የትግራይ ህዝብ መዋእል ከትግልና ከጀግንነት የተቆራኘ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። የትግራይ ህዝብ ብቻውን ሆኖም ይሁን ከሌሎች ኢትዮጵያውያን/ት ወገኖቹና ኤርትራውያን ወንድሞቹ በጋራ ከበርካታ የውጭ ወራሪዎችና ተስፋፊዎች ፊትለፊት ተጋጥሞ ጠላትን አሳፍሮ መልሰዋል። የራሱንና የሃገሩን ክብር አስጠብቋል። ይህ በታሪክ ድርሳናት የተከተበ ሃቅ ነው። ሆኖም ግን ይህ በመስዋእትነት የታጀበ አኩሪ ገድላዊ ታሪኩ በሚያሳዝን ሁኔታ በአንዳንድ ኢትዮጵያውያን ልሂቆችና ገዢዎች ዘንድ የሚገባውን ክብር አላሰጠውም። የትግራይ ህዝብ ግን ራሱን አውቆ የሚያከብር ከስሜታዊነት የራቀ በጊዚያዊ ትርፍም ኪሳራም ቦታውን የማይለቅ ህዝብ በመሆኑ እጅግ አስቸጋሪና ውስብስብ በሆነ የረጅም ጊዜ ታሪኩ ማንነቱን ጠብቆ ኖሯል። ሆኖም ግን በዚህ አጭር ጽሁፍ ለመዳሰስ በማይሞከሩ ውስብስብ ሰው ሰራሽ ችግሮች ምክንያት በአንድ ወቅት ከነበረበት ቁንጮ የስልጣኔ ማማ ወርዶ በድህነትና በኋላቀርነት ለመኖር ተገዷል።
በቅርቡ ባደረገው መራራ ብረታዊ ተጋድሎ በተጎናጸፈው ድል ምክንያት ወደነበረበት የስልጣኔ ማማና የሚገባውን ክብር ለመመለስ እርምጃ ለመጀመር የሚያስችሉ ሁኔታዎች ተፈጥረው ተስፋ መሰነቅ በጀመረበት ወቅት በራሱ አመራሮች በተፈጠሩ ድክመቶች እንዲሁም በታሪካዊ ተቀናቃኝ ሃይሎችና የጊዜን ሁኔታ ጠብቀው የሚነጥቁ የውስጥና የውጭ ጩሉሌዎች (opportunistic) ቡድኖች በጋራና በተናጠል በሰሩት አሻጥር የትግራይ ህዝብ ለተለያዩ ጥቃቶች ተጋልጦ ይገኛል። አሁንም ማንነቱን ለመጨፍለቅ፣ ክብሩን ለመግፈፍና የማደግና የመልማት ራእዩንና ጥረቱን ለማሰናከል በገዛ የራሱ ሃገር መንግስት ያውም ከድርሻው በእጅጉ የበዛ መስዋእትነት ከፍሎ ከውድቀት በታደጋት ሃገር የተቃጣበትን ያልተገባ ዙሪያ መለሽ ጥቃት እየተፈጸመበት ይገኛል። በቀጣይም ጥቃቱን የመንግስት ይሁንታ ምናልባትም ትብብር ጭምር በተሰጣቸው የተለያዩ ቡድኖች፣ የመንግስት ተቋማትና የውጭ ሃይሎች እየቀጠለ ይገኛል። አንዳንድ የዋሆች ወይም አውቆ አጥፊዎች ሃገር አይበድልም ይላሉ። ሃገር የሚወከለው በተቋማቱ ነው። በነዚህ ለጋራ ጥቅም በተቋቋሙ የተለያዩ የገንዘብ፣ የጸጥታ፣ የህግ፣ የንግድና ኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ እንዲሁም የህግ አውጭ ተቋማት በአንድ ህዝብ ላይ ጥቃትና በደል ሲፈጸም ሃገር እንደበደለ ይቆጠራል።
