በ ደጀን የማነ
የፅሑፉ መነሻ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን (የኢኦተቤክ) ቅዱስ ሲኖዶስ ሓምሌ 9 ቀን 2015 ዓ.ም በትግራይ የሚከናወነውን የኤጲስ ቆጶሳት ሹመት በማስመልከት ባወጣው መግለጫ፣
“ሹመቱ የሕገ ቤተ ክርስቲያንና አንቀጽ 37 እና 38 ያላከበረና ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን አንጻር ተገቢ ያልሆነ የቤተ ክርስቲያንን ማዕከላዊነት የሚጥስ፣ የቤተ ክርስቲያንን አንድነት የሚጎዳ . . . በመሆኑ . . . የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ እና ክቡር አቶ ጌታቸው ረዳ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት እንዲሁም የፌዴራልና የክልሉ መንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እየተደረገ ያለውን ሕገ ቤተ ክርስቲያንን ያልተከተለ የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ እንዲያስቆሙልን ብሎም ሰላም ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት በመደገፍ ችግሮቹ በውይይት እንዲፈቱ መንግሥታዊ እገዛ በማድረግ የውይይት መድረክ እንዲያመቻቹልን . . . “ ሲል ጥሪ ኣቅርቧል። ጥሪው በቅዱስ ሲኖደሱ ምልአተ ጉባኤ ይሁንታ የተሰጠው መሆኑንም ይገልፃል።
እንግዲህ ይህ መንግስት በሃይማኖት ጣልቃ እንዲገባ የሚጠይቅ ጥሪ፣ ከእምነት ተቋም የማይጠበቅ ብቻ ሳይሆን፣ ዓላማዉ የትግራይ ኤጲስ ቆጶሳት ሹመት በማስፈራራት ለማደናቀፍ ነበር። ከፍ ሲል ደግሞ ሕጋዊ በመምሰል ቀኖናና ሕገ ቤተ ክርስቲያን አጣቅሰው በመላው ዓለም የሚገኙት ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እና ሕዝበ ክርስቲያኑ በመቀስቀስ፣ ያልተቋጨው የኢኦተቤክ ቤተ ክህነት ከጆኖሳይዱ በህይወት የቀረውን የትግራይ ህዝብ ከመድረ ገፅ የማጥፋት ፍላጎት ለማሳካት በይፋ ዘመቻ መጅመራቸውን የሚያሳይ ምልክት ነው። ይህ የኢኦተቤክ ቅዱስ ሲኖዶስ በምልዓተ ጉባኤው ጥቅምት 2007 ያፀደቀውን “ሕገ ቤተ ክርስቲያን” የጣሰው እና ሕገ ወጡስ ማነው፣ የሚለዉን ጥያቄ የተወሰነ ማብራሪያ በማቅረብ ለአንባብያን ማስገንዘብ የዚህ ፅሑፍ ዓለማ ነው።
ሕገ ወጡና ሕገ ቤተ ክርስቲያን የተላለፈው ማን ነው?
በዮሐንስ ወንጌል 21፡15-17 “ግልገሎቼን አሰማራ፡ ጠቦቶቼን ጠብቅ፡ በጎቼን አሰማራ” የሚለውን አምላካዊ አደራ፣ እንዲሁም በሐዋርያት ሥራ 20፡28 “በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ” የለውን የወንጌላዊው ምክር ወደ ጎን በመተው ያጸደቀውን ሕገ ቤተ ክርስቲያን ባለ ማክበርና ከ ተልዕኮው ውጭ በፖለቲካዊ ስራና በዘር ማጥፋት ዘመቻ የተዘፈቀው የኢኦተቤክ ሲኖዶስ ነው ሕገ ወጡ?
ወይስ
ሕገ ቤተ ክርስቲያኑ እየተጣሰ ስለ ሆነ ለዕቅበተ እምነት እንዲሁም በትንቢተ ሕዝቅኤል 34፡5 “. . . በጎቼ እረኛ በማጣት ተበተኑ፡ ለምድርም አራዊት ሁሉ መብል ሆኑ፡ ተበተኑም” እንዲል በፖለቲከኞችና በዘር አጥፊ የኢኦተቤክ ቤተክህነት አገልጋዮች ምክንያት፣ ከበረታቸው የጠፉት ምእመናን ለምሰብሰብና የተክኩላዎች ሲሳይ እንዳይሆኑ ለመጠበቅ “በጎቼን ጠብቅ” የሚለውን አምላካዊ ትእዛዝ ለማክበር በማቴዎስ ወንጌል 18፡ 15-17 “ወንድምህም . . . ቢበድልህ ውቀሰው። ቢሰማህ ወንድምህን ገንዘብ አደረግኸው፤ ባይሰማህ ግን፥ . . . ዳግመኛ አንድ ወይም ሁለት ከአንተ ጋር ውሰድ፤ እነርሱንም ባይሰማ፥ ለቤተ ክርስቲያን ንገራት፤ ደግሞም ቤተ ክርስቲያንን ባይሰማት፥ እንደ አረመኔና እንደ ቀራጭ ይሁንልህ . . .”
በሚለው መሰረት ከስሕተታቸው እንዲታረሙ በግል ብቻ ሳይሆን በአድባባይ ጭምር ከአንዴም ሶስቴ ጥሪ አቅርበው፣ `የትም አይደርሱም
` በሚል ትዕቢት ሰሚ በማጣታቸው አዲስ ሳይሆን ጥንታዊው፣ አማናዊውና ታሪካዊውን መንበረ ሰላማ ትንሳኤውን ያበሰሩ የትግራይ አባቶች ናቸው ሕገ ወጦች?
