“የኢትዮጵያ ችግር በፌደራሊዝምም ሆነ ብአሃዳዊ የመንግስት መዋቅር የሚፈታ አይደለም”

ፌደራሊዝም ምንድነው? ከሚል ጥያቄ ስንነሳ በትግራይ የሳልሳይ ወያነ ፓርቲ የሕግ ክፍል ሃላፊ የሆነው ኣቶ ተስፋኣለም እንዲህ ይመልሳል።

“ፌደራሊዝም ማለት በ ኣንድ ሃገር ውስጥ ወይም በ ኣንድ ግዛት ውስጥ ሁለት የተለያየ ስልጣን ያላቸው መንግስታት ሲኖሩ ማለት ነው። እነዚህ መንግስታት የየራሳቸው የ ፖለቲካ፣ ፋይናንዊና ኣስተዳደራዊ ክፍፍል ይኖራቸዋል። በፌደራሊዝም ስርዓቱ ደግሞ የግድ በፅሑፍ የተቐመጠ የክልሎችና የ ማእከላይ መንግስቱ ስልጣን በግልፅ የሚያስቀምጥ ሕገ መንግስት ሊኖር ይገባል።

ፌደራሊዝም በ ሁለት መንገድ ሊፈጠር ይችላል። ኣንደኛው የተላያዩ ሃገራት በ ስምምነት ወደ ኣንድ ሲመጡ ሲሆን ሉኣለዊ የነበሩና የራሳቸው ስልጣን የነበራቸው ሃገራት ኣንድ ሃገር ሲሆኑ ነው። ሁለተኛው ደግሞ በ ኣሃዳዊ ስርዓት ስትተዳደር የነበረች ሃገር የየራሳቸው ስልጣን ያላቸው ክልላትና ፌደራላዊ መንግስት ስትፈጥር ነው።

ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ በሃገሪቷ በተለያዩ ግዚያት የነበሩት ስርኣቶች ባህሪያቸው ኣሃዳዊ ነው። ያ ኣሃዳዊ ስርዓት ፈርሶ ነው የፌደራሊዝም ስርኣት የተተከለው። ቢሆንም ግን ኢትዮጵያ ውስጥ የታነፀው ፌደራሊዝም ሁለት ኣበይት ችግሮች ኣሉበት። ኣንዱ ፅንሰ ሃሳቡ ራሱ ሲሆን  ሁለተኛው ደግሞ ኣተገባበሩ ላይ ችግር ኣለበት። ሁለተኛው ደግሞ ዋና እና መሰረታዊ ነገሮች ናቸው።

ለ ማእከላይ መንግስት ትልቁን ኢኮነምያዊ፣ ፖለቲካዊና ወታደራዊ ስልጣን የሚሰጥ፣ ጉልበተኛ ማእከላይ መንግስት እንዲፈጠር የሚያደርግ ሕገ መንግስት ነው ያለን። የተፈጠረው ሕገ መንግስት በ ኣሃዳዊው ስርዓት ወቅት ጥያቄ ያነሱ ብሄሮችን ዝም ለማስባል ትንሽ ስልጣን በመስጠት ከ ክልሎች የሚነሳን ተቃዉሞ ለማርገብ የተቋቋመ ነው። የ ሃይል ሚዛኑ በጣም ከፍተኛ የሆነ መንግስት የፈጠረው ኣይነት ነው።

ከታሪክ ተነስተንም ስናይ ሁልግዜ ክልላዊ ወይም ዞባዊ ሃይሎች ኣሸንፈው የፈጠሩት ፌደራሊዝም ክልሎቹ ጠንከር ያለ ስልጣን እንዲኖራቸው ማእከላይ መንግስቱ ደግሞ ኣነስ ያለ ስልጣን እንዲኖረው ሆኖ ነው የሚፈጠረው። ኢትዮጵያ ውስጥ የሆነው ግን በተቃራኒው ነው። ክልሎች ኣሸንፈው ሲያበቁ ሐያል ማእከላይ መንግስት እና ደካማ ክልሎች እንዲፈጠር ነ ያደረጉት።