የትግራይ ህዝብም ይህንን በህልውናውና በደህንነቱ ላይ ያነጣጠር ውስብስብ አደጋ በአግባቡ በመገንዘብ እንደወትሮው አንድነቱን ጠብቆ ከመቼውም ጊዜ በላይ በመመከት ላይ ይገኛል። መላ ህዝቡና የክልሉ መንግስት በወሰዱት ፈጣንና ቆራጥ ዝግጅት ምክንያት የታሰበውን ጥቃት ለጊዜ ለማክሸፍ ችሏል። ለሚመጣውም በተጠንቀቅ ላይ ነው።
የትግራይ ህዝብ በታሪኩ ከጭቆና፣ ከድህነትና ኋላቀርነት ለመውጣት ባካሄደው የረጅም ጊዜ የትግልና የጀግንነት ጉዞ ውስጥ ጥቂት ተጋሩ ከዚህ በታቃራኒ ቆመው አሳፋሪና ወራዳ ተግባር መፈጸማቸው አሌ የማይባል ሃቅ ነው። በአብዛኛው ያልተሳካ የባንዳነትና ህዝብን ለጠላት አሳልፎ የመስጠት ይቅር የማይባል ታሪካዊ ስህተት የፈጸሙ ግለሰቦች በየዘመኑ ተፈጥረው እንደነበሩ ከታሪክ እናስታውሳለን። የትግራይ ህዝብም በየአጋጣሚው በማንሳት ለማስተማሪነት በሚሆን ልክ ድርጊታቸውን በቁጭት ያስታውሰዋል ለትውልድም ያስተላልፏል። አንዳንዶቹ ከጠላት የወገኑ ከሃዲዎች ታሪካቸውን ከማጠልሸት የዘለለ አደጋ ሊያደርሱ አልቻሉም። በቁጥር እጅግ ትንሽ የሆኑ ግለሰቦች ግን በተለያዩ ወቅቶች በትግራይ ህዝብ ላይ ታሪክ ይቅር የማይለው በደል ፈጽሟል። ይህ ክህደትም በተለያዩ የታሪክ ምዕራፎች አጋጥሟል። ከነዚህ ጥቂት ለግል ስልጣን ወይም በተራ ቂምበቀል ወይም በድንቁርና ታውረው ለጠላት ያደሩ የውስጥ መረጃዎችን ለጠላት አሳልፈው የሰጡ ወይም በቀጥታ ተሰልፈው የትግራይን ህዝብ የወጉ፣ ያደሙና ለታሪካዊ ውርደት የዳረጉ አንዱ ሓንታ ገብሩ እንደሆኑ በታሪክ ተዘግቦ ይገኛል። (ለማጣቀሻነት መምህር ገ/ኪዳን ደስታ (2010) አፄ ዮሃንስና አፄ ምኒልክ በኢትዮጵያ ታሪክ መነፅር፥ ገጽ 50 ይመልከቱ)። በቅርቡ የ17 ዓመታት መራራ የትጥቅ ትግል ወቅትም ተመሳሳይ ክህደት የፈጸሙ መኖራቸው በቅርብ የምናውቀው ነው።
በከሃዲነት ወይም ባንዳነት የሚፈረጁት የትኞቹ ወይም ምን የበደሉ ናቸው? መልሱ አወዛጋቢ እንደሚሆን መገመት አያስቸግርም። ለአንባቢ ግልጽነት ይሁን ለትችት እንዲመች ወይም ለተወሰነ መግባቢያነት እንዲበጅ የጸሃፊው አተረጓጎም እንደሚከተለው ነው። በጸሃፊው አረዳድ በዓላማ ወይም በፖለቲካ አመለካከቱ ልዩነት ወይም በደል ደርሶብኛል በሚል ምክንያት ከትግሉ ራሱን ያገለለ ወይም በፖለቲካ ርዕዮቱ ምክንያት በሰላማዊ መንገድ የተቃወመ በክህደት አይፈረጅም (በዚህ ጽሑፍ በወንድ ጾታ የተገለጸው ሴትንም ያካትታል)። ታዲያ ከሃዲነት ምንድነው? የተለየ አቋም ከማራመድ ወይም ጎራ ለይቶ ከመታገል በምን ይለያል? ጉዳዩ በጊዜና በገቢራዊ ጭብጥ ልክ አንጻራዊ ትርጉም ሊኖረው ይችላል። በመሰረተ ሃሳብ ብቻ ከተወሰደ የአንድ ወቅት ከሃዲ በሌላ ጊዜ ጀግና ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። በተመሳሳይ መልኩ ላንዱ ከሃዲ ለሌላው ጀግና ሊሆንም ይችላል።