እነኝህን ጥያቄዎች ለመመለስ የኢትዮጵያ ሲኖዶስ የትግራይ አባቶች ለመክሰስ ያጣቀሰውን ሕገ ቤተ ክርስቲያን ምን ይላል የሚለውን ማየት ያስፈልጋል።
በ2007 ያፀደቀውን የሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጾች ምን ይላሉ?
1) በሕገ-ቤተ ክርስትያኒቱ አንቀጽ 4.1.1 ላይ የቤተ ክርስቲያን አርማ በተመለከተ “መደቡ ነጭ ነው” ቢልም ቤተ ክርስቲያኒቱ ግን ይህንን በመሻር ፖለቲካዊው “አረንጓዴ፣ ብጫ፣ ቀይ” መደብ በመጠቀም መንፈሳዊ የአደባባይ በዓላት በመጡ ቁጥር ፀብና ንትርክ በመጋበዝ በተደጋጋሚ የአገር ሰላም ለማደፍረስ ምክንያት ስትሆን አይተናል።
በተጨማሪም አንቀጽ 4.3 (ሀ) ላይ “ዓርማው የቤተ ክርስቲያኒቱ ሉዓላዊ ክብር መገለጫና መለያ ስለሆነ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር የሚገኙ የቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅር ጽፅፈት ቤቶችን ከዚህ አርማ በቀር ሌላ ሊጠቀሙ አይችሉም” የሚለውን ሕግ በመጣስ በፓትርያርኩ ጽህፈት ቤት፣ በጠቅላይ ቤተክህነቱ ጽህፈት ቤቶች፣ በአህጉረ ስብከቶች ጽህፈት ቤት አረንጓዴ ፣ ብጫ ቀይ መደብ ያለው ሕገ ወጥ አርማ ሲያውለበልቡ ይታያሉ።
2) የሕገ ቤተ ክርስቲያን መሰረታዊ መርሆዎች በሚለው ስር ገለልተኝነት በሚጠቅሰው በ አንቀጽ 8 (1) ላይ “በኢፌዴሪ ሕገ መንግስት አንቀፅ 11 እንደተገለጸው ቤተ ክርስቲያን በመንግስት ጉዳይ ጣልቃ አትገባም” ቢልም ቅሉ በሲኖዶሱ መግለጫ “. . . የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ እና ክቡር አቶ ጌታቸው ረዳ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት እንዲሁም የፌዴራልና የክልሉ መንግሥት የሥራ ኃላፊዎች . . .” ጣልቃ እንዲገቡ በግላጭ ጠርቷል።
ሲተኩስ በማንኪያ ሲቀዘቅዝ በእጅ እንዲሉ ሲኖዶሱ ጣልቃ ግባልኝ እያለው ያለው፣ ቤተ ክርስቲያን እያዳከመብኝ ነው ብሎ፣ አንዴ የኦሮሙማ መንግስት፣ ሌላ ጊዜ የብልፅግና ወንጌል ያራምዳል እያለ ለሚከሰው የፌዴራል መንግስትና፣ ተመልሶ አይመጣም እንዲሁም ፀረ ቤተ ክርስቲያን እና ፀረ ኢትዮጵያ ነው፣ ጁንታ ከሚገዛን ሴጣን ቢገዛን ይሻለናል የተባለለትን ህወሓት በአብላጫ ለሚመራው የትግራይ ጊዝያዊ መንግስት መሆኑ ስታይ፣ ሲኖዶሱ መርህ አልባ እንደሆነ መመልከት ይቻላል። በጣም የሚደንቀው መንግስት ጣልቃ እንዲገባ የሚማፀነው በትግራይ እና በኦሮሚያ ሲሆን ብቻ መሆኑን ደግሞ የሲኖዶሱ ልክ ያጣ መዋቅራዊ ዘረኝነት ማሳያ መሆኑን ያሳያል።
3) በአንቀጽ 8 (2) ላይ “ቤተ ክርስቲያን ዘርን፣ ብሔርን፣ የፖለቲካ አመለካከትን፣ ቋንቋን፣ ሀብትንና የመሳሰሉትን መሰረት በማድረግ በአገልጋዮቿና ምእመኖቿ ላይ ልዩነት ሳታደርግ በእኩልነት ታገልግላለች” ቢልም ሲኖዶሱ ሕገ ቤተ ክርስቲያን በ መጣስ ውግንናው ለአንድ ብሔር፣ ፖለቲካዊ አመለካከት፣ ተመሳሳይ ሀገረ-መንግስት ቅርፅ ተጋሪዎች እና ቋንቋንና ማንነት ጫኝ ጠቅላይ-አግላዮች እንደሆነ ደጋግሞ አሳይቷል።
እንደ ማሳያ፣ ሲኖዶሱ “የኔ” የሚላቸውን ማሕበረሰቦች ተጠቁ ብሎ ባሰበ ጊዜ መግለጫ ያወጣል፣ ሰልፍ ይጠራል፣ በቢልዮኖች የገንዘብ ድጋፍ አሰባስቦ ይረዳል።
Tweet
የኢኦተቤክ ሲኖዶስና መዋቅሩ ከላይ ከተጠቀሰዉ አለፎ በትግራይ ህዝብ ስም ጭምር ለምኖ ያሰባሰበውን ድጋፍ “የኔ” ለሚላቸው ማህበረሰቦች የሚሰጥ የዘረኞች ዋሻ መሆኑን ፀሀይ የሞቀው ሀቅ ነው። ለዚህ ማሳያ ከ600-800ሺ ንፁሓን ተጋሩ ሲያልቁ፣ ጥንታውያን ገዳማት ሲፈርሱና ሲራከሱ፣ በመቶ ሺዎች የትግራይ እናቶች፣ ልጃገረዶችና መነኮሳይት በመንጋ ሲደፈሩ ምንም ሳይመስላቸውና ግፋ በለው እያሉ በገንዘብና በፕሮፖጋንዳ ሲደግፉ እንዳልከረሙ፤ ከወራት በፊት በአንድ የሰፈራቸው ካህን ቀብር ስነ ሥርዓት ሊቀ ጳጳሳት በተሰባሰቡበት አቡነ ማርቆስ የተባሉ ጳጳስ “እነ ኣፄ ሃይለስላሴ፣ እነ በላይ ዘለቀ፣ ቴዎፍሎስ፣ የሽዋው ተክለሃይማኖት ከመቃብር ውጡና ኑ ኣግዙን” ሲሉ አድምጠናል።