ቢያንስ ቢያንስ እንኳን ማእከላይ መንግስቱና ክልሎቹ ሚዛናቸውን የጠበቁ እና ተመጣጣኝ ሃይል ያላቸው ሊሆኑ ይገባ ነበር” ይላል።

ኣቶ ተስፋኣለም በመቀጠልም “ኣተገባበሩ ላይ ስንመጣ ደግሞ፡ ኢህአዴግ የሚባለው ኢትዮጵያን ለ 27 ዓመታት ያስተዳደረ ፓርቲ ርእዮተ ኣለሙ ኣብዮታዊ ዲሞክራሲ ነው። ኣብዮታዊ ዲሞክራሲ በባህሪው ደግሞ ማእከላዊነትን የሚያራምድ ርእዮተ ኣለም ስለሆነ በ ኣፈፃፀሙ ክልሎቹ በጣም ደካማ እንዲሆኑ በማድረግ ሕገ መንግስቱ ራሱ ተግባር ላይ ያልዋለበት ነው የሆነው። ጠንካራ ክልሎች ኣለመፈጠራቸው ነው ሃገሪትዋን ወደ ቀውስ የከተታት።” ይላል።

ኣቶ ተስፋኣለም ፌደራሊዝሙ በትክክል ከተተገበረ ኣሁንም ኢትዮጵያ ውስጥ ሊተገበር ይችላል ወይ? ለሚለው ጥያቄ እንደሚከተለው ይመልሳል።

“በመሰረቱ ኢትዮጵያ ውስጥ እየታየ ያለው ችግር ፖለቲካዊ ችግር ብቻ ኣይደለም። ፖለቲካዊ ችግር ብቻ ስላልሆነ ደግሞ ስርዓተ መንግስት በመቀየር ወይም ፌደራላዊ ስርዓት በመዘርጋት የሚፈታ ኣይደለም። ለምሳሌ ኣሁን ትግራይ ላይ  ጦርነቱ ያወጁ ሃይሎች ፌደራላዊ ስርዓቱ እንዲቀጥል ኣይፈልጉም። ፌደራሊዝሙን ራሱ ስርዓት ባለው መንገድ ሊቀይሩት ኣይፈልጉም። ኣፓርታይድ ስርዓትም እኮ ሕገ መንግስት ነበረው።

ደቡብ ኣፍሪካውያንን በገዛ ሃገራቸው ሁለተኛ ዜጋ ሆነው ወረራ እንዲፈፀምባቸው ሲደረጉም ወራሪዎቹ ሕገ መንግስት ነበራቸው። ነገር ግን ደቡብ ኣፍሪካውያን ነፃነታቸውን ሲያገኙ ሕገ መንግስቱን ኣልጣሉትም። ኣብረው እንዲኖሩ የሚያስችላቸው መንገድ ኣሻሻሉት እንጂ። እኛ ሃገር ግን ሕገ መንግስቱ እንዲሻሻል ራሱ ፍላጎት የለም። ሕገ መንግስቱን እንዳለ ኣጥፍቶ ኣሃዳዊና ጨፍላቂ ስርዓት እንዲፈጠር ነው የሚፈለገው። ያ በ ኢትዮጵያዊነት ስም ሊተገበር የሚፈለገው ስርዓት ሸዋን ማእከል ያደረገ መንግስት ነው።

ድሮ ትግራይን ወይም ኣክሱምን ማእከል ያደረገ መንግስትነት ነበር። ኣሁን ያለው ግጭት ማነነታዊ ግጭት የፈጠረው ነው። በሁለት ማእከላት ወይም Two core states ላይ የተፈጠረ ማንነታዊ ግጭት ነው። ይህ ደግሞ በፌደራሊዝምም ይሁን ብ ኣሃዳዊነት ሊፈታ የማይችል ነው። በስርዓተ መንግስት ሊፈታ የሚችል ኣለመግባባት ኣይደለም። ምክንያቱም እዚህ ጋ እየሆነ ያለው ኣንዱ ማንነት ጎልቶ እንዲወጣ ሌላኛው ደግሞ እንዲጣፋ የሚደረግ ትግል ነው። ይህ ደግሞ ፈፅሞ ሊሆን የማይችል ነገር ነው” ሲል ይገልፃል።

ከዚህ ቀደም እውቁ የኦሮሞ ኣክቲቪስት ኣቶ ጃዋር መሓመድ “እኔ እንደ ኣንድ ኦሮሞ ማንነቴ እንዲጎላ እፈልጋለሁ፣ ቋንቋዬ እንዲያድግ እፈልጋለሁ። ባህሌ በ ኣለም እንዲተዋወቅ ኣፈልጋለው። ኦሮሞኣዊ ማንነቴ ኢትዮጵያ ውስጥ ተከብሮ ማየት እፈልጋለሁ ይህ የትግራዩም የ ሌላዉም ፍላጎት ነው ብዬ ነው የማምነው ሲል ተደምጦ ነበር።”