ጸሃፊው የትርጉሙን አሻሚነት ለመቀነስ ይረዳ ዘንድ ከተነሳው ውስን ጭብጥ ልክ ብቻ በጠባቡ ለመተርጎም ጥረት አድርገዋል። እንደጸሃፊው እምነት በጎራ ልዩነት ከኢህአፓ ወይም ከደርግ የወገኑ ሁሉ በአሰላለፋቸው ባይስማማም በያዙት አቋም ብቻ በከሃዲነት አይፈርጃቸውም። ይልቁንም የትግራይን ህዝብ መብቱን ለማስከበር ወይም ህልውናውን ለማረጋገጥ በሚያደርገው ትግል በማናቸውም ሰበብ ከጠላት ጎን ተሰልፈው በሃይል ወይም በጦር የሚወጉ፣ የሚሰልሉ (ቁልፍ መረጃ አሳልፈው የሚሰጡ)፣ ከፍተኛ የፖለቲካና የኢኮኖሚ አሻጥር የሚሰሩ/የሚያሰሩ፣ በተለያየ ምክንያት ህዝቡን እርስ በርሱ በማጋጨት አንድነቱን በመናድ ለተሸናፊነት የሚዳርጉና መሰል ጥፋቶችን የሚፈጽም ማንኛውም ትግራዋይ ክህደት እንደፈጸመ ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል የሚል እምነት አለው ጸሃፊው። ይህ በጣም አሻሚ ሊሆን ይችላል። የተሰጠው ትርጉም ከመደበኛ የህግ ትርጉም ጋር ሊጋጭ ይችላል። ጸሃፊው ግን አሁን ካለንበት ፈታኝ ወቅት አንጻር ከመሰረታዊ የትግራይ ህዝብ ዘላቂ ጥቅም ብቻ መታየት እንዳለበት ያምናል። ለዚህም ከህግ ትርጉም ይልቅ ፖለቲካዊ ትርጉም ሊሰጠው ይገባል። የራሱን ማንነት ጠብቆ/አስጠብቆ በነጻነት የመኖር፣ የመልማት፣ የማደግ፣ የሰላምና ደህንነቱን የመጠበቅና የማስጠበቅ እና ሌሎችም መብቶች በተጻራሪነት ቆሞ ለመጨፍለቅ በሚደረግ የጠላት ጥቃትና በደል ወግኖ በመሰለፍ ያጠቃ ወይም ጥቃት እንዲፈጸም ያደረገ በከሃዲነት አለፍ ሲልም በጠላትነት መፈረጅ ይኖርበታል። በዚህ ጎራ የተፈረጀ ደግሞ ምን መደረግ እንዳለበት የታወቀ ነው። እንዳመጣጡና እንደአሰላለፉ ልክ መመከት አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ተመጣጣኝ አጸፋዊ ምላሽ መስጠት! በጅምላ ሳይሆን ነጥሎና አነጣጥሮ! ይህ እብሪትም (violence) ጀብደኝነትም ጭፍንነትም አምባገነንትም ዘረኝነትም ወይም በሃገራችን ፖለቲካ/ሚዲያ እንደተለመደው ሌላ ተቀጽላ ስም የሚያሰጥ አይደለም። በፍጹም! በክፉ ጊዜ፣ ህልውና አደጋ ላይ ሲወድቅ ጠላት ሃይልን ተጠቅሞ ህዝብን እንደ ህዝብ ለማንበርከክ ዘመቻ ሲከፍት (በሃይል/በአሻጥር) ራስን ለመከላከል በሚደረግ ትግል የሚወሰድ ትክክለኛና ሞራላዊ ድርጊት ነው። ላይወደድ ይችላል። ከ“ወገን” ጋር የሚደረግ ፍልሚያ በመሆኑ ሊወደድም አይችልም። ይልቅ ሳይወዱ በግድ የሚገባበት አሳዛኝ ትግል ነው።