ሌላው የሲኖዶሱ የዘረኝነነት ሁነኛ ማሳያ ቀኖና ቤተ ክርስቲያን ለምን ተጣሰ ሳይሆን ማን ጣሰው የሚያስጨንቃቸው መሆኑ ነው። ከሁለት አመት በፊት በጎጃም የተከናወነውን የጳጳሳትና ፓትርያርክ ሹመት የዚህ ዘረኝነት እይታ ማስረጃ ነው። ይህ ጉዳይ ከቀኖናም ያለፈ የዶግማ ልዩነት ያለበት ሲሆን (የቅባት እምነት ተከታዮች ስለሆኑ)፣ በኦሮምያ እንዳስጮኹት በትግራይም እያስጮኹት እንዳለው አለማጮኻቸው፣ የመንግስት ጣልቃ ገብነት አለመጠየቃቸውና ፈጥነው ለውሳኔ አለመድረሳቸው ብቻ ሳይሆን ሰዎቹ ቅባቶች ሆነው ሳለ አውግዞ እንደመለየት፣ የተሿሿሙትን ሹመት ተነስቶ በቀድሞ መዓርጋቸው እንዲቀጥሉ ማድረጋቸውን ይታወሳል።
በተጨማሪም ከ7 ዓመት በፊት በኢሳት ቴለቭዠን፣
Tweet
የሚል ዜና ሲስተጋባ የቤተ ክርስቲያንን ማዕከላዊነት ተጣሰ ፣ የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ተሸረሸረ ብለው ጣልቃ እንዲገባ የተማፀኑት የፌደራል ሆነ የክልል ባለስልጣን አልነበረም። እንዲሁም “አንድ ሲኖዶስ ፣ አንድ ፓትርያርክ ፣ አንድ መንበር” ብሎ ፖለቲካዊ መፎክር ያሰማ ቤተክህነትም ሆነ ማሕበር አልታየም ብቻ ሳይሆን ለሚድያ ውይይትም አልበቃም። ለምን ቢባል መልሱ ቀላል ነው፣ ሲኖዶሱ ለአንድ ብሔር፣ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ፣ ቋንቋ ተናጋሪዎች፣ . . . የቆመ ፍፁም ዘረኛ፣ አድሉኣዊና ፖለቲካዊ ስብስብ ስለሆነ ነው።
ከፖለቲካ አመለካከት አንፃር ከባንዴራ አጠቃቀም ጀምሮ ሲኖዶሱ ነጋ ጠባ ፌደራሊዝምን በመርገም በአሀዳዊ ስርዓት አቀንቃኝነቱ እውቅና ያተረፈ ነው።
Tweet
መች ይህ ብቻ፣ ሚያዚያ 2021 ዓምፈ አቡነ ቴዎፍሎስ በሚባሉ የሰሜን ካሊፎርኒያ ኔቫዳና አሪዞና አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የሚመራ “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የዘር-ጥፋት መከላከያ ተቋም (ኢተክዘተ)” የተሰኘ ተቋም የተቋቋመ ሲሆን፣ ዓላማውም “to protect and safeguard #Christians, #Amharas, #Amhara_Muslims who have been the targets of elimination by the current government intensified more in the last three years” መሆኑን ይፋ ሲያደርጉ፣ ሲኖዶሱ ለአንድ ብሔር/ማንነት፣ ፖለቲካዊ አመለካከትና፣ ቋንቋ ተናጋሪዎች እንደሆነ ሁነኛ ማሳያ ነበር። ይህ ተቋም በትግራይ የደረሰ የንጹሐን እልቂት፣ የስነ ልቦና ጉዳትና የአካል መጉደል እንዲሁም የጥንታውያን ገዳማት መውደምና መመዝበር አንዳች ነገር ሳይተነፍስ ይልቁንም በትግራይ የተፈጸሙ ግፎችና የወደሙ ጥንታውያን ገዳማት ፎቶና ቪድዮ አማራ ክልል እንደተፈጸሙ አድርጎ ሰነዶች በማዘጋጀት የተለያዩ አገራት ኤምባሲዎችን በማደናገር ጩኽት የሚቀማ እና ገንዘብ የሚሰበስብ ነውር የማውቅ ተቋም ነው።
4) የቤተ ክርስቲያን አቋም በሚገልፀው በ አንቀፅ 9.4 (ሀ) ላይ “በ ቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደር ውስጥ ለሚፈፀሙ የስራ ጉድለቶች በ ቤተ ክርስቲያኒቱ ሕግና ስርዐት መሰረት የመቆጣጠር፣ የመቅጣት፣ የማረም ከስራ ማባርና ጡረታ የማግለል ሥልጣን አላት።” ቢልም ተጋሩ የማጥፋት ዘመቻ በተካሄደባቸው እና እየተካሄደባቸው በሚገኙ ሶስት ዓመታት በውጭና በሀገር ውስጥ ያሉ የትግራይ ማሕበረ ካህናት፣ ማሕበረ ምእመናን፣ የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማሕበር፣ የነገረ መለኮት ምሩቃን ማሕበር በደብዳቤ በተደጋጋሚ የዘር ማጥፋት ጦርነቱ እንዲቆም ተማፅነው ሰሚ አላገኙም። በተጨማሪም በዚህ የዘር ማጥፋት ዘመቻ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የተሳተፉትን የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮች ከድርጊታቸው እንድታስቆም፣ ቀኖና እንድትሰጥ፣ ያልታረሙትና በግላጭ የታሳተፉትን ደግሞ አውግዛ እንድትለይ ያቀረቡትን ክስና ተማፅኖ በ አንቀፅ 9.4 (ለ) ላይ እነደሰፈረው “. . . በዲሲፕሊን ጉባኤ/በአስተዳደር ጉባኤ/በመንፈሳዊ ፍርድ ቤት/በቋሚ ሲኖዶስ አልያም በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ” አቅርበው መንፈሳዊ ዳኝነት በመስጠት ፈንታ እንመራበታለን የሚሉትና ሌሎች የሚከሱበትን ሕግ ሽረውታል።
5) የመልካም አስተዳደር መርሖዎች በተሰኘ አንቀጽ 11 ላይ “መንፈሳዊነት፣ ፍትሐዊነት፣ ሕጋዊነት፣ አሳታፊነት፣ ግልፀኝነት፣ ተጠያቂነት፣ ተደራሽነት ፣ምላሽ ሰጪነት፣ ሚስጢር ጠባቂነት፣ ታማኝነት” በማለት ቢዘረዝርም አንዳቸውም ባለማክበር ሌሎች የሚከሱበትን ሕግ ሽረውታል።
ለምን ቢባል?
ከመንፈሳዊነት ይልቅ በዘረኝነት፣ ስጋዊነትና ፖለቲከኝነት የተጠቁ ስለሆኑ።
Tweet
በምሳሌ 6፥16 እግዚአብሔር የሚጠላቸው ስድስት ነገሮች ያለሐፍረት በዓውደምህረት ሳይቀር የሚፈፅሙ ስለሆኑና ይልቁንም “የእግዚአብሔር ነፍስ አጥብቃ ትጸየፈዋለች” የተባለለትን በወንድማማች መካከል ጠብን የሚዘሩ ስለሆኑ።
Tweet
በሕጋዊነትም ቢሆን ሕገ እግዚአብሔር ፣ ሕገ ቤተ ክርስቲያንና ሕገ ሰብእ የሚጥሱና ሲነገራቸውም ለምን ተነካን በሚል ውግዘትና ስም ማጥፋት የሚቀናቸው ስለሆኑ።
Tweet
ተጠያቂነት የሚባል ጭራሹ የማይታሰብበት ተቋም ቢኖር ይህ ተቋም ነው። ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ከቤተ ክርስቲያኗ ተልዕኮና አባታዊ ስነ-ምግባር ባፈነገጠ መልኩ፣ በዘር ማጥፋት የተሳተፉ ነውረኛ አገልጋዮቿ ተጠያቂ ላለማድረግ የኦርቶዶክስ አማኝና የመግቢያ በር የሆነውን የትግራይ ህዝብ እንዲጠፋ የወሰኑና ፍትሕ እንዳይነግስም ፍትሕ ለመቅበር አትዋሽ የሚለዉን የእግዚአብሔር ሕግ ተላልፈው ሐሰተኛ ምስክር በመሆን ፍትሕ የሚቀብሩ በመሆናቸው። የትግራይ ማሕበረ ከሀናት እና ምእመናንን ጩኸት ምላሽ በመስጠት ፈንታ፣ ምላሽ ባለመስጠት የዘር ፍጅቱ ፊታውራሪ መሆንን መረጡ።
ዓብይ አሕመድ ወደ ስልጣን ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ አቡነ እንባቆም የተባሉ የሀገረ ኢየሩሳሌም ገዳማት ሊቀ ጳጳስ ተጋሩ መነኮሳት ፓስፖርታቸው ቀምተው ፣ ሰብአዊ መብታቸውን ገፈው ፣ ደጀ ሰላም እንዳይሳለሙ ፣ በቤተ ክርስቲያን ገብተው እንዳይቀድሱና እንዳያስቀድሱ ፣ ስጋ ወደሙ እንዳይቀበሉና ክርስትና እንዳያነሱ መከልከላቸው ለሲኖዶሱ አቤቱታ ቢያቀርቡም ፍትሕም ሆነ መፍትሔ ተነፍገው በሰው አገር ልእንግልትና ለመከራ ዳርገዋቸዋል።
ፍትሕ በመንፈጋቸውና ምላሽ በአግባቡና በጊዜው ባለመስጠታቸው በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀፅ 12 (1) “ማነኛውም የቤተ ክርስቲያኒቷ አገልጋይ በ ቤተ ክርስቲያኒቱ ሕግ ፊት እኩል ሆኖ የመታየት መብት አለው” የሚለውን ፣ አንቀጽ 12(2) “ማነኛውም የቤተ ክርስቲያን አባል ደረጃው በፈቀደለት መጠን በ ቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ በሚደረጉ መንፈሳዊ ፣ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የመሳተፍ መብት አለው” የሚለውን፣ አንቀጽ 12 (3) “ማነኛውም የቤተ ክርስቲያን አባል ለደረሰበት አስተዳደራዊ በደል