ሌላው ትግራይን ሃገር ለማድረግ የሚንቀሳቀስ ‘ዉናት’ ተብሎ የሚጠራው የፖለቲካ ፓርቲ ሊቀ መንበር የሆነው ኣቶ ግርማይ በርሀ “ኢትዮጵያ ለኔ እንደ ኣንድ ትግራዋይ ምን ትየቅመኛለች በሚል ነው የምመዝናት። መጀመርያ እኔ ብሄራዊ ጥቅሞቼን ወይም ፍላጎቶቼን ዘርዝሬ ኣስቀምጫለሁ። ታድያ ኢትዮጵያ ለእነዚህ ብሄራዊ ጥቅም እና ፍላጎቲቼ ምን ትጠቅመኛለች በሚል ነው የምመዝናት” ይላል።

ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ግዚያት ስለ ፌደራሊዝም በተካሄዱ ፖለቲካዊ ውይይቶች ላይ ሁለት ሃሳቦች ይነሳሉ። ኣንደኛው ሃይል “ኢትዮጵያ ውስጥ የፌደራሊዝም ስሪኣቱን የማይቀበሉ ኣሃዳዊ ስርዓት ተመልሶ እንዲመጣ የሚፈልጉ ሃይሎች ኣሉ” የሚል ኣካል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ” የለም! ኢትዮጵያ ውስጥ ኣሃዳዊ ስርዓት ተመልሶ እንዲመጣ የሚፈልግ ሃይል የለም። እስቲ ኣንድ ቋንቋ፣ ኣንድ ባህል፣ ኣንድ ማንነት የሚል በግልፅ ወጥቶ የሚቀሰቅስ ሃይል ውይ ፖለቲካዊ ሃይል ጥሩ” ሲሉ ይሞግታሉ።

ይሄን ኣቶ ልደቱ ኣያሌው መቐለ በተካሄደው የፌደራሊዝም ውይይት ላይም ኣንስተዉት ነበር። ሆኖም ፓርቲ መስርቶ ፖሊሲ ኣውጥቶ ኣሃዳዊነትን በ ኣደባባይ የሚሰብክ ህጋዊ ፓርቲ ባይኖርም ኢትዮጵያዊነት በሚል ስም ኣሃዳዊነት እንደሚሰበክ ግን ብዙ ፌደራሊስት ሃይሎች ያነሳሉ። ለዚህ እንደ መንገድ የሚጠቀሙበት ደግሞ የውሸት ትርክቶችን በመፍጠር ህዝብን ማወናበድ እና ማጭበርበር ኣንደኛው ነው። ታላቅ ነበርን ታላቅም እንሆናለን፣ ታሪክና ክብራችንን እናስመልሳለን፣ ኢትዮጵያን ማፍረስ የሚፈልጉ ይፈርሳሉ እንጂ ኢትዮጵያ ኣትፈርስም የሚሉ የሌላውን ማንነት በሚያፈርሱ ሃይሎች የሚባል ነገር ነው።

ሁለተኛው ደግሞ ርስት በሚል ኣባዜ ዘልኣለሙን ግጭት ውስጥ መኖር የሚፈልግ ሃይል መኖሩ ነው። ርስት ማስመለስ የሚል ሃሳብ በ ኣንድ በኩል ሌላው ክልል የራሱ መሬት እንዳይኖረው እና ራሱን በ እርሻና ኢኮኖሚ እንዳይችል ጥገኛ እንዲሆን የሚደረግ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በመሬት ይገባኛል ሰበብ የራስን ባህል፣ ማንነትና ቋንቋ ሌላው ላይ ለመጫን የሚደረግ ሴራ መሆኑ ነው።

በመቐለ ዩንቨርሲቲ የ ፖለቲካል ሳይንስ መምህር እና የ ትግራይ ነፃነት ፓርቲ መስራች መሓሪ የውሃንስ

“ሲጀምር ኢትዮጵያ ኢምፓየር ነች። ኢምፓየር ማለት ደግሞ ሃፀያዊ ግዛት ማለት ነው። ኢምፓየር ውስጣዊና ውጫዊ እድገቶች፣ ህልማቸው፣ ፍላጎታቸው፣ ታሪካቸው እና መንነታቸው የማይስማማ ብሄሮች በ ኣንድ ግዛት ወይም ኣንድ ሃገር ጠቅልሎ የሚይዝ ህዝባዊ ያልሆነ ስርዓት ማለት ነው።  ህዝባዊ ያልሆነ ስንል ደግሞ እነዛ ህዝቦች እርስ በ እርሳቸው የማይተዋወቁ፣ የሚያመሳስል ነገር የሌላቸው በመሆናቸው ካለፍቃድ እና ፍላጎታቸው በሃይልና በማጭበርበር ሳያምኑበት ኣብረው የሚኖሩበት ሁኔታ ነው። ውጤቱ ደግሞ በማያበራ ግጭት ኛ ኣለመግባባት ውስጥ መኖር ነው።