ጸሃፊው ይህንን ደስ የማይል ነገር ግን ሊጋፈጡት የሚገባ የዘመናችን አደገኛ የክህደት ክስተት ብቅ ጥልቅ እያለ በመሆኑ ሳይቃጠል በቅጠል እንዲሉ በወቅቱ ግንዛቤ እንዲወሰድበት፣ ምክርና ተግሳጽ እንዲሰጥ፣ በወቅቱ እንዲታረምና አደጋውን ከታሪክና ከተጨባጭ ህሉው ኩነቶችና አቅጣጫዎች አንጻር በመገምገም በየጓዳው የምናወራውን ስጋት በአደባባይ በማውጣት የድርሻውን ለማለት ነው። በቅርቡ በተወሰኑ የትግራይ ክልል አመራሮች በተለይ በዋና አስተዳዳሪው ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል “ባንዳ” የሚል ቃል መጠቀማቸው በወቅቱ እጅግ አነጋጋሪ ጉዳይ ሆኖ እንደነበር በተወሰኑትም በአጨቃጫቂነቱ እንደቀጠለ ነው። ጸሃፊውም በወቅቱ ትግራይ ውስጥ በነበረው የፖለቲካ ትኩሳትና የተወሰነ መደበላለቅ ምክንያት የህዝቡን አንድነት ሊጎዳ ይችላል ከሚል ስጋት የቃሉ መጠቀም በበጎ ጎኑ አላየውም ነበር።
አሁን ባሉት ህልው ኩነቶች ሲመዘን ግን ተገቢነቱ ያመዘነ እንደሆነ ጸሃፊው ይገነዘባል። ማነው ከሃዲ በሚለው በተግባር በትክክል በመተግበሩ ጉዳይ ግን ጸሃፊው አሁንም ስጋት አለው። ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው በክህደት ጎዳና የተሰለፉትን መለየትና ማጋለጥ ያለብን በተራ የፖለቲካ ወይም የርዕዮት ልዩነት ሳይሆን ከትግራይ ህዝብ ጥቅምና ከተጋረጠበት የህልውና አደጋ አንጻር በጥንቃቄ ነጥሎና በአስተውሎት መሆን ይኖርበታል። ሆኖም ግን በዚህ አተረጓጎም መሰረት ከህወሓት ጋር ቅራኔ ወይም ጥላቻ ስላለው ወይም ህወሓት በድሎኛል በሚል ወይም በማናቸውም የጎራ መለያየት ምክንያት ብቻ በትግራይ ህዝብ ላይ ጥቃት መፈጸም ወይም እንዲፈጸም መርዳት፣ ከጠላት ጋር ተሰልፎ አሻጥር መፈጸም ወይም እንዲፈጸም መርዳት ወይም መሰል በደል መፈጸም ተቀባይነት የለውም። በአንጻሩ ግን ከላይ በተገለጹት የጎራ መለያየት ምክንያት አቋም መያዝ፣ እምነቱን/ተቃውሞውን መግለጽ በአጠቃላይ ሰላማዊ ትግል ማድረግ በከሃዲነት መፈረጅ ትክክል አይሆንም አይገባምም።
