሆኗል። ቀውሱም ጦርነቱን በደገፉት አገሮች (ኤርትሪያ፣፣ዩኤኢ፣ቻይና እና ቱርክ)ሳቢያ ዓለም አቀፋዊ መልክ ይዞ ይገኛል፡፡ ለኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ የፖለቲካ ችግሮች ወታደራዊ አማራጭ መፍትሄ ሊሆን እንደማይችል ግልጽ ነው። በተቃራኒው፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ጦርነት ተባብሶ መቀጠሉ ሀገሪቷን ለከፋ ውድቀት፣ ህዝቦቿንም ለጥልቅ ችግር መዳረጉ አይቀሬ ነው፡፡ በዚህም ሳቢያ ኢትዮጵያ ወደ ከፋ ግጭትና መቆሚያ አልባ ቀጠናዊ ብጥብጥ እንዳትገባ ያሰጋል። ይህንን አሰቃቂ ክስተት ለማስወገድ በጎ ፈቃድ ያላቸው ሰዎች እና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጣልቃ በመግባት የበኩላቸውን ሀላፊነት እንዲወጡ ጥሪያችንን እናቀርባለን። 

  1. የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች አብሮነት ጸንቶ እዲቀጥል የተጠናከረ ትብብር፤ የጋራ አጀንዳዎች መጎልበት እና የጋራ ሰላም ግንባታን ማጠናከር ይጠበቅብናል። በአሁኑ ሰዓት በተጋሩ እና ኦሮሞዎች ላይ ያነጣጠረውን ግፍ ሁላችንም ልንቃወመው ይገባል፡፡ ዛሬ ተባብረን ግፍና በደልን ካልተቃወምን ነገ እያንዳንዳችን ሰለባ ላለመሆናችን ምንም ዋስትና አይኖረንም። ይህ ታዋቂው የማርቲን ኒሞለር ታሪካዊ ንግግር ይህንኑ ሁኔታ ጠቋሚ ነው፥ “ናዚዎች ኮሚኒስቶችን ሊወስዱ ሲመጡ እኔ ኮሚኒስት ስላልሆንኩ ዝም አልኩ። ሶሻል ዴሞክራቶች ሲታሰሩም ዝም አልኩ ፣ ምክንያቱም እኔ ሶሻል ዲሞክራት አልነበርኩም። በመቀጠል የሠራተኛ ማኅበር አክቲቪስቶችን መፈለግ ሲጀምሩ እኔ የሠራተኛ ማኅበር አክቲቪስት ስላልሆንኩ አልተቃወምኩም። አይሁዶችን ለመውሰድ ሲመጡ እኔ አይሁድ ስላልሆንኩ ምንም አላልኩም። በመጨረሻ ወደ እኔ ሲመጡ ለኔ ድምጹን ሊያሰማልኝ የሚችል የቀረ ሰው አልነበረም”። 
  1. በኢትዮጵያ እየተከሄደ ያለው የእርስ በርስ ጦርነት አሁን ዓለም አቀፋዊ ይዘት እንዲኖረው ሆኗል። የውጭ ተዋናዮች ለገዥው ብልጽግና ፓርቲ የጦር መሳሪያ እና ገንዘብ በማቅረብ ጦርነቱ ተባብሶ እንዲቀጥል ማድረጋቸው በተጨባጥ እየታየ ያለ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በእነዚህ ሀገሮች ላይ ጫና በማሳደር ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ግፊት የማድረግ ሃላፊነት አለበት። የዘር ማጥፋት ወንጀል እንዳይፈፀም ሁላችንም “በኛ ይብቃ” በማለት ተፈቃቅደንና ተባብረን እንድንኖር ተባብረን መስራት ይጠበቅብናል፡፡
  1. የሚኒስትሮች ምክር ቤት በቅርቡ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን እንዲቋቋም ውሳኔ ማሳለፉ ይታወቃል፡፡ ሆኖም ግን የኢትዮጵያ መንግስት በወቅቱ ያለውን ግጭት በማማባስ ላይ እያለና የሰበዓዊ መብት ጥሰት ወንጀል በሃገሪቷ የተለያዩ አከባቢዎች እየተከሰሰ ባለበት ሁኔታ ገለልተኛ ተቋም ያቋቁማል ማለት የህልም እንጀራ ነው፡፡ ስልጣን ላይ ያለው መንግስትም ሀገሪቱ የገባችበትን አዘቅት ተረድቶ ዘላቂ መፍትሄ ይፈልጋል የሚል እምነት የለንም፡፡ ሁሉን ያሳተፈ ሀገራዊ ውይይት፣ ሁሉን አቀፍ የሽግግር ስርዓትና ሁሉን አቀፍ ውይይት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ማለቂያ ከሌለው መከራና ዘር ማጥፋት የሚያድን እንዲሁም የአፍሪካ ቀንድን ወደ ትርምስ ቀጠናነት ከመውረድ ሊታደግ የሚችለው ብቸኛው መፍትሄ መሆኑን እናምናለን። አለም አቀፉ ማህበረሰብም በዚህ ሂደት ላይ ድጋፍ የማድረግ ሀላፊነት አለበት ብለን እናምናለን፡፡ 
  1. በሶማሊ ክልል የተከሰተው ተደጋጋሚ ድርቅ የማህበረሰቡን የመቋቋም አቅም አሽቆልቁሎታል፤ ማህበረሰባችንም ለከፋ አደጋ ተጋልጧል፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን በሚያሳዝን ሁኔታ የክልሉ መንግስት ሰብአዊ እርዳታ ለተጎጂው ማህበረሰብ ከማድረስ ይልቅ የተመደበውን በጀት ለምርጫ ማስኬጃነት እንዳዋለው የውስጥ ምንጮች ይጠቁማሉ፡፡ የክልሉ ባለስልጣናት ህዝብ ለማዳን ተጨማሪ በጀት ከመመደብ ይልቅ ሀብት በማሸሽ ተግባር ላይ መጠመዳቸውም ይስተዋላል። በመሆኑም ዓለም አቀፍ ተቋማት የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት አስቸኳይ የሰብአዊ ዕርዳታ እንድያደርጉ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡ 

የሶማሊ ጉዳይ ኮንግረስ 

ታህሳስ 06፣ 2014