ቅሬታ የማቅረብና ላቀረበው ቅሬታም ለቀረበበት ቅሬታም ዳኝነት የማግኘት መብት አለው” የሚለውን ፣ አንቀጽ 12(6) “ማነኛውም የቤተ ክርስቲያን አባል በዘር፣ በብሔር፣ በቀለም፣ በሃብት ወይም በሌሎች ከሚፈፀም አድልአዊ አሰራር የመጠበቅ መብት አለው” የሚለውን፣ አንቀጽ 12(13) ላይ ”ማነኛውም የቤተ ክርስቲያን አገልጋይና ሰራተኛ በሕጋዊ ውሳኔ ካልታገደና ካልተሰናበተ በቀር ሰርቶ ደመወዝ የማግኘት መብቱ በሕግ የተጠበቀ ነው” የሚለውን የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮች መሰረታዊ መብቶችና፣ በ አንቀጽ 13(1) ላይ “ምእመናን በ ቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ የሚሰጡ መንፈሳዊ ፣ ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልጋሎቶችን ደረጃቸው (አቅማቸው) በሚፈቅደው መሰረት በእኩልነትና ያለ አድልዎ የማግኘትና የመጠቀም መብት አላቸው” የሚለውን የምእመናን መሠረታዊ ምብቶችን ጥሰዋል።
6) የሰራተኛ መሰረታዊ መብትና ግዴታዎች በሚደነግገው አንቀጽ 12 (12) ላይ “ማነኛውም የቤተ ክርስቲያን አገልጋይና ሰራተኛ ራሱን ከሙስናዊ አሰራር ነፃ በማድረግ ቤተ ክርስቲያንና ምእመናንን በመንፈሳዊነት፣ በቅንነትና በታማኝነት ማገልገል አለበት” ቢልም ቅሉ የኢኦተቤክ ቤተ ክህነት አገልጋዮች ግና በሙስና የተዘፈቁ ናቸው። የቤተ ክህነቱ አገልጋዮች መዓርገ ክህነትና ጵጵስና ለመሾም፣ የአገልግሎት እድገት ለማግኘት፣ የደብር አለቃ ለመሆንና፣ የውጭ አገራት ምድብ ለማግኘት በመቶ ሺዎች እጅ መንሻ መቀበል የተለመደ አሰራር (Modus Operandi) ያደረጉት ሲሆን፣
ጌታ ቢመጣ በማቴዎስ ወንጌል 21፥13 እንደተጻፈው “ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች ተብሎ ተጽፎአል፥ እናንተ ግን የወንበዶች ዋሻ አደረጋችኋት” በማለት በጅራፍ ገርፎ ያስወጣቸው ነበር።
Tweet
7) የቅዱስ ሲኖዶስ ዓላማ በሚገልጸው አንቀጽ 15 ስር፣
7.1) በ አንቀጽ 15(1) ላይ “ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ሃይማኖታዊ ፣ ቀኖናዊና ታሪካዊ ትውፊት እንዳይፋለስ መጠበቅና ማስጠበቅ አገልግሎቱም የተሟላ እንዲሆን ማድረግ” የሚል ተቀምጦ ይገኛል።
ሆኖም ግን የቅዱስ ሲኖዶሱ አባል የሆኑትን አቡነ ሚካኤል የተባሉ ጳጳስ “በሥላሴ እያመንኩና እየተማፀንኩ፣ ማርያም ምስክሬ አድርጌ፣ በእናቴ በቤተ ክርስቲያን ፊት ቁሜ ጠላቴን ሰይጣንን እክዳለሁ” የሚለውን ትምህርተ ወጸሎተ ሃይማኖት የሚያፋልስ “ጁንታ ከሚገዛን ሰይጣን ቢገዛን ይሻላል፣ ሰይጣን ቢያንስ እግዚአብሔርን ይፈራል” ሲናገሩ በ አንቀጽ 18 (5) ላይ “አንድ የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ሃይማኖትንና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን የሚያፋልስ ሆኖ ከተገኘ ከአባልነቱ ይሰረዛል” የሚለውን መሰረት በማድረግ እርምት ባልመውሰድ ሽረዉታል።
ይህ ለምሳሌ የቀረበ እንጂ ብዙ ከሃይማኖታዊ አስተምህሮም ሆነ ከክርስቶስ ባህርይ የማይሄዱ መፋለሶች ያሉባቸው ገድላት፣ ተአምራትና ድርሳናትን ማጣቀስ ይቻላል።
7.2) በ አንቀጽ 15 (2) ላይ “ጥንታዊውን የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ቤቶችን መጠበቅና ማስፋፋት” ፣ እንዲሁም በአንቀጽ 15 (3) ላይ “ገዳማትና ስርዓተ ገዳማትን እንዲሁም ስርዓተ ምንኩስናን መጠበቅና ማስፋፋት” የሚል ቢገኝበትም፣ ማስፋፋትና መጠበቁ ይቅርና እንደ ደብረ ዳሞ፣ ደብረ አባይ፣ ዋልድባ የመሳሰሉ ጥንታውያን የቤት ክርስትያን ትምህርት ቤቶችና ገዳማት ሲወድሙና መንኮሳት ፣ የአብነት መምህራንና የአብነት ተማሪዎች ሲበተኑ፣ ስርዓተ ገዳምና ስርዓተ ምንኩስና አደጋ ውስጥ ሲገባ፣ ሲኖዶሱ ለመንግስት ጦር እና የአማራ ክልል ታጣቂ ሃይሎች የገንዘብና የፕሮፖጋንዳ ድጋፍ በመስጠት የህዝብን እልቂት ደገፈ።