ክፉ ዘመን ለብዙ ችግር ማጋለጡ አይቀርም። በመከራና ለአደጋ በተጋለጡበት ጊዜ እንኳን ጠላት ወዳጅም ፊቱን ያዞራል። ወገንም እንደ ጴጥሮስ ሶስት ጊዜ ሳይሆን ሰባት ጊዜ ሊክድ ይችላል። ሰው ማለት ሰው ሆኖ የሚገኝ ነው ሰው የጠፋለት እንደተባለው የወገን ቁርጠኝነትም የሚለካው በቁርጥ ጊዜ ነው። አርቲስቱ እንዳለው አርቲስትዋም እንደደገመችው “ዘይዓረኻ ዓሪ ….. ኣብ ቁርጺ እዋን ተመዓራረ” ነው።
ታዲያ የህዝቡ ጥሪ አልገባ ብሏቸው ይሁን ጊዚያዊ ወንበር አጓጉተዋቸው ወይም ምን ያለው ዝላይ አችልም ሆኖባቸው እንዳይታሰሩ ፈርተው ብቻ እነሱ በሚገባቸው ምክንያት የዘመናችን “ሓንታ ገብሩ” ለመሆንና ለክህደት በአደገኛ የቁልቁለት መንገድ በመንደርደር ላይ እንደሆኑ ጸሃፊው ይታዘባል። በርግጠኛነት ተሸናፊነት ከሚያከናንባቸው የውርደትና የክህደት ጎዳናና ድርጊት ወጥተው የህዝቡን ደህንነትና ጥቅም በሚያስከብር ተግባር እንዲሰለፉም ጸሃፊው በታላቅ አንክሮና ተማጽኖ ሊጠይቃቸው ይፈልጋል። አንዳንዶቹ ደግሞ የትግራይ ህዝብ ላይ እየተቃጣ ያለውን አደጋ በመቀልበስ ብቻ ሳይሆን ምኒልክ ቤተመንግስት ተቀምጦ ሃገር በማመስ ላይ ከሚገኘው ቡድን በተለይ ደግሞ ከአውራው ጋር ካላቸው ዘለግ ያለ ጓደኝነት ወይም ጊዚያዊ ታክቲካዊ ጉድኝት አንጻር ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦች ሊጠቅም የሚችል ተግባር ሊያከናውኑ ወይም ተጽእኖ ሊፈጥሩ የሚችሉ በመሆኑ ሳይረፍድ ራሳቸውን ሊፈትሹ ይገባል። ክህደት ምናልባት ምናልባት እንደጤዛ የሚተን ጊዚያዊ ጥቅም ያስገኝ ካልሆነ በስተቀር ከታሪክ እንደምንማረው መጨረሻው ውድቀት ውርደት ሃፍረት ብቻ ነው። ህዝብን መካድና ለጠላት አሳልፎ መስጠት በወንጀልም በታሪክም ያስጠይቃል! ወገን ጊዜ ያልፋል ክፉ ስራ ግን ታሪክ ሆኖ እንደእግር እሳት ሆኖ ሲያቃጥል ይኖራል። ህዝብን የካደ ደግሞ መቼም ቢሆን የሽንፈት ጽዋ ይጎነጫል። ከሁለት ጥፋት መጠንቀቅ ያሻል። የትግራይ ህዝብ በራሱ አንድነትና አቅም እንዲሁም በወዳጆቹ ድጋፍና አጋርነት የሚጠይቀውን ዋጋ ከፍሎ ማንነቱን፣ ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብቱን፣ ልማቱንና ዕድገቱን ለማስከበር የሚያደርገውን ትግል በድል እንደሚወጣ ጥርጥር የለውም። “ትግላችን ረጅምና መራራ ነው ድል ማድረጋችን የማይቀር ነው” ብለን በቃላችን መሰረት እንደተገኘን ሁሉ አሁን ደግሞ “ትግላችን አጭርና መራራ ነው ድሉም የኛው ነው” ብለን በድጋሚ ቃላችንን ጠብቀን እንገኛለን።
ፋቶ (ምዕራፍ ጻድቃናት)
21 ጥር 2012 ዓ/ም
http://aigaforum.com/amharic-article-2020/the-current-hanta-gebrus.htm