የ ገዢ ሃይሎች ፍላጎትና ጥቅም ላማሟላት ሲባል የማይስማማ ህልም እና ኣላማ ያላቸውን ብሄሮች ሳይፈልጉ እና ሳይግባቡ ኣንድ ላይ እንዲኖሩ ይደረጋሉ።

በ ኢምፓየራዊ ሰርዓት ውስጥ ያሉት ህዝቦች ብሄራዊ ፍላጎታቸው፣ ሃገሪቷ እንድትታነፅበት የሚፈልጉት መንገድ፣ ህልምና ኣላማቸው ኣንድ ሳይሆን በጥቕምና በዝምድና የተሳሰሩት ገዢዎቹ ግን ለስልጣናቸው ሲሉ ሰላም ሳይኖር ሰላም እንደሰፈነ፣ ፍቅር ሳይኖር ህዝቡ እርስ በእርስ እንደሚፋቀር ፣ ልማት ሳይኖር  ወይም ልማቱ ኣንድ ኣከባቢ ብቻ እያለና ሃብቱም ማእከላይ መንግስቱ ጋር ተከማችቶ እያለ በማስመሰል ነው ሃገሪትዋን ያቆይዋት። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው መሰረታዊ ግጭት ኣንዱ የ ኣንዱን ማንነት መጨፍለቅና መዋጥ መፈለጉ ነው።” ይላል።

ፌደራሊዝም ኢትዮጵያ ውስጥ ለምንድነው ያልተሳካው?

****

ኣሁንም የፖለቲካል ሳይንስ ሙሁሩ መሓሪ የውሃንስ ሲመልስ፡

“በመሰረቱ ብዙሓነት (Diversity) ፀጋ ኣይደለም። ልዩነቱ የሃሳብ ከሆነ ችግር የለውም። ልዩነቱ የብሄር  ከሆነ ግን ኣንድ ኣይነት ህልም፣ ኣንድ ኣይነት ፍላጎት እና ኣንድ ኣይነት ኣላማ የሌላቸው ብሄሮች ኣብረው ሲኖሩ በ ፌድራሊዝምም ይሁን በሌላ መንገድ ዘላቂ መፍትሄ ሊመጣ ኣይችልም። ይህ ባህሪያዊ ነው።

እያንዳንዱ ብሄር ኢትዮጵያን መገንባት የሚፈልግበት መንገድ የተለያየ ነው። ኣማራዉ የራሱ ፍላጎት ኣለው እሱን የምትመስል ኢትዮጵያ ነው መገንባት የሚፈልገው፣ ኦሮሞው የራሱ ፍላጎት ኣለው።  ትግራይም ኢትዮጵያ ለሱ የምትጠቅም እንድትሆን ይፈልጋል ሌላውም ብሄር ተመሳሳይ። እውነት እናውራ ከተባለ ኮ ኢትዮጵያ ውስጥ ስልጣን የሚይዘው ፓርቲ ወይም ፖለቲካዊ ስነ ሃሳብ ሳይሆን ብሄር ነው። ትግራይ ስልጣን ላይ ነበር፣ ኦሮሞው ትግራይን ኣባሮ ስልጣን ያዘ።  ኦሮሞው ጉልበቱ ሲዝል ወይ በውስጥ ጉዳይ ሲታመስ ደሞ ሌላው እሱን ኣባሮ ስልጣን ይይዛል ኣዙሪት ነው።” ይላል።

ሰዎች በ ሃገሪቷ ውስጥ ልማት መጥቷል ይላሉ። የመጣው ልማት ግን የመንገድ እና የ ህንፃዎች ልማት ነው። እርስ በርሱ የሚጋጭ ህልምና ፍላጎት ያላቸው ብሄሮች ያላት ሃገር ደግሞ ውሎ ያድር ይሆናል እንጂ ወደ እርስ በእርስ ግጭት እና ኣንዱ ኣንዱን ለማጥፋት እንደሚነሳ እያየነው ያለን ጉዳይ ነው። ያኔ ለ ኣመታት የፈራው ሃብትና ልማት በወራት ግጭት ኣፈር ይሆናል። ሃገሪቷ ችግሩን ከመሰረቱ ካልፈታች ኣዙሪት ውስጥ ትኖራለች።