ዓለም የእነዚህ ጥንታውያን ትምህርት ቤቶች መፍረስ አሳስቦት ድምጽ በሚሆንበትም “ምንም አልተፈጠረም ውሸት ነው” በማለት የእውነት ግርዶሽ መሆን በመምረጡ ሕገ ቤተ ክርስቲያንን ጥሷል። ሌላዉ ቢቀር እንደነ ደብረ ኤልያስ በመሳሰሉት ገዳማት ከስርዓተ ገዳማትና ስርዓተ ምንኩስናን ባፈነገጠ መልኩ በገዳማት ላይ ሽፍቶች ምሽግ እስከ መስራት ሲደርሱ ሲኖዶሱ የወሰደው አንዳች እርምጃ የለም።
7.3) በ አንቀጽ 15 (4) ላይ “የስርዓተ ክህነት አሰጣጥና አጠባበቅ በፍትህ መንፈሳዊ በተደነገገው መሰረት እንዲፈፀም ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ ነው” ቢልም በዚህ መልኩ ሳይሆን ሕጉን እየተጣሰ በዘመድና በገንዘብ ክህነት እየታደለ፣ አሁን ለምናየው ካህን አይደለም አሳዳጊ የበደለውም የማይናገረው ንግግር በመናገር የቤተ ክርስቲያኒቱ ስም የሚያስነቅፉና ለብዙ ምእመናን ፍጅት፣ መፈናቀል እና ስደት ምክንያት ሆኗል።
7.4) በ አንቀጽ 15 (7) ላይ “የሰው ዘር ሁሉ ከርሃብ፣ ከእርዛት፣ ከበሽታና ከድንቁርና ተላቆ በሰላምና በአንድነት በመተሳሰብና በመረዳዳት በመንፈሳዊ ሕይወት እንዲኖር ማስተማርና መጸለይ ነው” ቢልም ሲኖዶሱ ተልዕኮውን በመዘንጋት ሚልዮኖች ለማስራብ፣ በእርዛትና በበሽታ እንዲያልቁ ለመቀስቀስ በጣልቃ አትግቡብን ሰበብ፣ ሰብአዊ እርዳታ እንስጥ ላሉ አሜሪካውያን “ተዉ፣ አቁሙ” ለማለት 12 ጳጳሳት አሜሪካ ነጩ ቤተ መንግስት ድረስ በመላክ ረሀቡ፣ እርዛቱና በሽታው እንደ ጦር መሳርያ በመጠቀም ጥሰውታል።
ሌላዉ ቤተ ክህነቱ ህዝቡ በአደንዛዥ ስብከቶችና ተረቶች እንዲደነቁር ትልቅ ሚና ተጫውቷል፣ እየተጫወተም ይገኛል። ቤተ ክህነቱ የሰላምና የአንድነት ተምሳሌት በመሆን ፈንታ በብሔር፣ በቋንቋ፣ በፖለቲካዊ አስተሳሰብ በሚያደርገው አድልዎ የሰላምና የአንድነት ጠንቅ በመሆን ሕጉን ሽሯል።
7.5) በ አንቀጽ 15 (7) ላይ የቅዱስ ሲኖዶስ ዓላማ “በ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ፍትህ ርትዕ እንዲሰፍን የሁሉም መብት በሕግ ፊት እንዲከበር እኩልነትና አንድነት እንዲጠናከር ጠንክሮ መስራት” ነው ቢልም፣ ከላይም ለመጠቃቀስ እንደሞከርኩት በተቃራኒው ፍትህ ርትዕ እንዳይሰፍን ፣ የሁሉም መብት በሕግ ፊት እንዳይከበርና፣ እኩልነትና አንድነት እንዳይጠናከር ጠንክሮ በመስራት ሕጉን ሽሯል።
8) በ አንቀጽ 17 (19) ላይ የቅዱስ ሲኖዶስ ተግባርና ሀላፊነት ስር “በ ቤተ ክርስቲያን ስም የሚሰበሰብ ነገር ግን ቅዱስ ሲኖዶስ በቀጥታ የማያውቀው፣ የማይቆጣጠረውና የማያዝበት ገንዘብና ማንኛውም ንብረት እንዳይኖር ጥብቅ ቁጥጥር ያደርጋል፣ ተግባራዊነቱም ይከታተላል፣ በሕግም መብቱን ያስጠብቃል” እንዲሁም በ አንቀጽ 17 (24) ላይ “. . . የማህበራት ገንዘብና ንብረት በቤተክርስቲያኒቱ ሞዴላ ሞዴል እንዲሰበሰብ ያደርጋል፣ የማህበራቱን ገንዘብ ንብረትና አስተዳደር ይቆጣጠራል፣ ኦዲት ያደርጋል፣ ማስተካከያ እርምት ይወስዳል። ማህበራቱ በ ቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደር ጣልቃ እንዳይገቡ ይቆጣጠራል . . .” ይላል።
ነገር ግን ማኅበረ ቅዱሳን የተባለ ተቋም በ ቤተ ክርስቲያን ስም ከምእመናን ያግበሰበሰውን ቅዱስ ሲኖዶስ በቀጥታ የማያውቀውና የማይቆጣጠረው እንዲሁም የማያዝበት በቢልዮኖች የሚቆጠር ሃብትና ንብረት ከአስር ዓመት በፊት ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንዲያስረክብ በቅዱስ ሲኖዶስ ቢወሰንም ተፈጻሚ ሳይሆን ቀርቷል። ይህ ብቻ ሳይሆን የሚሰበስበው ገንዘብና ንብረት በ ቤተ ክርስቲያኒቱ ሞዴላሞዴል እንዲሰበሰብ፣ ኦዲት እንዲያደርግ ቢያዝም ሲኖዶሱ ጥብቅ ቁጥጥር ባለማድረጉ፣ ተግባራዊነቱ ባለመከታተሉና ፣ በሕግም መብቱን በማስጠበቅ ግዴታው ባለመወጣቱ ሕጉን ሽሯል።