ኢትዮጵያ እንደ ዩጎዝላቭያ

*****

እንደ ኣውሮፓውያኑ ኣቆጣጠር በ 1918 እንደቆመች የሚነገርላት ዩጎዝላቭያ በ 1945 ስሎቪንያ፣ ክሮሽያ፣ ቦስንያ ሄርዞጎቪንያ፣ መቅዶንያ፣ ሰርብያና ሞንቴኔግሮ የተባሉ ግዛቶችን ይዛ እንደ ሶሻሊስት ሃገር በፌደሬሽን ቆመች።

በ 1980 ዎቹ መጨረሻ ላይ ትምክህተኞቹ የሰርብያ ብሄሮች እኛ የተማርንና ሃብታሞች ስለሆንን በ ማለት በሃገሪቷ ያሉት ፖለቲካዊ፣ ኢኮነምያዊ ስፍራዎችን ተቆጣጠሩ። የ ሰርብያውያን ኣካሄድ በሌሎቹ የሃገሪቷ ኣባል ፌደሬሽኖች ቁጣን ቀሰቀሰ። ማእከላይ መንግስቱ ደግሞ በሃገሪቱ በተለያዩ ክፍሎች የተነሳውን ህዝባዊ ዓመፅ ለመቆጣጠር በሚል ሃይል መጠቀም ጀመረ። የሚካሄዱ ህዝባዊ ሰልፎችን የሚድያ ሽፋን እንዳያገኙ ማድረግ እና ሁኔታውን በማፈን ችግሩ እንዳልተፈጠረ ለማድረግ ሞከረ።

ብዙዎች የ ኢትዮጵያና ዩጎዝላቭያ ታሪክ ኣይመሳሰልም። ዩጎዝላቭያ ስለፈረሰች ኢትዮጵያ ትፈርሳለች ማለት ኣይደለም ሲሉ ይደመጣሉ። ኢትዮጵያን ከ መሰረቱ የታነፀችበትን መንገድ ስንፈትሸው ግን ኣንድ ላይ ሊያቆማት የሚችል የጋራ ህልምና ፍላጎት ያላቸው ህዝቦች እንደሌሉዋት እንገነዘባለን።

ልግዜው ወደ ብሄርተኝነት መድረክ የመጡ ብሄራዊ ፍላጎትና ህልማቸውን በዝርዝር ያስቀመጡ ብሄራት ሶስትና ኣራት ሊሆኑ ይችላሉ። በግዜ ሂደት ግን ሁሉም ብሄር ኢትዮጵያ የምትባል ሃገር ውስጥ ሊመሰርተው የሚፈልገው ስርዓት የሱን ፍላጎትና ማንነት መሰረት ባድደረገ መልኩ ነው። በዚህ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ብዙ ብሄርና ብሄረሰቦች ያሉዋቸው ሃገራት እንደፈረሱ ታሪክ የሚነግረን ነገር ነው።

በመጨረሻም ፌደራሊዝም ኢትዮጵያ ውስጥ የማይሳካበት ምክንያት የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ መሓሪ የውሃንስ እንደሚከተለው ያቀርበዋል።

“በ ዓለም ላይ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ የ ኢምፓየር ግዛቶችና ኣስተዳደራዊ ስርዓቶች ላይ ኣንድም ሰላም፣ ዲሞክራሲና ልማት ያረጋገጠች ሃገር የለችም። ህገ መንግስቱ እና ፌደራላዊ ስርዓቱ ስልጣን ላይ ያሉ ሰዎች ህዝቡን ማጭበርበር ስልጣን ላይ እንዲቆዩ የሚያደርግ ስልት ነው። ስናጠቃልለው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ብዙህነት የህልም፣ የ እላማና ሃገሪትዋ በምን መልኩ ትታነፅ የሚል ልዩነት ስለሆነ ፌደራሊዝም የሚፈታው ግጭት ኣይደለም በመሆኑም ኢትዮጵያ የፈለገው ዓይነት ስርዓት ብትከተል እንደ ሀገር መቆም ኣትችልም” ይላል።