በተጨማሪም “ሲኖዶሱ ማህበራት በ ቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደር ጣልቃ እንዳይገቡ ይቆጣጠራል” የሚለውን ተጥሶ፣ ዛሬ ማሕበረ ቅዱሳን በሲኖዶሱ ጣልቃ መግባት ብቻ ሳይሆን ለሲኖዶሱ ሕገ ደንብ ካላወጣሁለት፣ እገሌ የሚባል ጳጳስ/ካህን ካልተሾመ ወይም ካልተሻረ ሞቼ እገኛለሁ እያለ ሲፈነጭ ተገቢውን ቁጥጥርና እርምት ባለመወሰዱ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሉዓላዊነት እንዳይከበር ተባባሪ በመሆን ሕጉን ሽሯል።
9) በ አንቀጽ 35 (1) ላይ ስለ ኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ “በስርዓተ ምንኩስና በድንግልና መንኩሰው በክህነት ቤት ክርስቲያንን ከሚያገለግሉና ለኤጲስ ቆጶስነት ብቁ ከሆኑ መነኮሳትና ቆሞሳት መካከል በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በሚቋቋም አስመራጭ ኮሚቴ አማካኝነት ተገምግመውና ተመዝነው በቅዱስ ሲኖዶስ ተቀባይነት ሲያገኙ ለውድድር ይቀርባሉ” ይላል።
ነገር ግን ያልመነኑና ፍትፍት ያልሰለቻቸው፣ ድንግልና የሌላቸውና ልጆች የወለዱ፣ ደመወዝ፣ ቤት እና መኪና የሚያጓጓቸው፣ በ ሐዋርያት ስራ 8፡18-19 ላይ “ሲሞንም በሐዋርያት እጅ መጫን መንፈስ ቅዱስ እንዲሰጥ ባየ ጊዜ፥ ገንዘብ አመጣላቸውና። እጄን የምጭንበት ሁሉ መንፈስ ቅዱስን ይቀበል ዘንድ ለእኔ ደግሞ ይህን ሥልጣን ስጡኝ አለ” እንዲል በሲሞናዊነት ግብር መዓርገ ክህነት በሚልዮኖች እየቸበቸቡ መንፈሳውያን ያልሆኑ ሰዎች መንፈሳዊ ሥራ እንዲሰሩ በመሾምና፣ በ አንቀጽ 12 (12) ላይ የሰፈረውን “ማነኛውም የቤተ ክርስቲያን አገልጋይና ሰራተኛ ራሱን ከሙስናዊ አሰራር ነፃ ማድረግ አለበት” የሚለውን በመተላለፍ ሕግ ሽሯል፣ እግዚአብሔር አሳዝኗል፣ የቤት ክርስቲያኒቱ ልዕልና አዋርዷል።
የቤተ ክህነቱ አሁን የምናያቸውን ከተልዕኮው ውጭ በፖለቲካና በመለካዊነት የሚጠቃዉ የዚህ ጦስ ነው።
10) ሲኖዶስ ኢትዮጵያ አንቀጽ 37 በመጥቀስ የትግራይ አባቶችን ሕገ ቤተ ክርስቲያን ጥሷል ሲል ከሷል። የትግራይ አባቶች ግን በዚህ አንቀጽ ንኡስ አንቀጽ 1፣ 2 እና 3 የተቀመጡት ተግባራት በምሉእነት እየፈጸሙና እያስፈጸሙ ይገኛሉ።
ይልቁን በዚህ ንዑስ አንቀጽ የተዘረዘሩትን የሊቀ ጳጳስ ተግባርና ሓላፊነት በመሻርና በ ዮሐንስ ወንጌል 10፣11 ላይ “. . . እረኛ ያልሆነው በጎቹም የእርሱ ያልሆኑ ምንደኛ ግን ተኩላ ሲመጣ ባየ ጊዜ በጎቹን ትቶ ይሸሻል …. በጎቹንም ይበትናቸዋል” ተብሎ እንደተጻፈው፣ ባሳለፍናቸው የመከራ ጊዝያት በተሾሙበት ሀገረ ስብከት በመገኘት በጎቻቸው እንደ መጠበቅና እንደ ማጽናናት ሃገረ ስብከታቸውን ትተው አዲስ አበባ የከተሙ የደቡብና የደቡብ ምብራቅ ትግራይ አህጉረ ስብከቶች ሊቀ ጳጳስ አቡነ ዲዮስቆሮስና፣ የምዕራብ ትግራይ ሑመራ ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ አቡነ ሉቃስ ሲሽሩትና በቅዱሳን አበው በመጽሐፈ ፍትህ መንፈሳዊ አንቀጽ 5፤ ንዑስ አንቀጽ 138 ”ኤጲስ ቆጶስ ሆይ ከበጎች የተለየህ ብትሆን ጠላታቸው አንተነህ፤ የእግዚአብሔር ባላጋራው (ጠላት) አንተ ነህ። እግዚአብሔር ጠባቂ የሆናቸውን በጎች የምታጠፋ አንተ ነህ” የሚለውን ሕገ ሲኖዶስ የጣሱትን መገሰጽ ነበረባቸው። አለመታደል ሆኖ በዚህ ፈንታ፣ ሕገ ቤተ ክርስቲያንና ፍትህ መንፈሳዊ የሚያዘውን ግዴታቸውን የተወጡት የትግራይ አባቶች መክሰስን መርጧል።
11) የትግራይ አባቶችን ለመክሰስ ሕገ ቤተክርስቲያን አንቀጽ 38 ጭምር መጠቀሱ ደግሞ እጅግ በጣም አስደናቂ ያደርገዋል። በ አንቀጽ 38 (1) ላይ “ሊቀ ጳጳስ ፣ጳጳስ ወይም ኤጲስ ቆጶስ በትሾመበት ሀገረ ስብከት ይኖራል” የሚለውን ከላይ የጠቀስኳቸው ሊቃነ ጳጳሳት ሽረውታል። ይህ ስል የትግራዮቹ ላይ ማተኮር ስለ ፈለግኩ እንጂ አብዛኞቹ ሊቃነ ጳጳስት አህጉረ ስብከቶቻቸውን ትተው አዲስ አበባ በመቀመጥ በርቀት ነው የሚያስተዳድሩት።
Tweet
በተጨማሪም አንቀጽ 38 (2) ላይ “በቅዱስ ፓትርያርኩ ፈቃድ ወይም በሥራ ወይም በሕመም ምክንያት ካልሆነ በቀር ከሀገረ ስብከቱ ውጭ ከ15 (ዐስራ አምስት) ቀናት የበለጠ መቆየት የለበትም” ቢልም ቅሉ፣ አብዛኞቸ ሊቃነ ጳጳሳት ቀናት አይደለም ወራት ከሀገረ ስብከታቸው ወጥተው በአዲስ አበባ ነው የሚቀመጡት።
ይህን የሚያጠናክር በረስጠብ (ሕገ ሲኖዶስ) “አንድ ኤጲስ ቆጶስ ወይም ጳጳስ መንበሩን ትቶ ወደ ሌላ ሀገረ ስብከት ይሔድ ዘንድ አይገባውም”፣ እንዲሁም በኒቅያ “ኤጲስ ቆጶሳት ከሀገረ ስብከታቸው ወደ ሌላ ሀገረ ስብከት ቢሔዱ ከ 6 ወር የበለጠ አይኑሩ። ከዚህ የበለጠ ቢኖሩ ወይም ሀገረ ስብከታቸውን ትተው በሌላው ሀገር በዓለ ትንሳኤን ቢያከብሩ ከሹመታቸው ይሻሩ” የሚለውን ሰለስቱ ምዕት የደነገጉትን ቀኖና ቤተክርስቲያን ጥሰው ሳለ፣ ቀኖናውን ያከበሩ የትግራይ አባቶችን በቀኖና ቤተ ክርስትያን መክሰሳቸው፣ ህዝቡ ሕገ ቤተ ክርስቲያንና ቀኖና አያውቅም ከሚል ንቀት የሚነሳ ነው።
12) አንቀፅ 50 (1) ላይ “የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብጹዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ሀገረ ስብከት ነው” ቢልም፣ በጥቅም 2013 ዓ.ም የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ “የሀገረ ስብከቱ አሠራር ላይ አመቺ ሆኖ ስለአልተገኘ ከሕገ ቤተ ክርስቲያኑ እንዲወጣ እና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት እንደማንኛውም ሀገረ ስብከት ራሱን ችሎ ሊቀጳጳስ ተመድቦለት እንዲመራ ወስኗል” በማለት ሕገ ቤተክርስቲያን ሳያሻሽሉ ቅዱስ ፓትርያርኩ ያለ ሀገር ስብከት በማስቀረት ሕጉን ሽሯል።
ውድ አንባብያን ሆይ!
ታድያ ከላይ ባየናቸው አንቀጾች መሰረት ማን ነው ሕገ ቤተ ክርስቲያን የጣሰው? ህገ ወጥ መባል የሚገባው የኢኦተቤክ ሲኖዶስ አይደለምን?
Tweet
እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ የትግራይ አባቶች በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ንዑስ አንቀጽ 104 በሚሰጣቸው ሥልጣን ሐምሌ 9/2015 ዓ.ም ሲመተ ኤጲስቆጶሳት ሲያከናውኑ የ5 ኪሎው ሲኖዶስ ተሰባስበው ማውገዛቸው አይቀርምና፣ ከወዲሁ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ”ዘአውገዘ በከንቱ ውጉዝ ውእቱ ለሊሁ” እንዲሉ ከላይ በዘረዘርኳቸው የሕገ ቤተክርስቲያን ጥሰቶች ምክንያትና ከተልዕኮው በማፈንገጥ በዘር ፍጅት በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ የተሳተፈው የኢኦተቤክ ሲኖዶስ ውጉዝ ሰለሆነ ቢያወግዝም ንጉሥ ሰሎሞን በመጽሐፈ ምሳሌ 26፡2 “እንደሚተላለፍ ድንቢጥ ወዲያና ወዲህም እንደሚበርር ጨረባ፥ እንዲሁ ከንቱ እርግማን በማንም ላይ አይደርስም” እንዳለው ውግዘቱ ትርጉም እንደማይኖረው መግለጽ ያስፈልጋል።
ወስብሓት ለእግዚአብሔር ፣ ወለ ወላዲቱ ድንግል ፣ ወለ መስቀሉ ክቡር አሜን!
—————————————————————————————————-
ደጀን የማነ ተኽለ፣ አውስትራልያ በሚገኘው ኒው ሳውዝ ዌልስ ዩኒቨርሲቲ የፒኤችዲ ተማሪ ሲሆን፣ በመቐለ ዩኒቨርሲቲ፣ የጤና ኮሌጅ ስፔሻላይድ ሆስፒታል መምህርና ተማራማሪ ነው።